በጃ-war ኢትዮጵያ ነዋሪዎች ባሮች ናቸው! – መስከረም አበራ

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የቆየ ቢሆንም አሁን የያዘውን መልክ የያዘው ግን ጃ-war የተባለ ራሱን ሾሞ የጨረሰ ሰውየ በአስር ጣቱ ገብቶ ማቡካት ከጀመረ በኋላ ነው፡፡አሁን የያዘው መልክ ምንድን ነው ከተባለ ሆስፒታል የገቡ የ85 አመት ሽማግሌ ከሆስፒታል አውጥቶ ደብድቦ ከመግደል እስከ ንብረት ማውደም የደረሰው የማውቀውን የሲዳማ ህዝብ ሳይሆን የጃ-war ሜንጫዊ ፖለቲካ የመሰለውን ማለቴ ነው፡፡

በሲዳማ ህዝብ መሃል ኖሬያለያለሁ፤ህዝብን እንደ ህዝብ ክፉም ደግም የማድረግ ቀልማዳነት ውስጥ መግባት ባልፈልግም ከወራት በፊት በሲዳማ ዞን የተደረገው ነገር አብሬው ከኖሩኩት የአካባቢው ህዝብ አመዛኝ ባህሪ ጋር የሚመሳሰል አይደለም፡፡በሃገር ሰላም የሚታየው የሰዎች ባህሪ ሁከት ሲነሳ ሌላ እንደሚሆንም አይጠፋኝም፡፡ ሆኖም ከዚህ ሁሉ በላይ በሲዳማ ዞን በተደረገው አስከፊ ነገር ሁሉ የ ጃ-war ጨካኝ ማንነት ጎላ ብሎ የሚታይበት ነው፡፡ሰው ተዘቅዝቆ ሲሰቀልለት እንኳን ቅጭም የማይለው ጃዋር ታዲያ በዚህ ሁሉ ውድመት ውስጥ ያለውን የእሱን ሚና ለመደበቅ “የሲዳማ ጥያቄ የእኔ አያት አንቀልባ ላይ እያሉም የነበረ ነው እንጅ እኔ የፈጠርኩት አይደለም” ሲል ያምታታል፡፡ጥያቄው ግን አንተ ፈጠርከው አልነበረም-አንተ አውሬነትህን አጋባህበት እንጅ!

የማይፀፀተው ጃ-war ታዲያ በሲዳማ ጎረምሶች መሃል ቆሞ እንደ ሙሶሎኒ በሚመስለኝ የዘወትር መወናጭፉ እየተወናጨፈ “በጉልበትም ቢሆን አላማችሁን አሳኩ” ያላቸው ወጣቶች ሰምተውት ጉልበታቸው የሚችለውን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በባለፈው ሳምንት የL-TV ቆይታው “የሲዳማ ወጣቶች በስተመጨረሻው የታክቲክ ስህተት ሰርተዋል” ሲል ሊወቅሳቸው ቃጥቶታል፡፡

የታክቲክ ስህተት የሚለው ቤተክርስቲያን ማቃጠሉን፣እሱ “ነዋሪዎች” ሲል እንደ ባሪያ የሚቆጥራቸውን ሲዳማ ያልሆኑ የሰው ልጆች ነፍስ እና ንብረት ማውደማቸውን ወዘተ ነው፡፡ለመሆኑ ያኔ በጉልበት አላማችሁን አስፈፅሙ እያለ ስሜቱ እንዳቀበለው ሲደነፋ የነበረው ወጣቶቹ ከዚህ ሌላ ምን እንዲያደርጉ አስቦ ነበር?

የስሜት ፈረሱን ጭኖ መጥቶ አዋሳ ላይ ባራገፈ ማግስት በሲዳማ ዞን የጠፋው ጥፋት ሳያንስ ዛሬ ደግሞ እነዛኑ ያስገደላቸውን መጤዎች እንደባሪያ የሚቆጥር ነገር እየተናገረ ነው፡፡ ከእኔ በላይ አዋቂ ላሳር የሚለው ጃ-war በሲዳማ ሪፈረንደም ላይ ከሲዳማ ዘር ውጭ ያሉ ሰዎች መሳተፍ የለባቸውም፣ይህን ማድረግ ህገመንግስቱን መፃረር ነው ፣ህገ-መንግስቱ የሚለው ምርጫ መምረጥ የሚችሉት ብሄር ብሄርሰቦች እና ህዝቦች እንጅ ነዋሪዎች አይደሉም ሲል እየለፈፈ ነው፡፡

