ከጀርመን እና አካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ካህናት፣ ሰንበት ት/ቤትና ምእመናን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ኩራት የሆኑ ስነ ጽሑፍ ከነ ፊደሉ፣ ስነ ሕንጻን ከነ ውበቱ፣ ሥነ ምግባርን ከነ ሥርዓቱ አስረክባለች። እንዲሁም ለመንፈሳዊና ለዓለማዊ አስተዳደር መመሪያ የሆኑ ፍትሕ መንፈሳዊ ፍትሕ ሥጋዊን በየመልኩ ቀምራ ለሀገር አበርክታለች። በዚህም እየተመሩ ኢትዮጵያዊያን መሪዎች ሕዝባቸውን በሥርዓት በመምራታቸው ምክንያት ከሩቅ ነገሥታት እና መሪዎች ሳይቀር ኢትዮጵያዊያን ፍርድ አዋቂዎች፣ እንግዳ ተቀባዮችና ለተገፉ አዛኞች መሆናቸው በታሪክ መዛግብት ተመዝግቦ ይገኛል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የመጀመሪያዎቹ የእስልምና ተከታዮች በችግራቸው ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መላካቸው የሚጠቀስ ነው።

ዛሬ-ዛሬ ግን ይህን ፍርድ ያስተማረችና ሀገራችን በበጎ እንድትመሰገን ያደረገች የፍትሕ ምንጭ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ፍትሕ በማጣት አብያተ ክርስቲያኖቿ በጠራራ ፀሐይ ይቃጠላሉ፤ ካህናቶቿና ምእመናኖቿ በአደባባይ ይታረዳሉ፤ የመስቀል እና ባሕረ ጥምቀትን የምታከብርባቸው ይዞታዎቿ ይነጠቃሉ። አባላቶቿ በያሉበት ይሳደዳሉ፣ ከመንግሥታዊም ሆነ ከሌሎች ተቋማት በስልት ይገለላሉ። ቤተ ክርስቲያን ይህንንም ሁሉ ግፍና መከራ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል በሚል ተስፋ ሃይማኖታዊ መርኆዋ በሆነው ትእግስት ተሸክማ ቆይታለች። ሆኖም ግን ይህን ሁሉ ትእግስት ብታደርግም ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ ሄዶ ሰሞኑን ደግሞ መዋቅራዊ አንድነቷን ለማፈራረስ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናቋቁማለን” በሚሉ ወገኖች ሰበብ ታላቅ ደባ እየተፈጸመባት ይገኛል።

ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ሁሉ ግፍ እንዲያስቆምና በአጥፊዎችም ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ደጋግማ ብታሳስብም በመንግሥት በኩል ግን ሁኔታውን እንደሚከታተልና እንደሚያጣራ በቃል ከመግለጽ ባለፈ እስከ ዛሬ ድረስ ቃሉን ጠብቆ አጥፊውን ለፍርድ ሲያቀርብና በአጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ ተግባራዊ እርምጃ ሲወስድ አልታየም። ይህ ዓይነቱ የመንግሥት ዝምታ ደግሞ አጥፊዎቹን “አበጃችሁ!” ብሎ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያጠፉ ፈቃድ ከመስጠት የተለየ ሆኖ የሚታይ አይደለም።

መንግሥት ይህንን ዓይነት ተግባራዊነት የሌለው የቃላት መግለጫውን በማለፍና ዝምታውን በመስበር በጽንፈኞችና በሕገ ወጦች ከወዲሁ ተግባራዊ እርምጃ ካልወሰደ በስተቀር በዚህ አያያዝ እነዚህ ጽንፈኞች እና ሕገ ወጦች አድገው እና የመንግሥትነት ኃይል ጨብጠው ፋሺስት ኢጣሊያ በቤተ ክርስቲያናችንና በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን እልቂት አይደግሙም ብሎ ማሰብ አይቻልም።

በመሆኑም እኛ በጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት በጀርመን፣ ሆላንድ፣ ስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያ የምንገኝ የአብያተ ክርስቲያናት የካህናት፣ ዲያቆናት እና የምእመናን ተወካዮች የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

ሀ. ለኢትዮጵያ መንግሥት

1. መንግሥት እስካሁን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ጥፋት እያደረሱ ያሉትን የጥፋት አካላት ለይቶ እንዲያወጣ እና በእነዚህ አካላት ላይ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
2. መንግሥት በጽንፈኞች የተቃጠሉ እና የወደሙ አብያተ ክርስቲያናት መልሰው እንዲቋቋሙ ድጋፍ እንዲያደርግ እና ለወደፊቱም ይህ ዓይነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ላሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያኖች የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ፤
3. የቤተ ክርስቲያናችንን ሲኖዶሳዊና መዋቅራዊ አንድነት የሚያፈርስ አደገኛ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት መጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ፣
መንግሥት ከላይ አቋም የወሰድንባቸውን ጉዳዮች በአስቸኳይ እንዲያስፈጽም እየጠየቅን ይህ ባይሆን ግን የቤተ ክርስቲያናችንና የተከታዮቿ ሕጋዊ መብትና ደህንነት እስኪረጋገጥ ድረስ በምንደርሳቸው ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሁሉ ተቃውሟችንን ማሰማት የምንቀጥል መሆናችንን ለማስገንዘብ እንወዳለን።

