ከዋለልኝ እስከ ጊንጪ … እና ከዚያ ባሻገር – በያዬ አበበ

የዛሬ አራት አመት ሐሙስ ፣ ህዳር 2 2008 ዓ.ም. ጊንጪ ላይ ህዝባዊ ተቃውሞ ተለኮሰ። ለዚያ ህዝባዊ ተቃውሞ በተዘዋዋሪ ስነልቦናዊና ርዮታለማዊ መሰረት ያስቀመጠው የዋለልኝ መኮንን ጽሁፍ ላይ የሰፈረው ሀሳብ ነው። የጽሁፉ 50ኛው ዓመት መጪው እሁድ ህዳር 7 ፣ 2012 ዓ.ም. ነው።

ዋለልኝ በጽሁፉ ላይ ካነሳቸው አበይት ሀሳቦች ዋናዎቹ፦

1. ኢትዮጵያ የአንድ ብሄር/nation ሀገር ሳትሆን የብዙ ብሔሮች/nations ሀገር መሆኗን (ብዝሃነት)

2. የሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው የሚባለውን ‘ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት’ የቁጩ ብሔርተኝነት /”fake nationalism”/ በማለት ፈርጆ ፣ ያ ብሔርተኝንት ቢበዛ ለዐማራና ትግራይ የሚመጥን ማንነት እንጂ ለሌሎች ብሔሮች ማንነቶች የማይመጥን እንደሆነ ዋለልኝ በጽሁፉ ላይ አስፍሯል።

ከላይ ያሉት ሃሳቦች ዛሬ በአንዳንድ ልሂቃን ዘንድ ውግዘት ቢደርስባቸውም ፣ ዛሬ በእርግጠኝነት ማለት የሚቻለው ከ50 ዓመት በፊት የነበረቸው ኢትዮጵያና ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ መሰረታዊ ልዩነት እንዳላቸው ነው።

ዛሬ የኢትዮጵያ መሰረት በሕገመንግስቱ እንደሰፈረው ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሆነዋል። ዋለልኛዊው እይታ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ከስር ከመሰረቱ አፍርሶ እንደገና እየገነባት ይገኛል።

የዋለልኝ ሀሳብ የሀገሪቷን መሰረት ከመቀየር አልፎ በትውልድ ላይ ያደረሰው መሰረታዊ የስነልቦና ቅኚት ዛሬ በሀገራችን ከሚታዩት ስኬቶች ፣ ስጋቶችና ፈተናዎች ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት አለው።

የዛሬ አራት ዐመት ጊንጪ ላይ የፈነዳው ግብታዊ ህዝባዊ ተቃውሞ መነሾዎች ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ብሶቶች ቢሆኑም ፤ በሕብረብሔራዊ ፌደሬሽኑ ከ23 ዓመታት በላይ በብሔሮች ማንነት ላይ የተደረገው የማንነት ማብቃት /identity empowerment/ ሂደት በአዲሱ ትውልድ ላይ የፈጠረውን የብሔርተኝነት ስሜትና ወኔ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹን በንቃት የተከታተልን ሁሉ ያየነው ነው።

ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ በግሃድ ያሳዩት ግን ብሔርተኝነት በወጣቱ ትውልድ ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ፣ የብሔር ልሂቃንና ኃይሎች ውስጥ ምን ያህል የስትራቴጂ ክፍተት በሰፊው መኖሩን ጭምር ነው።

ከሁሉ ያስደነቀኝ ጉዳይ ዋለልኝ መኮንን ኢትዮጵያን ያየበት እይታ ያስመዘገበውን ስኬት (እንኳንስ የአንድነት ኃይሎች ቀርቶ) የብሔር ልሂቃን ራሳቸው ከጠበቁት በላይ በድንገት እንዳስደነገጣቸው (surprise) ነው።

ዛሬ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያልተረዱ በከፊል የገዢው ፓርቲ ፣ በብዙው ግን የተፎካካሪ ፓርቲዎች የብሔር ልሂቃን ከዋለልኝ-ባሻገር ሀገሪቱ ወዴት መሄድ እንዳለባት ርዕይም/vision/ ሆነ አጀንዳ የላቸውም ቢባል ማጋነን አይደለም።

ለዚህ ማስረጃው መልሰውና ተመላልሰው የሚያጠነጥኑት የብሔር ማንነት ጥያቄ ፓለቲካ መሆኑ ነው። የብሔር ጥያቄ በሕገመንግስቱ ውስጥ በሰፊውና በመሰረታዊ መልኩ ለብሔሮች ሉዓላዊነት በማጎናጸፍ ተመልሷል።

