የንጹሃን ሕይወት ከጠፋ በሁዋላ ኮማንድ ፖስት ለማን ነው!? (ህብር ራዲኦ)

በደቡብ ክልል የጸጥታውን ሁኔታ ለማረጋጋት በሚል ኮማንድ ፖስት ታውጇል።የዚህ አዋጅ መዘግየት ብዙ ዋጋ አስከፍሉዋል ።የደረሰው ጥፋት በዚህ አዋጅ አለመታወጅ ከሆነ ተጠያቂው ንጹሃንን በብሄር ማንነታቸው የገደሉ፣ያፈናቀሉ፣ንብረት የዘረፉ እና ያፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን ይህ እንዳይሆን አስቀድሞ የመከላከል እርምጃ መውሰድ የነበረበት የክልል እና የፌደራል አመራር ጭምር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረጅም ጊዜ የቆየውን በምስጢር ሳይሆን በአደባባይ ሲካሄድ የቆየውን የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ቀነ ገደብ ሲቀመጥ እስከ ሰኔ 24 ለምን ዘገዩ? 
ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔ ቀነ ገደብ እንዲያሳውቅ በተደጋጋሚ ሲለመን ለምን ዋዜማው ድረስ ለወራት በዝምታ ቆይቶ ሐምሌ 10 በአምስት ወራት ውስጥ በየደረጃው ሂደቱን አስፈጽማለሁ አለ?

አንዳንድ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን እና የአብይ አህመድ የቀኝ እጆች ሳይቀር ህገ መንግስቱን አልተከተለም ብለው የሚኮንኑትን የጥያቄ አካሄድ በግልጽ ሲደግፉት ለምን ቆዩ? የመንግስት ስልጣን የያዘው አካልስ ይህ ሲሆን የት ሄዶ ነበር!?

የሰው ሕይወት እስኪጠፋ፣ንብረት እስኪወድም የሐምሌ 11 ዋዜማ ሁሉም ወገኖች ስጋት አለ ሲሉ ቆይተው ዛሬ ከ30 በላይ ንጹሃን ከሞቱ በሁዋላ ለሕዝብ ተቆርቁዋሪ መስሎ የሚቀርበው ሀይል ምን ሲሰራ ነበር?

የደህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በድርጅቱ ሊቀመንበር ሙፈሪያት ካሚል ቢሮ አዲስ አበባ ላይ ለሁለት ቀናት አደርገዋለሁ ያለውን ስብሰባ በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ውስጥ ሆኖ ከሳምንት በላይ ፈጅቴበታል። ይህን ስብሰባ በውጥረት ሲያኪያሂድ መንግስት ቢያንስ ሐምሌ 11ን ተከትሎ ግጭት ሊነሳ፣የሰው ሕይወት ሊጠፋ እንደሚችል መረጃ አልነበረውም?

የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ከጥያቄው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች ብሄር ለይቶ ንብረት ማጥፋት፣በአስነዋሪ ሁኔታ ጭምር ሕይወታቸውን ማጥፋት ፣አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል ሲደረግ ዛሬ ኮማንድ ፖስት አውጃለሁ የሚለው ሀይል የት ነበር?

የደረሰው ጥፋት ተጠያቂው ችግሩን እያወቀ የንጹሃን ሕይወት እንዲጠፋ ያደረገው አመራር ጭምር ሳይሆን ከሁዋላ እና ከፊት ኤጄቶን በል በል ሲሉ የነበሩ ሁሉ በዚህ ጥፋት ሚናቸው ምንድነው?

የኮማንድ ፖስቱን ማወጅ ጥፋት እስኪደርስ ከዘገዩ በሁዋላ መሆን ከተጠያቂነት አያድንም። በደቡብ ክልል የደረሰው ጥፋት ከፌደራል መንግስቱ ሆነ ከክልሉ ባለስልጣናት ጀምሮ ጥፋቱን ከፊት እና ከሁዋላ ሆነው ያቀነባበሩ ሀይሎች ሚና በገለልተኛ አካል ሊጣራ ይገባል። ይህ ካልሆነ ዜጎች ላይ ሽብር እስኪፈጸም ቆመው ሲያዩ የነበሩ ባለስልጣናት እነሱ የሚፈልጉት ካልሆነ ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላም እና እውነተኛ መረጋጋት በኮማንድ ፖስት ከዚህ ቀደም ሲመጣ አልተስተዋለም።

ዛሬም ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ ሰላም የሚያመጣው እርምጃ አገር ለመምራት ብቃት የሌለውን ኢህአዴግ የአገሪቱን የፖለቲካ ችግር በሚፈታ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል።

በሕግ ማዕቀፍ የተወሰን ሀላፊነት የሚሰጠው፣የዴሞክራሲ ተቁዋማትን የሚገነባ፣ወደ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሻግር ስርዓት ለማቆም እውነተኛ ሁሉንም ወገኖች የሚወክል የሽግግር መንግስት ማቁዋቁዋም እንጂ በግልገል አምባገነኖችም ሆነ ንጹሃን ከሞቱ በሁዋላ ለይስሙላ በሚቁዋቁዋም ኮማንድ ፖስት የአገሪቱን ችግር መፍታት እንደማይቻል ደጋግሞ መናገር ይገባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.