ለ. “የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እናቋቁማለን” ለሚሉ አካላት

ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሰማነው “የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እንቋቁማለን” በሚል ሰበብ እየተደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴዎች መታዘብ ችለናል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ቋንቋዎች ማስተማርን እንደትሩፋት ሥራ የምታየው ሳይሆን የተላከችበትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ እንደሚያግዛት እንደ ዐይነተኛ መሣሪያ፤ ብሎም እንደ መልካም ዕድል የምትቆጥረው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል በቋንቋ ስታስተምር ኖራለች፤ በማስተማር ላይ ትገኛለች፤ ወደፊትም የምትቀጥል ይሆናል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በበቂ ሁኔታ ባይሆንም በአፋን ኦሮሞም ስታስተምር ቆይታለች። አሁንም በማስተማር ላይ ትገኛለች። ይህንን ጥረቷን በማስፋትም ከዚሁ ማኅበረ ሰብእ አብራክ የተከፈሉና ወንበር ተክለው፣ ጉባኤ ዘርግተው ሊቃውንትን ሲያፈሩ እንደነበሩት የቅኔና መጻሕፍት መምህር አለቃ ገብረሥላሴ ክንፉ፣ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ፣ ዝነኛው የቅኔና መጻሕፍት መምህር መምህር ጥበቡ ገሜ፣ ሰማእተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ አቡነ ጴጥሮስና ሌሎችም መምህራንን ስታፈራ ቆይታለች።

ዛሬም ማኅፀነ ለምለም ቤተ ክርስቲያናችን የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዳሏት የሚታወቅ ነው። በተጨማሪም ኦሮምኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች የሚሰጠው አገልግሎት ማእከላዊነትን በጠበቀ መልኩ መሠራት ያለባቸው ተግባራት በርካታ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም የጸሎታት ሁሉ መክብብ የሆነው ጸሎተ ቅዳሴን በኦሮምኛ ቋንቋ መቀደስ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ማኅበራት እና ግለሰቦች ትግሃት በርካታ መጻሕፍት፣ መጽሔት፣ በድረ ገጽ የሚለቀቁ ትምህርታዊ ጽሑፎች፣ መዝሙራት፣ ቴሌቪዠን ዝግጅት …ወዘተ እንደ ቀላል የማይታዩ እንደ መሆናቸው መጠን ምንም እንዳልተከናወነ መቁጠር ለአገልግሎቱ ከመቅናት በዘለለ ሌላ ፍላጎት ለመኖሩ ጥርጣሬ አሳድሮብናል፡፡
ስለዚህ

1. ክልላዊ ቤተ ክህነት እንዲቋቋም በማለት ጥያቄአቸውን ያቀረቡት ወገኖቻችን ከአሁን ቀደም ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄአቸውን በአግባቡ ማቅረባቸው ተገቢ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በመጠበቅ ፋንታ በራሳቸው መንገድ ሄደው ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጪ ማኅተም ማስቀረጻቸው እና የቤተ ክርስቲያናችን ኃላፊዎችን ትእዛዝ ተላልፈው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫዎችን መስጠታቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ይህንን ተግባራቸውን አጥብቀን እንቃወመዋለን፡፡

2. እነዚህ ወገኖች ቤተ ክርስቲያናችንን ባመኑትና ባለመኑት ሰዎች ፊት ሲነቅፉአት ስንመለከት ለየትኛዋ ቤተ ክርስቲያን እየተቆረቆሩ እንደነበር ጥያቄን አጭሮብናል፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲናችንን በአደባባይ ነቅፈው ለሚነቅፉት አሳልፈው መስጠታቸውን እንዲያቆሙ እንጠይቃለን።

3. በኦሮሚያ ክልል ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንም በተለይም መንፈሳውያን ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከመጠበቅ አንጻር በሓላፊነት ስሜት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበር ቅሬታም ሲኖር በልጅነት መዓርግ ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያንን አካል በማቅረብ የመፍትሔ አካል መሆን አንዲችሉ እንጠይቃቸዋለን፡፡