በቀጥዩ የሲዳማ ህዝባችን ህዝበ-ውሳኔ እንደሚደረገው ፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ጉዳይ የዋለልኝ አይነት “ብሔር ጥያቄ” ሳይሆን ፡ ብሔሮች ሕገመንግስታዊ መብታቸውን መጠቀምና ማስከበር ነው።

እኔ የማንኛውንም ብሔር ፣ ብሔረሰብና ህዝብ ሕገመንግስታዊ የራስን እድል በራስ የመወሰን መበት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲጠበቅና እንዲከበር አቋሜ ነው።

ምንም እንኳን ዛሬ ከነገስታቱ ሐውልት ጋር የመታገል አምሮት ያላቸው ጥቂት ወገኖች ቢኖሩም ፣ የጊንጪው ህዝባዊ ፍንዳታ በተግባር ያሳየን ተጨባጭ ጉዳይ ፡ ዋለልኛዊት ኢትዮጵያ ምንሊካዊት ኢትዮጵያን መተካቷን ነው።

ዛሬ የብሔር ልሂቃንና ኃይሎች ከ50 ዓመታት በፊት በእነ ዋለልኝ ትውልድ ምናብ ውስጥ የነበረው ሃሳብ በገሃዱ አለም ህያው ሆኖ ቢያዩትም ፡ የብዝሃዊነት አሸናፊነትን ወይ አልተቀበሉትም (they are in denial) ወይንም እውነታውን መቀበሉ የማንነት ፓለቲካቸውን ክስመት እንደዳያፈጥነው ሰግተዋል።

ከሁሉ በላይ ግን የብሔር ልሂቃንና ኃይሎች ከዋለልኛዊነት እሳቤ ስኬት ባሻገር ሀገሪቱ ወዴት እንደምታመራ አጀንዳ አለመቅረጻቸው ወቅታዊው ፈተናና ተግዳሮት ነው።

እዚህ ላይ ዋና ዋና ፈተናዎች ናቸው ብዬ ማስባቸውን ነጥቦች ላንሳ፦

1. ዋለልኝ የቁጩ ብሔርተኝነት ያለውን ‘ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት’ የሚተካም ሆነ የሚፎካከር ሌላ አማራጭ ሀገራዊ ማንነት አለመፈጠሩ

2. ‘ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት’ በከተማ ውስጥ ያለው እጂግ የዳበረና የደረጀ መሰረት በአንዳንድ ዋልታረገጥ/polarizing/ የብሔር ልሂቃን ወገኖች እንደ አደጋ/threat/ መታየቱና መፈረጁ

3. የሕብረብሔራዊ ህገመንግስታዊ ስርዓት ቅቡልነት እንዲሸረሸር በዋናነት ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ዋለልኝ “የቁጩ” ያለው ኢትዮጵያዊነት ልሂቃን መሆናቸው

4. በዋናነት ዛሬ ‘ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት’ ከከተሜነት ጋር የተቆራኜ መሆኑ

5. ሌላ አማራጭና አቻ ሀገራዊ ማንነት (ወይንም ሀገራዊ ማንነቶች /’ኢትዮጵያዊነቶች’) ለማዳበር የአምራች ኢንዱስትን ተጠቅሞ ግዙፍ ከተሞች መፍጠር የግድ በመሆኑ እና

6. ግዙፍ ከተሞችን ለመፍጠር የሚያስፈልገውን የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ከገዢው ፓርቲ እና ከቅንጂት-ወራሾች (የCUD መስመር ውስጥ ያሉ) የአንድነት ኃይሎች ሊሂቃን ውጪ አማራጭ የብሔር ኃይሎች ፎኖተ ካርታ አለማቅረባቸው ናቸው።

ከላይ የጠቀስኳቸው ነጥቦች ውጤት ዛሬም ከሀገራዊ ማንነት አንጻር “ሁሉንም አቃፊ ነኝ ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ብቁ ነኝ” ብሎ ራሱን ገበያ ላይ ያቀረበው ነባሩና የ’ቁጩው’ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ይሄንን ክፍተት እንደ ግሩም አጋጣሚ የሚጠቀሙና አርቀው ለ20 እና 30 ዓመታት ማለም የሚችሉ የተፎካካሪ ጎራ የብሔር ልሂቃንና ኃይሎች የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታቸውን ካላዘጋጁ በሀገሪቱ ፓለቲካ ፋይዳና ሚና ቢስ ይሆናሉ።

