ህወሃት ይቀየራል ብለን የቀበሮዋን ታሪክ አንድገመው (አሰፋ በድሉ)

የህወሃት ፋይል ስላልተዘጋ፤ ትግሉም እንደገና ጥሬ እየሆነ ስለመጣ አሁንም ስለ ህወሃት እንጽፋለን፡፡ጽሁፋችን ደግሞ ጉልበት እንዳለው ልብ የሚል ልብ ይለዋል፡፡ አንድ አፍቃሪ ኦነግ ወዳጄ ሁሌ እንደሚለኝ ጽሁፍ ሲጥል እንጂ ሲቆርጥ አይታይም ይላል፡፡ትንሽ ዘረኛ ነገር ስለነበረው ለአንባቢ ስል አሻሽየዋለሁ፡፡የበሬ ብልት ይወድቃል ብላ ስትከተል እንደ ኖረችው ቀበሮ እንዳንሆን ያልሁት ደጋግሜ ልብ ካልሁት ህወሃት መንደር ለውጥ እንዳንጠብቅ ለማሳሰብ ነው፡፡ከጠቅላያችን በላይ ቅን መሪ፤ይቅር ባይ፤ የሚያራሩ ቃላትን የሚናገር ሳይሆን የሚያዘንብ፤አብሯቸው የሚውል ሰው ብዙ እንደሞከረ የሚታወቅ ቢሆንም ትንሽ ኢንች እኳን ፈቀቅ አላደረጋቸውም፡፡እንዴት ሰው ተሳስተን ሊሆን ይችላል፤እኛ የተረዳነው በዚህ መንገድ ነበር እንኳን አይልም፡፡ዝም ብለን የቤት ስራችንን እንስራ፡፡ በኬሚስትሪ እንረዳው ካልን ህወሃት የሁለት፤ሶስት ነገር ቅይጥ  አደገኛ ቡድን ነው፡፡ ልብ በሉ አደገኛ እንጂ ሃይለኛ አላልሁም፡፡ የኮሚኒስት፤የዘረኝነት፤የክህደት፤የሴረኝነት ውህድ ነው፡፡ከአስፈለገ ማብራራት ይቻላል፡፡እስከ አሁን የቆየው በዕኛ ድክመት እንጂ በዕርሱ ብርታትም አይደለም፡፡ ጀግና መሆኑን የሚያስመሰክረው ተመልሶ አራት ኪሎ ከገባ ብቻ ነው፡፡ፖለቲከኞችም ሆነ አክቲቪስቶች የህወሃት የበላይነት ነበር ሲሉ ደሜን ያፈሉታል፡፡ሰው ዝም ብሎ ጌታ ራሱ ላይ ይሾማል እንዴ? በቃ የበላይ ነህ ካልኽው የበላይ ነኝ ይላል፡፡ሰኞ የወጣ ስም፤ማክሰኞ አይመለስም እንዲሉ፡፡ህወሃት ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የበታችነት ነው ሲሰማው የኖረው አሁንም የሚሰማው፡፡ይህ ስሜቱ ይመስለኛል ጨካኝም ያደረገው፡፡የፈሪ ዱላ፡፡ይህንን በአማራ ያላክካል እንጂ አስፋልት አታቆሽሽ ሲለው የነበረውን ራሱ ያውቀዋል፡፡ይህን ደግሞ ከመስራቾቹ አንዱ ከሆነው ከአሰግድ ገ/ስላሴ መጽሐፍ ገሃዲ ቁጥር አንድ ታገኙታላችሁ፡፡እውነት ስለጻፈ አይወዱትም፡፡ከድርጅቱም ለቋል፡፡ለእኔ ይህ መጽሃፍ ብዙ ነገር የነገረኝ ነው፡፡ጸሐፊውን አመሰግናለሁ፡፡ እናም ላለፋት 27 ዓመታት የነበረው የህወሃት የበላይነት ሳይሆን “የህወሃት ወንበዴነትና ሌብነት” ነው፡፡ወንበዴነት የሚለው Mafia ለሚለው ሲሆን ሌብነት ደግሞ corrupted ለሚለው ነው፡፡ጠቅላያችን እንዳሉት ሙስና ካልተሸሞነሞነ  ሌብነት ነው፡፡ የፈለገ በሚፈልገው መግለጽ ይችላል እኔ ግን አንድም ቀን የህወሃት የበላይነት ብየ ጽፌም ተናግሬም አላውቅም፡፡ለምሳሌ የነጮች የበላይነት አለ፡፡የአሜሪካ የበላይነት አለ፡፡ዕውነት ነው፡፡ህወሃት እኮ አገር  አተራምሶ ና ዘርፎ አይደል የሄደው፡፡ ዕውነቱ ይህ ነው፡፡ታዲያ በስሙ እንጥራው ከተባለ የሚገልጸው ይኽው ነው፡፡ዘመዶቹ በፈለጉት ይጥሩት፡፡

የህወሃትን ቁማር አለማብቃቱንና መዘናጋት እንደሌለብን ሰሞኑን ዩ ቲዩብ ላይ ከተለቀቁ ሰሞንኛ ጉዳዮች ላንሳ

1ኛ፡ እናቶች በየክልሉ እየዞሩ እንባቸውን ሲያፈሱ ነበር የከረሙት፡፡ትግራይም አቅንተው ነበር፡፡እናም አንዷ ዕናት ደብሬ ፊት እያነባች ወደ ፊት መጥታ ሰትንበረከክ ያሳያል ቪዲዮው፡፡ጨካኙ ደብሬ ግን ወደ ወንበሯ እንድትመለስ በእጁ እያመላከተ ነው ያሸማቀቃት፡፡ከሁኔታው ስርዐት ያዥ አይነት ነው፡፡100% እርግጠኛ የምሆነው አብይ ቢሆን ኖሮ መጀመሪያ ሮጦ ያነሳታል፤ ከዚያም አቅፏት ያለቅሳል፡፡ይቺ  እናት እኮ ከሰፈር በሩህሩህነቷ ተመርጣ የሄደች እናት ናት፡፡ደደቢት ያጠናው የስብሰባ ስነ ስርዐት እንጂ እንባዋ ደብሬ አልታየውም፡፡በእናት የሚቀልድ ጨካኝ፡፡እንደ አብይም አያልቅስ ግን እንደ ባህላችን ሮጦ እንኳን ኧረ አይገባም አናቴ ይነሱ ብሎ ቢያነሳቸው? እኔ የማውቀውን መልስ ለምን እጠይቃለሁ፤ ደብሬ ያደገው ደደቢት ነው፡፡ከዚያ በኋላ ያወራላቸው ደረቅ ፖለቲካ ያው የተለመደው ክህደት ነው፡፡እንