ዛሬው የደሴ የመንጋዎች የጅምላ ፍርድ መወገዝ ይኖርበታል

ፍትሕ ለተጎዱት አሁኑኑ!

የጎጥና የጎሣ ፓለቲካ ያጠፋናል ስንላቸው “መዳኛችን ነው” ይሉናል:: ኢትዮጵያዊነት ይመጥነናል ስንል “ኢትዮጵያ ለዚህ አብቅታናለች:: ገደል ትግባ” ብለውናል::

የጎጥና የጎሣ ፓለቲካ በአርተፊሻል መንገድ ማለትም በእትኖጂነሲስ በውጭ ሃይሎች የተሰራ ነው:: የዛሬው አማራ የነገ የጎንደር፤ ሸዋ፤ ወሎና ጎጃም፤ የዛሬው ኦሮሚያ የነገ ባሌ፤ አርሲ፤ ሐረር፤ ወለጋና ባሌ የክፍፍል ጥንስስ ወይም በጊዜ ስሌት የሚፈነዳ ቦንብ ነው ስንላቸው ሊሰድቡን ሞክረዋል::

የዛሬው በደሴ- ወሎ የተፈፀመው ድብደባ ምስክር ሆኖ ከኛ ሃሳብ ጎን ቆሟል:: የጎሣ ፓለቲካና ጎጣዊ አደረጃጀት የዴሞክራሲ ፀር መሆኑን በራሱ የጋጠ ወጦች ዱላ አረጋግጧል:: ጥያቄው ተሰብሳቢዎቹ የሚያራምዱት መስመር ላይ አይደለም:: የሃሳብ ነፃነት በሰላማዊ መንገድ እስከተገለፀ ድረስ ይህን ነፃነት በዱላ ለማምከን መነሳት በተፈጥሯዊ፣ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የተቃጣ የመንጋዎች የጅምላ ፍርድ ነው:: ሊወገዝም ይገባዋል::

“በክልልላችን አትገቡም” የሚል የጎጠኞች እብሪት ከክልላቸው ውጭ በሚኖረው ሚሊዮኖች ሕዝብ ላይ የደህንነ ት ሥጋትም ነው:: እነኝህ መንጋዎችና የጎጥ ባላባቶች የተገበሩት እርምጃ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የሐገሪቱ ክፍሎች የመዘዋወርና የመኖር መብትን የሚጋፋ ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያን መበተን ለማምጣት ኢትዮጵያውያንን ያላቸውን የግል አመለካከትንና የሃሳብ ነፃነትን በመዋጋት የኢትዮጵያን መበተን ከሚሰሩ ሃይሎች ጋር የዓላማ አንድነት እንዳላቸው ብቁ ማስረጃ ነው::

ትላንት “የነጃዋር ደጋፊዎችና ኦነጋውያንን ዱላ ይዘው እንዴት ሠልፍ ይወጣሉ?” እያሉ ሲተቹ የነበሩ ጎጠኞች ዛሬ እራሳቸው በዱላ የገዛ ወገናቸውን ሲፈነክቱ ማየት እጅግ ያሳዝናል:: ያሳፍራል:: ኦነግ ሲይዘው የሚወገዝ እናንተ ደም ስታፈሱበት የሚወደስ የጎጠኛ ዱላ የለም:: ዱላ ያው ዱላ ጎጠኛም ያው ጎጠኛ ነው::

መታወቅ ያለበት ይህ የጎጠኞቹ መንገድ የገደል መንገድና ጭፍን ጀብደኞች ሕዝብ በሰላም የሚኖርበትን ቀጠና የሁከትና የብጥብጥ በማድረግ የጥፋት ድግስ እየከወኑ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል:: “የአማራውን የህልውና ጥቃት (“existential threat”) ለማስጠበቅ በአማሮች ውስጥ ያለውን የሃሳብ ልዩነት በዱላ ማስተናገድ አይደለም:: ዱላ አካልን እንጂ ሃሳብን አይበሣም:: ፒየርስ ብራውን <<የሠው ልጅ በባርንት እንዲኖር ባስገደደው ኢ-ፍትሐዊነት ነፃ መውጣት አይችልም>> ይላል:: ይልቁንም “የህልውና ጥቃትን” እንመክታለን የሚሉን ባለ መላምቶች እራሣቸው ለአማራው መከፈል እየሰሩ የህልውናው ጥቃትና አደጋ እየሆኑ መምጣታቸው ነው::