ሐ. ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት

1. ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችንን ወቅታዊ ፈተናዎች በሚመለከት ሰፊ ጊዜ ወስዶ መወያየቱን፣ አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ መጥራቱን እንዲሁም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን እና ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣናትን ማነጋገሩን በአድናቆት እንመለከተዋለን፡፡
2. በዛሬው ዕለትም (ጳጉሜን ፪ ቀን ፳፻፲፩ ዓ. ም.) ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣውን መግለጫ ሙሉ በሙሉ የምንደግፈው እና ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን የምንወጣ መሆኑን እየገለጽን በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት ቀርበው በአቋማቸው እንደሚጸኑ በገለጹትና እንዲሁም ወደ ሲኖዶሱ ባልቀረቡት ግለሰቦች ላይ ብዙ ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት አፋጣኝ ሲኖዶሳዊ ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው እንጠይቃለን።
3. ቤተ ክርስቲያናችን እያጋጠሟት ያሉትን በህልውናዋ ላይ የተቃጡትን ውጫዊ ፈተናዎች ለመቋቋም እና ውስጣዊ ችግሮችን በጊዜ እና በበቂ ሁኔታ ለመፍታት እንድትችል ቅዱስ ሲኖዶስ “የመሪ ዕቅድ አመራር እና ትግበራ ዐቢይ ኮሚቴ” እንዲቋቋም መወሰኑን በአድናቆት እንመለከተዋለን። አሁንም ኮሚቴው በሰው ኃይል ተጠናክሮ በከፍተኛ ፍጥነት ሥራውን አጠናቅቆ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ እንዲችል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡት እንጠይቃለን።
4. በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ማእከላዊነትን በጠበቀ መልኩ እየተጠኑ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየጠየቅን ወደ ፊት ሀገረ ስብከታችን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበር እንደዚህ ያሉ ሐዋርያዊ ሥራዎች እንዲከናወኑና ዘለቄታነት ያላቸው ሥራዎች መሠራት እንዲችሉ በተቻለን ሁሉ ድጋፍ ለማስተባበር ቃል እንገባለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ።

ፍራንክፈርት፣ ጀርመን

ጳጉሜን ፪ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. | 07.09.2019

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

2 COMMENTS

 1. Golden rule from the Bible: “In everything, therefore, treat people the same way you want them to treat you, for this is the Law and the Prophets.”

  The main source of racism, discrimination, economic and political corruption in Ethiopia is the Ethiopian orthodox churches. Since the era of Menilik it is the right hand of the government. It is and was used as tools, in orderto to discriminate other languages and cultures. One thirds of the Oromo land were controlled by such evil doers. All wickedness in the Ethiopian politics spring from the Ethiopian orthodox churches all the times till now. Everyone is aware of its wickedness. Now it is better, if you stop your malicious tactics and empty crying. It will not help you anymore. You have been imposing the Amaharic language and the Amahara culture on other peoples in Ethiopia. The Ethiopian orthodox churches controlled one third of the Oromia and the the Sutherland during Menlik and Haile Seilase. The churches clergy used to behave as lords over the peoples, but not as servants of the Almighty God.

  Now they make delibretly noises. But no more disgusting and discriminating others (especially the Oromo) in the name of christianity and the almighty God. Now it is better, if you stop your malicious tactics and empty crying. Cheap propoganda is not helpful for you and for the orthodox churches. No power on earth will stop the Oromo people from fulfilling its aspirations as a freedom loving nation to regain its human dignity and rights. It is up to you to respect this great nation for the sake of your own benefits.

 2. Revelation 7:9 New International Version (NIV)
  After this I looked, and there before me was a great multitude that no one could count, from every nation, tribe, people and language, standing before the throne and before the Lamb.evelation 2-3 New International Version
  <>
  2 1 “To the church in Ephesus,Tharsis,Ephesians ,etc
  The bible Christians use and guided knows a church by location not by race like the so called Oromo Church dividers are doing.This demonic vision of dividing faith community initiated by the jihadist J war who was once threatened to behead christians and later supported by Bekele Garba who even preached to break marriage with other races shame on you.Worshiping Almighty God by any human langage is not a sin but the motive of these ethnic divisive politicians is to dismantle the ancient Ethiopian church body as a tool to dismantle the nation and the continent of Africa.There is no ethnic church in the planet and our Kenyan and Nigerian brothers laugh on us when they hear Oromo church as there is none Kukyu and Klangeni church in kenya and there in none Uruba or Ebbo church in Nigeria.Thi is the latest scheme of the ayatollah evil J war through his puppets we are seeing them to give press statement violating the heavenly and earthly rule that the Synod is the right institution for any legal names and proceeding and the book of acts gives instructions for christians to be accountable for the respective synod or church body(Acts 20;17)
  Pastor Degone Moretew

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.