የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ‹‹ፍትሕ ካልተሰጠኝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ማንኛውም ውድድር አልሳተፍም›› አለ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ረጅም ዓመታትን የዘለቀው እና በታሪክ በርካታ ክብሮችን የያዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘገጃቸው ውድድሮች ላለመሳተፍ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ታኅሳስ 1928 ዓ.ም የተመሠረተው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በብዛት በስኬት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በችግሮች ውስጥ ዘመናትን ተሻግሮ ከ80 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ቡድኑ በ83 ዓመታት ጉዞው በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ላይ ትልቅ ስም ያላቸው ታላቁ የስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማን እና መንግሥቱ ወርቁን ጨምሮ በርክት ያሉ ተጫዋቾችን አፍርቷል፡፡

በቅርቡ ሳልሀዲን ሰይድ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ደጉ ደበበ፣ አዳነ ግርማ እና ሌሎች ተጫዋቾችም በቡድኑ ታሪክ ውስጥ ያለፉም ታሪክ የሠሩም ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በስፖርቱ ዘርፍ ለኢትዮጵያ በርካታ አስታዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ስፖርት አፍቃሪያንን በማሰባሰብ እና ወደ አንድነት በማምጣትም የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ የቆየ ቡድን ነው፡፡

በዚህ ወቅትም በኢትዮጵያ ፕርሚዬር ሊግ ከሚሳተፉ ቡድኖች መካከል በስኬትም ሆነ ረጅም ዓመት በመዝለቅ የሚስተካከለው የለም፡፡ በአዲስ አበባ ወጣቶች በተለይም በአራዳ አካባቢ ልጆች የተመሠረተው ይህ ታላቅ ቡድን እንደ ቡድን ሲመሠረት ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆኑለትም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሠረተበት ዓመት ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን በመውረሩ በሚፈለገው ልክ እግርኳሳዊ ክንውኖችን ማስሄድ አልቻለም ነበር፡፡

በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ስሙ ሳይቀር ባለመወደዱ ‹‹ቪቶሪዮ ውቤ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እንደነበርም ታሪክ ይናገራል፡፡ ስሙን ከመቀየርም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉ የእግር ኳስ ቡድኖች ጋር እንዳይጫወትም ማዕቀብ ተጥሎበት ነበር፡፡ ፈረሰኞቹ በለጋ ዕድሜ በነበሩበት ጊዜ አሁን ላይ በትልቅ ደረጃ የሌሉ የቀበና ናዳ፣ ጉለሌ፣ ስድስት ኪሎ፣ እንጦጦ እና ሌሎች ቡድኖች ነበሩ፡፡

አምስት ዓመቱን በመከራ ያሳለፉት ፈረሰኞቹ ከ1933 ዓ.ም ቡድኑን ከማጠናከርም አልፈው ከውጭ ሀገር ቡድኖች ጋርም መጫወት ችለዋል፡፡ በ1935 ዓ.ም ‹‹ፎርቲቲ›› የተባለውን የጣሊያን ቡድን በመግጠም በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው ለጣልያናውያን ዳግም ሽንፈት አቅመሰዋቸዋል፡፡

ይህ ታላቅ ቡድን ከበርካታ ዓመታት በኋላ በዘመነ ደርግ በ1970ዎቹ የመፍረስ አደጋ አጋጥሞት ነበር፡፡ ስያሜው በነበረው ስርዓት ባለመወደዱ ‹‹ አዲስ ቢራ ክለብ›› እንዲባል ተጽዕኖ ተፈጥሮበት ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን የኢትዮጵያ ፕርሜር ሊግ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ 14 ጊዜ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ተወዳደሪ የለውም፡፡

ፈረሰኞቹ በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ነጥብ በመሰብሰብ ባለታሪክ ናቸው፡፡ በአንድ የውድድር ዘመን በተቃራኒ ቡድን ላይ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር፣ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፉ ዋንጫ በማንሳት፣ በሊጉ አምስት ጨዋታዎች እየቀሩት ዋንጫ በማንሳት፣ በአንድ የውድድር ዘመን ከተከታዩ በ24 ነጥብ በመብለጥ ዋንጫ በማንሳት እና ሌሎች በርከት ያሉ ክብረ ወሰኖች ባለቤትም ነው፡፡

ይህ ታላቅ ቡድን በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ‹ተገፍቻለሁ› ሲል ራሱን ከውድደር እንደሚያገልል በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ የቡድኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አየነው አዲስ ስለጉዳዩ ለአብመድ በስልክ እንደገለጹት “በ28ኛ ሳምንት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር በሜዳችን ልናደርገው የነበረውን ጨዋታ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር በመከልከላችን እና በ29ኛ ሳምንት ጎንደር ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር ልናደርገው የነበረው ጨዋታ በፎርፌ በመነጠቃችን ‹ቡድናችን ላይ ኢ-ፍትሐዊ አሠራር አለ› ብለን ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ አቅርበናል፡፡ ፍትሕ እስኪሰጠን ድረስ ፌደሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው የትኛውም ዓይነት ጨዋታ ላለመሳተፍም ወስነናል” ብለዋል፡፡