ይህን የዛሬውን የደሴ እኩይ ምግባርና ተግባር የማያወግዝ ዜጋ ስለኢትዮጵያዊነት: ስለኦነግም ይሁን ስለወያኔ እንዲነግረኝ አልፈቅድም:: ለአንድ ዓይነት ክብደት የተለያየ ሚዛን (double standard) መጠቀም ግብዝነትና አድርባይነት ነው:: ‘ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ እበድሪኝ’ የብልጥ ብልሃት ሣይሆን የጅል ወይም ቂል (fool wit) ተረት ነው::

ሕግና የሕግ የበላይነት እየሟሸሸ በመጣበት ሐገር ሕገወጥነት ሕግ ይሆናል። ይህም ሥርዐተ – ዓልበኝነት ነው!!

ዱላውም ያው ዱላ፣ ጎጠኛውም ያው ጎጠኛ ነው!

ትላንት “የነጃዋር ደጋፊዎችና ኦነጋውያንን ዱላ ይዘው እንዴት ሠልፍ ይወጣሉ?” እያሉ ሲተቹ የነበሩ ጎጠኞች ዛሬ እራሣቸው ደሴ ላይ በሙቅ ውሐ በራሰ ዱላ የገዛ ወገናቸውን ሲፈነክቱ ማየት እጅግ ያሣዝናል:: ያሣፍራል:: የጎጠኞች እናት አንድ ናት የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም።

ኦነግ ሲይዘው የሚወገዝበት፣ እናንተ ደም ስታፈሱበት የምትወደሱበት የጎጠኛ ዱላ የለም:: ዱላውም ያው ዱላ፣ ጎጠኛም ያው ጎጠኛ ነው:: የጅምላ ፍርድ ያው የጅምላ ፍርድ ነው። ‘ከበሮ በሠው እጅ ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር’ ይባል የለ!

ጎጠኝነት መውረድ ብቻ ሣይሆን ወደ እንሠሣዊ ባህርይ መለወጥ ነው!
=======

ይህን ጠቅሰን ነበር!!

‘ጎሣዊ ኢፍትሃዊነት (Tribal Injustice)!’

1. <<ይህ ሌባ የሌላ ጎሣ አባል ነው:: በክሱ ጭብጥና ቅጣት መሠረት ወንጀለኛ ነውና ይገደል::>>

****
2. <<ይህ ሌባ የኛ ጎሣ አባል ነው:: በክሱ ጭብጥና ቅጣት መሠረት ወንጀለኛ ይመስላል:: ነገር ግን የኛ ሌባ ስለሆነ በነፃ ይሂድ::>> (ኢብነዘር አኪንሪኔድ)

1 COMMENT

  1. በወሎ የተካሄደው ግጭት አላስፈላጊ ነው:: ሆኖም አማራውን የበለጠ ሸንሽኖ ለማዳከም የወሎ :የጎጃም : ጎንደር እያለ ወያኔ ቢያደራጃቸው አይገርመኝም:: 27 አመታት የተረገጠው በአማራነቱ ብቻ ነው:: ይህን የማያውቅ ደደብ አማራ በየጎጣጎጡ የለም ብሎ መገመት አይቻልም:: የግንቦት 7 አጫፋሪዎች ከዚህ ክፍፍል የሚገኝ ምንም ትርፍ አይኖርም:: አማራ ተመልሶ ላለመተኛት ተንስቷል:: የማንንም ሞግዚት አስተዳዳሪ አይፈልግም:: አማራ ታላቅ ህዝብ ነው:: በጎጥና በጎሳ ሳስቶ እራሱን አይመለከትም::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.