አሁን ካለውና ዋለልኝ ሰሚናዊ ብሎ ከፈረጅው ኢትዮጵያዊነት ጋር የሚፎካከር ‘ደቡባዊ’ መሰረት ያለው ሀገራዊ ማንነት ግንባታ ላይ ማተኮር የብሔር ኃይሎች ዋናው ወቅታዊ ስራ ነው።

ያለዚያ የዛሬዋ ዋለልኛዊትና ብዝሃዊት ኢትዮጵያ ያፈራችው ወጣቱ ትውልድ ፡ ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ከተሞች ሲፈልስ የሚዋጠውና የሚጠመቀው በ’ቁጩው’ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ክብር ጊንጪ ላይ ለተለኮሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ሰማዕታት!
ክብር 1960ዎቹ የተማሪው ንቅናቄ ትውልድ ሰማዕታት!

—————
ከዋለልኝ ጽሁፍ የተቀነጬበ (November 17, 1969)

“What are the Ethiopian peoples composed of? I stress on the word peoples because sociologically speaking, at this stage, Ethiopia is not really one nation. It is made up of a dozen nationalities with their own languages, ways of dressing, history, social organization and territorial entity. And what else is a nation? It is not made of a people with a particular tongue, particular ways of dressing, particular history, particular social and economic organization? Then, may I conclude that, in Ethiopia, there is the Oromo Nation, the Tigrai Nation, the Amhara Nation, the Gurage Nation, the Sidama Nation, the Wellamo [Wolayta] Nation, the Adere [Harari] Nation, and however much you may not like it, the Somali Nation.

This is the true picture of Ethiopia. There is, of course, the fake Ethiopian Nationalism advanced by the ruling class, and unwillingly accepted and even propagated by innocent fellow travelers.

What is this fake Nationalism? Is it not simply Amhara and to a certain extent Amhara-Tigre supremacy? Ask anybody what Ethiopian culture is? Ask anybody what Ethiopian language is? Ask anybody what Ethiopian music is? Ask anybody what the “national dress” is? It is either Amhara or Amhara-Tigre!!

To be a “genuine Ethiopian” one has to speak Amharic, to listen to Amharic music, to accept the Amhara-Tigre religion, Orthodox Christianity and to wear the Amhara-Tigre Shamma in international conferences. In some cases to be an “Ethiopian”, you will even have to change your name. In short to be an Ethiopian, you will have to wear an Amhara mask (to use Fanon’s expression). Start asserting your national identity and you are automatically a tribalist, that is if you are not blessed to be born an Amhara. According to the constitution you will need Amharic to go to school, to get a job, to read books (however few) and even to listen to the news on Radio “Ethiopia” unless you are a Somali or an Eritrean in Asmara for obvious reasons.”

