ጥሬው እስኪበስል የበሰለው ያራል – ይገረም አለሙ

 

የወያኔ አገዛዘ እንደተጠላ እንደተወገዘ ሃያ አራት አመታትን አስቆጠረ፡፡ ወደ ፊትም የሚቀጥል ይመስላል፡፡በአንጻሩ ከነገሰበት መቶ በመቶ አሸነፍኩ እስካለበት አሁን ድረስ ተቃውሞው አላባራም፤ደግሞም ለውጤት ሊበቃ ቀርቶ ጥንካሬ አይታይበትም፡፡የአንድ ወጣት ዕድሜ፡፡ ያም ሆኖ የተቃውሞው ጎራ ጩኸት አቅም ኖሮት የማይሰማበት፣ ትግሉ ጉልበት አግኝቶ ትንሽ ውጤት የማያስመዘግብበት ይባስ ብሎ የኋሊት የሚጓዝበት ምክንያት ምንድን ነው ብሎ ለመፈተሽና ችግሩን ተረድቶ መፍትሄ ለመፈለግ ዛሬም ፍላጎት አይታይም፡

ሰላማዊ አንበለው የጠብ-መንጃ ፣በሀገር ውስጥ ይሁን በውጪ የሚደረግ ትግል በየመስኩ መደጋገፍ ይሻል፤አበው ጋን በጠጠር ይደገፋል አንዲሉ ትልቅ ነኝ ብሎ ሳይኩራሩ ትንሽ ነው ብለው ሳይንቁ በተደራጀ መልኩም ይሁን በየተናጠል የሚደረግ መደጋገፍ ለትግሉ አንድ ርምጃ ማደግ ወሳኝ ነው፡፡ መደጋገፍ አልቻል ካለ ደግሞ  አለመነቃቀፍ፡ መርዳዳት ባይሳካ አለማደናቃፍ፣ እውነት ተናግሮ ትግሉን ማገዝ ቢያቅት ሀሰት አለማውራት፣ አሉባልታ አለመንዛት ምንኛ መልካም ነበር፡፡  ለዚህ ግን የታደልን አንመስልም፡፡

የወያኔን አገዛዝ የምናወግዝ ፤ድርጊቱን የምንኮንን፤ ከዚህ አልፈንም ብዙ የምንል ወገኖች እጅ ለእጅ ተያይዘን በንግግር ተግባብተን፤የጋራ መስመር ይዘን ከሥልጣን መውረድ አለበት የምንለውን ወያኔ ለማውረድ የማንታገለው ለምን ይሆን ብዬ ሳስብ ብዙ ምክንያቶች ታሰቡኝ፡፡ ከእነዚህ አንዱ በተመሳሳይ ግዜ እኩል አለመጠቀታችን፣ ነግ በእኔ ብለን የአንዱን ጥቃት የራሳችን አድርገን የሚሰማን አለመሆናችን፣ በአጭርና ባሕላዊ አገላለጽ ብስልና ጥሬ መሆናችን መስሎ ታየኝ፡፡ ይህንኑ ሀሳቤን በጽሁፍ አስፍሬ ነውም አይደልምም የሚል አስተያየት ቢሰጥበት ለችግራችን ፍለጋ አንድ ድርሻ ይኖረዋል በማለት እየከተብኩ ባለበት ሰዐት ስርጉተ ስላሴ ያስነበበችን ጽሁፍ ላይ  የሀሳቤ ተጋሪ የሆኑ መልእክቶችን አገኘሁ፡፡ ብዙዎች እንዲህ በሀሳብ ብንቀራረብ ፣የተግባባንበትን እያዳበርን የተለያየንበት ሀሳብ ላይ በጤናማ ስሜት መወያየት ብንችል  የገአዛዝ ዘመናችን ባረዘመ ነበር፡፡ እኛ የተካንነው ግን መቆራቆስና መዘላለፍ፡፡