“በ28ኛ ሳምንት ከወልዋሎ ጋር ልናደርገው የነበረውን ጨዋታ ቡድናችን ዕውቅና ሳይኖረው አዳማ ሄደን እንድንጫወት ካለበለዚያ በዝግ ስታዲዮም አዲስ አበባ ላይ እንድንጫወት ተወስኗል” ያሉት አቶ አየነው ያለዕቅድ ሌላ ቦታ መሄድ ለአላስፈላጊ ወጪ እንደዳረጋቸዉ፣ ከደጋፊ የሚሰበስበውን ገንዘብ ያላገናዘበ እንደሆነና ውሳኔው ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው “በ29ኛ ሳምንት ጎንደር ላይ ልንጫዎት ልንሄድ ስንዘጋጅ ፌዴሬሽኑ ቀኑን በመቀየሩ ሳንሄድ ቀርተናል፡፡ ለፋሲል የተሰጠው ፎርፌም አግባብ አይደለም ” ብለዋል፡፡ ፌደሬሽኑ በሚሰጣቸው “አግባብነት የሌላቸው” ባሉአቸዉ ውሳኔዎች የተጫዋቾች እና የደጋፊዎች ሥነ ልቦና እንደተጎዳና ፌደሬሽኑ ፍትሕ ካልሰጣቸው እስከ ዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ድረስ ቅሬታቸውን ይዘው እንደሚቀርቡም አቶ አየነው ተናግረዋል፡፡
አቶ አየነው “ያለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርቱ አይደምቅም እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድኖች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ሲሉ በፌደሬሽኑ ያለውን ኢ-ፍትሐዊ አሠራር ለማስቆም መረባረብ አለባቸው” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ቡድን በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም እና በፌደሬሽኑ አሠራር ደስተኛ እንዳልሆነና ይህንንም በግልጽ እንዳሳወቀም አቶ አየነው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፐሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ላይ የተወሰነው ውሳኔ በሕግ እና በመመሪያው መሠረት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ የተለየ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጎድቶ ሌሎችን ለመጥቀም የተሠራ የሕግ አግባብ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ታሪክ ያለው እንደመሆኑ መጠን ውሳኔውን ቀይሮ ወደ ውድድር እንዲመለስ ከቡድኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ምክክር እንደሚያደርጉም ኮሎኔል አወል ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ በፌደሬሽኑ ውስጥ አሉ ብሎ ያነሳቸውን ክፍተቶችም ለማዬት ዝግጁ እንደሆኑ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታዎች የነበሩ ክንውኖችን የሊግ ኮሚቴው ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳርፍም ገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በ28ኛ ሳምንት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ሊደረግ ቀጠሮ እንደተያዘለትም ኮሎኔል አወል ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ኮሎኔሉ ይህን ይበሉ እንጂ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በተጠናቀቀ የሊግ ጨዋታ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደማያደርግ አስታውቋል፡፡ በብዙ ውዝገብ ታጅቦ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ፍጻሜውን ያገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስን ስድስት ነጥብ በፎርፌ አሳጥቷል፡፡ ከፕርሚዬር ሊጉ የወረደው ደደቢት እና ጅማ አባጅፋርም አንዳንድ ጨዋታዎችን በፎርፌ የተነጠቁ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ወላይታ ዲቻዎች በአንጻሩ ዘጠኝ ነጥብ እና ዘጠኝ ንጹህ ግብ በፎርፌ በመሰብሰብ የውድድር ዓመቱን አጠናቅቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ/ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 2/2011 ዓ.ም (አብመድ)

2 COMMENTS

  1. The problem with Ethiopia’s premier league is that of the 16 teams 4 are from Tigray region. The Federation allocates 25 % of fund to Tigray. That is not fair and should be corrected immediately. Secondly, teams that allow disturbances on home turf should be severely penalized and if need be ejected from league.

  2. እሳካሁንም የተባለው ተቋም፣ በወራሪ ወያኔና ፣ በመናጆዎቻቸው ስለሚመራ፣ ቅዱስ ጊኦርጊስን የመሰለ ፣ ያዲስ አበባ ተወላጅና ያገሪቱ አኩሪ ቡድን፣ የማጥፋት ተልእኮ ነው ድርጊቱ።
    አምስት ሚሊዎን ህዝብ ያለበት ትግራይ፣ የሚመደብለት ቡጀት ፣ የሃያምስት ሚሊየን ህዝብ ሊወክል ለሚገቡ ቡድበየታውም ዘርፍ ኢትዮጵያን ለማውደም ከሚደረግ ድርጊ፣ የተለየ ጎአደለም። ስለዚህ ጎበዝ ፣ ተወረናል ። ሃቁ ይኽ ነው። የቅዱስ ጊዎርጊስ የግር ኳስ ቡድን ፍዳ፣ አንዱ የዚህ ወረራ፣ ታርክ ማውደምያ አካል ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.