“On the Question of Nationalities in Ethiopia”, STRUGGLE, November 17, 1969

3 COMMENTS

  1. ስሙን በውል ለማይጽፍ ገበሬ “Identity empowerment” በማለት በክልልና በቋንቋ ከፍሎ ቋንጭራና ቢለዋ አስጨብጦ የሰው አንገት ቀንጣሽ ትውልድ አፍርተናል። የዋለልኝ በጊዜው መቀባጠር የዛሬው የቁልቁለት መንገድ ጉዞ ጅመራ እንደነበር ሰው ሊያስተውል ይገባል። በየትኛውም ዓለም ቢሆን ሙሉ ፍትህ የሰፈነበት ሃገር የለም። በዳይም ተበዳይም ተቻችለው የሚኖሩበት የዓለም ክፍል ይበዛል። የእኛው ሃገር ግን የተንዛዛ ማለቂያ የሌለው የቆመን ቀብሮ ሌላው በተራው ልታይ የሚልበት፤ የጠገበውን ገፍትሮ የተራበውን በጠገበው ቦታ የሚስቀምጥ የመጠላለፍ ፓለቲካ ነው። በኢትዮጵያ የዘመን መስፈሪያ (በግዕዝ አይደለም) ከ 50ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሃገሪቱን የሚያምሰው ፊደል ቆጠርኩ የሚለው ክፍል ሰውን ለስብሰባ ጠርቶ በመትረጌስ የሚያጭድ ትውልድ ነው። በፓለቲካ ጥልፍልፍ ወንድምና እህቱን ያስገደለ፤ የገደለ፤ ያሰረ፤ ያሳሰረ፤ ያስገረፈ፤ የገረፈ እኩይ ትውልድ ነው። በህዝብ ስም የሚነግድ። የሃገሪቱ ችግር አማራና የትግራይ ልጆች ናቸው ከተባለ ያው አሁን ሁለቱም በሥልጣን ኮርቻው የሉበትም። ግን አንገት የሚያርደው በኦሮሞ ስም በስልጣን ላይ የወጣ የኦሮሞ ክልል ለኦሮሞዎች ብቻ የሚለው ጊዜው የእኛ ነው በማለት ስልጣኑን ተገን ያረገ የዘር ሽብርተኞች ናቸው። ዛሬ ዋለልኝ መኮነን በህይወት ቢኖር ምን ይለን ነበር? በአንድ ሃገር ውስጥ ብሄራዊ እይታ መኖሩ የሌሎችን መብት የሚነጥቅ አይደለም። እንዲያውም ያጎለብተዋል እንጂ። የሰው ሰውነቱ የሚያምረው “በህብረት” መኖርን ሲለምድ ነው። ግን እኮ ቀድሞ የተፓተለከ ፓለቲካ ነው ዛሬ ሃገሪቱን የወንበዴ ዋሻ ያረጋት። የንጉሱን መንግስት በግፍ አሽቀንጥሮ በመጣል ለ 17 ዓመታት ምድሪቱን ደም ያራጫት የወታደር መንጋ ሲንኮታኮት በቦታው የተተኩት ሻቢያና ወያኔ ናቸው። እስቲ አፍህን ሞልተህ የትግራይ ህዝብ ነጻ ህዝብ ነው የመናገር፤ የመጻፍ፤ የመሰብሰብ፤ የአምልኮ መብቱ ተጠብቆለታል ብለህ ንገራቸው። ፊትህ ላይ ይተፉብሃል። በቀን 5000 ሰው ነፍሴ አውጪኝ ብሎ የሚሰደድባት ኤርትራ “አፍሪቃዊቱ ኮሪያ” በመባል ትታወቃለች። ለውጥ ይሉሃል እሱ ነው። ፍሬፈርስኪ! Understanding Eritrea: Inside Africa’s most repressive state by Martin Plaut and John Young “Peasant revolution in Ethiopia: The TPLF 1974-1991 ማንበቡ ብቻ በፊት የነበረውና አሁን ያለውን የሁለቱ ድርጅቶች ሁኔታ በግልጽ ያስረዳል። Awate.com ድህረገጽ ላይ ሻቢያ በበረሃ እያለ ይሰራ የነበረውን አንድ የዓይን ምስክር ሲገጽ እንዲህ ይላል። ትርጉም የእኔ። ” ለውጊያ የምንቀሳቀስበት ስፍራ ምንም አይነት የዛፍ ምልክት የለውም። ከመካከላችን ግን አንድ ሰው ሁልጊዜ አጠና መሳይ እንጨት ተሸክሞ ይዞራል። ያ እንጨት ያጠፉ ሰዎች ታስረው የሚገረፉበት ወይም የሚገደሉበት ነው” ይለናል። ሻብያና ወያኔ ሌሎችም የፓለቲካ ፓርቲዎች ኢህአፓን ጨምሮ የትግል አጋሮቻቸውን በግፍ ይገድሉ እንደነበር የበረሃ ታሪካቸው በግልጽ ያሳያል። ስለዚህ አበበ እንዲዚህ ብሎ ነበር አየለ እንዲያ አለ እያላቹሁ የሞተ ነገር በመቆፈር ሰው ማስለቀሳችሁ ይቁም። ዛሬ የምናየውና የምንሰማው ከዘመናት በፊት ከሆነው የከፋና የባሰ ነው። እስቲ ሁላችንም የእኛ ነው በምንለው ክልል እንኑርና የኑሮ መጣፈጥን እንቅመስ። አይ ጊዜ የጅል ፓለቲካ። ህይወት የሚጣፍጠው ሲጋሩት ነው። የድር አውሬ ይመስል ለእኔ ብቻ የሚለው ፓለቲካ የሃገርና የህዝብን ሰላም የሚቀማ አንድ ከሌላው እንዳይግባባ ሆን ተብሎ የተሰመረ የአረመኔዎች የፓለቲካ ፈሊጥ ነው። ከ50ዎች ጀምሮ እድሜ ልካችሁን በተንሻፈፈ የፓለቲካ እይታ ህዝባችን የምታምሱ እናተ እብዶች ደግሞ አፈር ካልተመለሰባቹሁ ከክፋት አትድኑም። 52 ዓመት ያለፈው የዋለልን መኮነን “On the Question of Nationalities in Ethiopia” መጣጥፍም ዛሬም የሚያባላንና አንገት የሚያስቆርጠን ፓለቲካ በመሆኑ ፉርሽ ነው። አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ የሚለው መርህ በቂ መሆን ነበረበት። ምን ያህሉ የሃገራችን ህዝብ ነው 52 ዓመት ሞልቶት የሚሞተው? ጭቃ ፓለቲካ! አንድን ለማጠብና ለማጥራት ሲቃጣ ሌላውን የሚቀባና የሚገል። ይቅርብኝ!