የስርጉተ ጽሁፍ አንዲህ ይላል  …. …የዛሬ አዲሶች ከአምስት ዓምት በኋላ በሥራቸው የታሰረው ታስሮ፤ የተሰደደው – ተሰዶ፤ የበቀል መከርከሚያ የሆነው – ታጭዶ፤ የሞተው  – ሞቶ፤ የተፈታው ቤት ተፈቶ ቀሪው ነባሩ አሮጌ ይሆናል። ስለዚህ አሮጌው እኛ አይተነዋል አያዋጣም ቢል አዲሱ ደግሞ ኖ! እኔ የተሻለ አለኝ ብሎ ያው ፍልሚያውን – ይቀጥላል። ነባሮችን – ይወቅሳል። ወያኔም አጋጠመኝ ይልና አዲስ ገብ በማግኘቱ – ይፈነጫል። በዙርና በፈረቃ የሚደቃ ፈቃድ ማግኘት ሎተሪ ነው። … ስለሆነም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያዝ ለቀቅ እያደረገ አዲሱን እያባበለ መጋረጃ ጠባቂ ያደርገዋል። መጨረሻ ላይ ጉሩቦውን ተረግጦ ሚሊዮኖች ከኑሯቸው ያፈናቅላል ….. ያሻውን ደባ ማወራረጃ ያደርገዋል፤ ይህ በዙር የታየ የአምክንዮ ቁንጮ ነው።

ተለያይተን መቆማችን ትግላችንን አዳክሞት ልንነቀንው እንዳንችል ያደረገን መሆኑን፣ ማዶና ማዶ ሆነን መጮኸችን ጩኸታችንን አቅመ ቢስ አድርጎት የወዳጆቹን ምዕራባዊያን ፍቅር ሊያሳጣው እንዳልቻለ ይልቁንም ለእድሜው መርዘም እንደጠቀመው የተረዳው ወያኔ  በድርጅት ደረጃም ሆነ በግለሰብ ብስልና ጥሬ ሆነን የምንኖርበትን መንገድ ይቀይስልናል የቤት ስራ ያዘጋጅልናል፡፡ የቅርቡን አንድነትና መኢአድ ውስጥ የሆነውን ምሳሌ አድርገን ብናይ ሁለቱም ፓርቲዎች   ልዩነታቸውን በንግግር ማስታረቅ ተስኖአቸው ሲታመሱ ይህን የመጫወቻ ካርድ ያገኘው ወያኔ በረዥሙ አቅዶ በመሳሪያው ምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሚገባ ተጠቀመበት፡፡ እነርሱ ግን ሂደቱን አጢነው አዝማሚያውን ገምተው ፓርቲዎቻቸውን ለማዳን የሚያስችል ስራ መስራት አልቻሉም፡፡  ንትርካቸው እንዲቀጥል ለማድረግ ያስችላል ያለውን ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ሲሰጥ ተወሰነባቸው አርረው ሲያላዝኑ  የተወሰነላቸው ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው  ለምንና አንዴት ነው  ብለው በረዥሙ ሳያዩ የእነሱን ሥልጣን ስላረጋገጠ ብቻ በአጭር ግዜ ድል ተጋርደው  ሲፈነጥዙ አስተውለናል፡፡  ወያኔ ግን ሲያጫውታቸው ቆይቶ በትልሙ መሰረት የመጨረሻው ሰአት ላይ ሁለቱንም ፓርዎች ከጨዋታ ውጪ ያደረገ ርምጃ ወሰደ፡

በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር ተሰባስበው እንታገላለን የሚሉ ዜጎች ብስልና ጥሬ ባይሆኑ ስለ ራስ ጥቅም ማሰብ፣ስለ ስልጣን መጨነቅ በሴራ ፖለቲካ መተሳሰር ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ በረባ ባረባው እየተነታረኩ ትግሉ አንድ ርምጃ ፈቅ እንዳይል ማድረግ ሲብስም እንዲህ ፓርቲን መግደል እኩል በስሎ ብሶት የወለደው መሆን አለመቻል ነው፡፡