የጃ-war ኢትዮጵያ ይህች ነች! እትብታቸው ከተቀበረበት መንደር ራቅ ብለው የሚኖሩ “ነዋሪዎች” የተባሉ ባሮች በህይወታቸው ላይ ተፅዕኖ በሚያደርግ ፖለቲካዊ ነገር ላይ መወሰን አይችሉም:: የሚወስኑላቸው ብሄር ብሄርሰቦች እና ህዝቦች የተባሉ ልዑላን ናቸው፡፡ ነዋሪዎች እንደ ግሪክ ዲሞክራሲ ባሮች እንደ ከብት እየበሉ እየጠጡ፣እየተኙ፣እየተነሱ ልዑላን ብሄር ብሄረሰቦች በወሰኑበት የፖለቲካ መንገድ መጓዝ ብቻ ነው፡፡የጃ-war ኢትዮጵያ ይህችን ትመስላለች!

ቃለ-መሃላ ያልፈፀመው ጠ/ሚ ጃ-war ይህንን ሲል አንድ እንዲመልስልኝ የሚፈልገው አበይት ጥያቄ አለ:: ይኽውም እስከ ዛሬ ስንት ሃገራዊ ምርጫ ሲደረግ ነዋሪዎች በሃገራዊ ምርጫ ድምፅ እንዳይሰጡ ያላሳሰበው ለምንድን ነው? እሱ አዛዥ ናዛዥ ከሆነ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው በሚቀጥለው ሃገራዊ ምርጫስ እኛ ነዋሪዎች መምረጥ እንችል ይሆን አይሆን የሚለውን በጊዜ ቢያሳውቀን ደግ ነው፡፡በህገ-መንግስቱ መምረጥ የሚችሉት ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ናቸው ከተባለ እኛ ነዋሪዎች እስከ ዛሬ ስንመርጥ የነበረው እሱን ምን አፍዝ አደንግዝ ይዞት ነው? ነዋሪዎች በሪፈረንደም እንዳይሳተፉ የሚለውን የዛሬውን የጃ-war ፅሁፍ ሳነብ ከጃ-war ኢትዮጵያ ይልቅ ነዋሪዎች እንዳይመረጡ ግን እንዲመርጡ መብት የሰጠቸው የመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የተሻለች መሆኗን ተገንዝቤያለሁ፡፡

ሪፈረንደም እና ምርጫ መንትዮች ናቸው፡፡በየአምስት አመቱ ከሚደረግ ሃገራዊ ምርጫ ይልቅ በሪፈረንደም የሚደረገው የዜጎች ውሳኔ በሕይወታቸው ላይ ቋሚ ተፅዕኖ ያለው ነው፡፡ ለምን ቢባል በ ሪፈረንደም የሚደረግ ፖለቲካዊ ውሳኔ ውጤቱ ታይቶ የመሻሻል እድሉ ዝግ ነው ማለት ይቻላል:: በሃገራዊ ምርጫ የተደረገ ውሳኔ ግን መጥፎ ውጤት ካመጣ በሚቀጥለው ምርጫ በሌላ ውሳኔ የመታረም እድል ያለው ነው፡፡ስለዚህ ዜጎች በሪፈረንደም አለመሳተፋቸው በምርጫ ካለመሳተፍ ተለይቶ መታየት የለበትም፡፡

በስተመጨረሻም ጃ-war በግዛቱ ሪፈረንደም እንዳያደርጉ የሚከለክላቸው ነዋሪዎች የሚከፍሉትን ታክስ መቀበሉንስ የሚያቆመው መቼ ነው፡፡ ወይስ እነሱ እንጅ ገንዘባቸው አይጠላም ?

2 COMMENTS

  1. ደህና ብለሽዋል አስተዋይዋ መስከረም። የዛሬው ምክር ለጦረኛው ጃ ብለሽ ካልሆነ በስተቀር የጥፋት ወንድሞቹን እነ በቀለ ገርባን መራራ ጉዲናን በግድ ትግሬ ካልሆንኩ ያለውን ጌታቸው ረዳንና እነሱ የሚፈልጉትን ጁዋር የሚናገርላቸውን ያስተሳሰብ ስንኩላንና ቀማኞች ጨምረሽ ብታስተምሪልን።

  2. This stupid woman is good for nothing. Just she tries to sell herself as an enlightened person. But she lives mentally in 18th century.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.