የ’ልማት አርበኞች’ በሚባሉ አለቆች ቤተ ክርስቲያን የበይ ተመልካች ተደርጋለች፤ ሀ/ስብከቱም የሕግ ጥሰቱ አካል ኾኗል: የመሬትና የሕንጻ ኪራይ ጥናታዊ ሪፖርት

  • ከሕጋዊ አሠራር ውጭ በውስጥ ስምምነትና ድርድር እንዲከራዩ በመደረጉ፣ በመሐል ከተማ ከብር 500 – 3500 እየከፈሉ በቤተ ክርስቲያን ሀብት ሚሊየነር የኾኑ በርካታ ግለሰቦች አሉ
  • በአዲስ አበባ የመሬት ገበያ በማይታሰብ ኹኔታ፣ ዝቅተኛው 0.37 ሳንቲም ከፍተኛው ብር 70 በካሬ ሜትር መከራየቱ አማሳኞቹ እና ግለሰብ ነጋዴዎቹ እንዲበለጽጉባት ዕድል ሰጥቷል

* * *

  • በሦስተኛ ወገን አከራዮች እና በዝቅተኛ ዋጋ የተሰጡ ውሎችን በሕግ በማፍረስ በወጥነት የሚያገለግልና የቤተ ክርስቲያንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አሠራር መዘርጋት ይገባዋል
  • የአድባራቱን የመሬት እና የሕንጻዎች አስተዳደር በማእከል የሚመራ፣ በፓትርያርኩ የሚሰበሰብ የሥራ አመራር ቦርድ ያለው ጽ/ቤት በማቋቋም ገቢያቸው በሕግ የሚጠበቅበት አሠራር ያሻል

* * *

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተመረጡ አድባራት እና አንዳንድ ገዳማት፣ ከመሬት እና ከሕንጻ ኪራይ፣ ከመካነ መቃብር አፈጻጸም እና ከመኪና ሽልማት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከታኅሣሥ ጀምሮ ማጣራት ሲያካሒድ የቆየው ኮሚቴ፣ ጥናታዊ ሪፖርቱን ማክሰኞ፣ ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ እና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስአቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አጥኚ ኮሚቴ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረበው ማስታወሻ መነሻነት በተሰጠ ትእዛዝ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የአስተዳደር ጉባኤ የተቋቋመው ኮሚቴው ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ በ51 አጥቢያዎች ላይ ማጣራት እንደተካሔደና ከእነርሱም÷ በመሬት፣ በሕንጻ እና ሕንጻ ነክ ጉዳዮች ከፍተኛ ችግሮች ያሉባቸው፣ መካከለኛ ችግሮች ያሉባቸው እና በደኅና ኹኔታ ላይ የሚገኙ ብሎ በመለየት በማሳያነት ማቅረቡን ገልጧል፡፡

ኮሚቴው የመፍትሔ ሐሳቦችን በማካተት በ33 ገጾች አቀናብሮ ካቀረበው ጥናታዊ ሪፖርት ከገጽ 27 – 33 የሚከተለው ሰፍሯል፤

በሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ 15 አድባራት የሚገኙ ሲኾን ለገቢ ማስገኛ በሚል የተከራዩ የአድባራቱ ቦታዎች፣ ሱቆችና ሌሎች የገቢ ተቋማት ዝርዝር ኹኔታ ሲታይ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ የአድባራት ሓላፊዎችንና ግለሰብ ነጋዴዎችን የሚጠቅሙ ኾነው ተገኝተዋል፡፡

በአንዳንድ ቦታዎች የሚታየው ሙስናም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰፋፊ መሬቶች እና የንግድ ተቋማት ያለጨረታ ከሕጋዊ አሠራር ውጭ በተቀራመቱ ስግብግብ ነጋዴዎች እና ነጋዴዎች በጥቅም በያዟቸው የአድባራት አለቆች እና የአስተዳደር ሠራተኞች እጅ እንዲወድቁ በማድረጉ፣ የቤተ ክርስቲያን የቦታ እና የሱቆች ባለቤትነት ስማዊ እና በገዛ ንብረቷ የበይ ተመልካች እንድትኾን አድርጓታል፡፡

ከአዲስ አበባ የመሬት ገበያ አንጻር መታየት ቀርቶ ሊታሰብ በማይችል ኹኔታ ዝቅተኛው 0.37 ሳንቲም (በብሔረ ጽጌ)፣ ከፍተኛው ብር 70(በመርካቶ) በካሬ ሜትር ሰፋፊ ቦታዎች መከራየታቸው፣ ቤተ ክርስቲያን እንደተቋም ሳይኾን ግለሰብ ነጋዴዎች እና ጥቂት አማሳኝ የሥራ ሓላፊዎች እንዲበለጽጉበት ዕድል ሰጥቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በየአድባራቱ የታላላቅ ሕንጻዎች እና ሱቆች ባለቤት ብትኾንም ከሕጋዊ አሠራር ውጭ በውስጥ ስምምነት እና ድርድር እንዲከራዩ በመደረጉ፣ ግለሰብ ነጋዴዎች እዚኽ ግባ በማይባል ዋጋ መሐል ከተማ ላይ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እየተዋዋሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ሚሊየነር ኾነዋል፤ የራሳቸውን ካምፓኒ የከፈቱና ሱቁን በከፍተኛ ዋጋ በማከራየት ለቤተ ክርስቲያን ከብር 500 – 3500 በመክፈል ግፍ የሚፈጽሙም ሞልተዋል፡፡

ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቂት ኪራይ እየከፈሉ እነርሱ ከ75 – 85 በመቶ የሚበልጥ ዋጋ የሚያከራዩና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የፈጠሩ ነጋዴዎችም፤ ለተመደቡ አለቆች፣ ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮች እና ሒሳብ ሹሞች በመሰባሰብና ዕቁብ በመጣል በወር ለእያንዳንዳቸው ከብር 10,000 – 5,000 እንደ ደመወዝ በመክፈል የቆይታ ዘመናቸውን በማራዘም ቤተ ክርስቲያኒቱን መበዝበዛቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ይህ ኹሉ ግፍ በጠራራ ፀሐይ ሲፈጸም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ሲደረግ፣ ዘረፋና ምዝበራው ሲጧጧፍ በነበረባቸው አድባራት የሚሠሩ አለቆች÷ ምስጉን፣ ጠንካሮች፣ የልማት አርበኞች ተብለው ለስሙ ከደብሩ ካህናት እና ሠራተኞች የወር ደመወዝ ይሰበሰብና ቦታ ወይም ሱቅ ወይም ሕንጻ በቅናሽ ዋጋ በሰጡት ባለሀብት ገንዘብ በተገዛ መኪና ‹‹ካህናት እና ምእመናን ለበጎ ሥራቸውና ለልማት አርበኝነታቸው ሸልመዋቸዋል›› ተብሎ ተሸላሚዎች ይኾናሉ፡፡

በአድባራትና በገዳማት በመሬት፣ በሱቆች፣ በሕንጻዎችና በመካነ መቃብር ተያይዞም በሌሎች የገቢ ማስገኛ ተቋማት ኢ-ሕጋዊ አሠራር ሲሠራ፣ ቃለ ዐዋዲው በዐደባባይ እየተጣሰ የምዝበራ ኔትወርክ ሲዘረጋ ሀገረ ስብከቱ ምን ይሠራ ይኾን? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም፡፡ መልሱም በተቋም ደረጃ የማይገለጽ ቢኾንም የጥቅም ትስስር ኔትወርክ እና በማጣራት እና በምርመራ ጊዜ በሚፈጸም እጅ መንሻ የሚድበሰበስ መኾኑን ያለፉ ተሞክሮዎችና በጥናቱ ሒደት ወቅት ከሀገረ ስብከቱ አካባቢ ይፈጸሙ የነበሩ ተግዳሮቶች ማሳያ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአድባራቱ ቦታዎች እና ሱቆች እንደተቋም ተጠቃሚ ያልኾነችበት ዋነኛው መንሥኤ ያወጣቻቸውን ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ማክበርና ማስከበር ባለመቻሉ ነው፡፡ የጥናት ቡድኑ በተዘዋወረባቸው አድባራትና አንዳንድ ገዳማት በሓላፊነት የተቀመጡ አለቆች የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ ጠንቅቀው እንደማያውቁና እየሠሩበት እንዳልኾነ አረጋግጧል፡፡

የቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ቢከበርና የሥራ መመሪያ ኾኖ ከዚያ ውጭ የሠራ ኹሉ የሚጠየቅበት አሠራር ተዘርግቶ ቢኾን ኖሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከዘረፋና ከዘራፊዎች መታደግ በተቻለ ነበር፡፡ በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ፲፪ ቁጥር ፰ ‹‹ከዚኽ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ኾኖ በቋሚ ንብረቶችና ግምታቸው ከፍተኛ በኾኑ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ውል መዋዋል በአስፈለገ ጊዜ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድና መመሪያ እየተቀበለ ይሠራል›› ይላል – ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ጉባኤ(ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው አንቀጽ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረቷን ከብክነት ለመታደግ ያስቀመጠቻቸውን ሕጎችና መመሪያዎች የሚያከብርና የሚያስከብር መጥፋቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ከመኾኑም በላይ የቃለ ዐዋዲውን ደንብ በሚተላለፉት ላይ ተጠያቂነት ያለመኖሩ ለችግሮቹ መፈጠርና መባባስ ዐይነተኛ ምክንያት ኾኗል፡፡ ይህ ኹሉ የሕግ ጥሰት በአድባራት ደረጃ የተፈጸመ ቢኾንም የሕግ ጥሰት መካሔዱን በመከታተል ሕግ ማስከበር የሚገባው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ከድንጋጌው ውጭ ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት የሕግ ጥሰቱ አካል እንጂ የሕግ አስፈጻሚ መኾን አለመቻሉ የችግሩ ባለቤት ያደርገዋል፡፡

ስለኾነም በሕግ ጥሰቱ ምክንያት የተከሠቱ፣ ለአንድ ወገን የሚያደሉ በተለይም ለግለሰብ ነጋዴዎች ጥብቅና የሚቆሙ ውሎች ተሽረው በአዲስና ወጥ በኾኑ ውሎች እንዲተኩ ማድረግ ይገባል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በቅናሽ ዋጋ ተከራይተው ለሦስተኛ ወገን በከፍተኛ ትርፍ የሚያከራዩ ነጋዴዎችን ውል በማቋረጥ የሦስተኛ ወገን ተከራዮች ለነጋዴዎች የሚከፍሉትን ክፍያ ለቤተ ክርስቲያን እንዲከፍሉ አዲስ ውል ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር እንዲዋዋሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

Source:: haratewahido

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.