በግለሰብ ደረጃም ጥቂት ምሳሌዎችን ብናይ ወያኔን የሚቃወመው ብዙ ቢሆንም ብስልና ጥሬ በመሆኑ ለትግሉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡  ወያኔም ይህንኑ አንድ ስልት አድርጎ ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ ለመንግሥት ሰራተኛው ደመወዝ ጨመረና ጥሬው እንዳይበስል ቀድሞ የበሰለውም እንዳያር ለማድረግ ሞከረ፤ በቂ አይደለም የሚል ተቃውሞ ሲሰማ ደግሞ በተለይ አዲስ አበባ ላይ  ራሱም ለመዝረፍ በሚያመቸው መንገድ በመቶዎች የሚቆጠሩ አውቶብዞችን ሰርቪስ ብሎ አሰማራ፡፡  እና ጥቅሙ ይነስም ይብዛ  የዚህ ተጠቃሚ የሆነው ከሌላው ዜጋ እኩል ብሶተኛ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፤ የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሰውና በኪራይ ቤት የሚሰቃየው እኩል ወያኔን ይቃወማል ለማለትም ይቸግራል፤ የምናይ የምንሰማው ይህን አያሳምና፡፡

ሁሉም እኩል እስኪበስል ደግሞ ምጽአት ሊሆን ነው፡፡ ሥርጉተ አንዳለችው ወያኔ አዳዲስ ሰዎችንም አዳዲስ ፓርቲዎችንም እየፈጠረ በየአምስት ዓመቱ አገዛዙን በስመ ምርጫ እያደሰ ይቀጥላል፡፡ታዲያ ምን ይበጃል፤ያረረው፣ ጥሬውና ብስሉ አንድ ማእከላዊ ቦታ ላይ የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዴት እንፍጠር ፤እስቲ መላ በሉ፡፡ አበው በእንጉርጉሮ  እንዲህ ይላሉ‹፤

ችግር ችግረኛው አንድ ላይ በሆነ

አንደኛው ለአንደኛው ያዝንለት ነበረ

ብስልና ጥሬ ሆኖ ተቸገረ

ከምርጫ 2007 ውጤት መታወቅ በኋላ ( አስቀድሞ ያልታወቀ ውጤት የተገኘ ይመስል)  ከአንዳንድ ፖለቲከኞች የሚሰማው የወያኔን ትክክለኛ ማንነት የተረዱት አሁን እንደሆነ ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የምርጫ 2007 ውጠየት ከጥሬነት ወደ መብሰል አሸጋግሮአቸው መድብለ ፓርቲ አበቃለት ለሰላማዊ ታጋዮች ትልቅ የቤት ስራ ነው ሲሉ ተደምጧል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከመብሰል አልፈው ማረር ደረጃ በመድረሳቸው ሰላማዊ ትግል አበቃለት ከማለት አልፈው  ዱር ቤት ማለት መጀመራቸው እየተሰማ ነው፡፡ እንዲህ ብስልና ጥሬ እየሆን ከቀጠልን የዛሬ አምስት አመትም የመጣንበት መንገድ ይቀጥላል፡፡  አዳዲስ ጥሬዎች ይፈጠሩና አሁን ካሉት በደንብ ያልበሰሉትም ይሆኑና በስመ ምርጫ ለወያኔ አገዛዝ ቡራኬ ያሰጡታል፡፡ ይህ እንዳይሆን ያረረውም ጥሬና ብስሉም አንድ አማካይ ቦታ ተገናኝቶ መላ መፈለግ ዛሬ መጀመር አለበት፡፡ ወያኔ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል ስራውንም ሴራውንም ፣ አፈናውንም መንገድ መዝጋቱንም አራት አመት ሙሉ ሰርቶ ነው፡፡ የእኛ ስራ የእኛ ለቅሶ የእኛ ጩኸት ግን በምርጫ ዋዜማና ማግስት ብቻ፣ከዛ አራ አመት ለጥ ጸጥ፡፡ ይህም እኩል ያለመብሰላችን መገለጫ ነው፡፡ የበሰለና ያረረ እንዴት ይተኛል፡፡ ብሶት የወለደው እንደምን ይዘናጋል፡፡

ስለሆነም በኢትዮዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዐት እውን አንዲሆን የሚመኝ ሁሉ ምን ይበጃል ብሎ ለመምከር ከዛሬ የባሰ ግዜ አይኖርም፡፡  ጥሬው በራሱ ደርሶ እስኪበስል እየጠበቀ ለዚህ ፍቃደኛ አልሆን ካለ ያረረውና ብስሉ እየተጠራሩ ፣ ምን ይበጃል ብለው አንድ ላይ ይምከሩ፣ የወያኔ አገዛዝ አንዲያጥር ዘመኑ፡፡ እያላዘኑ መኖር ይብቃ፡፡

Loading...