  2. Isn’t Oromuma and Oromo nationalism the fakest of them all? That rule applies to each and everyone of the so-called nations, nationalities, and peoples. Not only are these associations fictional but they are also extremely dangerous and anti-democratic.

  3. ዋለለኝ መኮንን ከዘመን የቀደመ ለራሱ ብሄር ወይም ዘር ሳያዳለ ግፍን የተቃውመ ታላቅ ሰው ነው::ድሮ የባርያ ልጅ ስራቤት ጋላ ጉዴላ ወላሞ ደራሳ ሞረቴ ወዘተ በሚል ሰዎች በከፋ ግፍ የሚሰቃዩበትን እምቢ ብሎ የማንነት ጥያቄን በዚያ ድንቅ ትውልድ የዘራ በፍሬውም ዛሬ ህዝቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር መዳኘት መታከም ማከም ለቻሉበት ዘመን ደርሰናል:: ይህ ወደኋል ይመለስ ዘንድ የምትፈልጉ ናፋቂዎች ሲያምራችሁ ይቅር::ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ ብላችሁ በጨቋኝ ነግስታት ባላባቶች መሳፍንቶች ወላጆቻችን አያት ቅድም አያቶቻችንን የጨቆናችሁ በዛሬው ትውልድ ላይ ልትደግሙ አትችሉም:: ትንሽ ህሊና ቢኖራች ሁ ከዘመን የቀደሙት የዚያ የግፍ ዘመንን በደል በልብወለድ መልክ ደራሲ ዶ/ ሃዲስ አለማየሁ ያቀረቡትን ፍቅር እስከመቃብር ተረድታችሁ ትታረሙ ነበር ነገር ግን ታላቅ መጽሃፍ እነደሚለው አይን አላች ሁ አታዩም ጆሮ አላች ሁ ኣተሰሙም ራሴ ልቸምረው ህሊና አላች ሁ በጎ ማሰብ አይችልም ፈጣሪ ይማራችሁ::የዚያ ትውልድ መሬት ላራሹ ጥያቄን ያፈነ ንጉሳችሁ ድንቅ ጸሃፊ ዮፍታሄ ንጉሴን በምርዝ ያስገደለ ጋዜጠኛ አሳምነው ገብረወልድን በተገዛች ሴት ያሳረደ ሚስቱን ሴት ቤት ሞቶ ተገኘ በይ ብለው ያስገደዷትን ከአሜሪካ ድምጽ ሰምተናል::ማሞ መዘመር ሰላምዊ የሜጫና ቱለማ ባህላዊ ማህበር በማደራጀቱ የንጉሱ ሎሌ አክሊሉ ሃብተወልድ ሳያምንበት በንጉሱ ቀጭን ትእዛዝ ያሰቀለው አሳፋሪ ታሪካችሁ ተቀይሮ የገባር ልጆች ሚንሊክ ቤተመንግስትን ተቆጣጥረዋል ከፈለጋችሁ ማበድ መብታችሁ ነው:: በዋለልኝና በዚያ ዘመን የትግል ተሳትፎ ሰዎች ማንነታቸ የሚከበርበት ዘመን ደርሰናል:: የጽንፈኖች ስህተቶችን በማረም በተለይ በአማራ ላይ የተደረገው ዘመቻ ተስተካካሎ የሁሉም ብሄር ህዝቦች ተከባረው የሁሉም እኩል ሃገር ኢትዮጲያ አሮጌዋ ኢትዮጲያ ታድሳ ብቅ ትላላች ኣተፈርስም አትወድቅም::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.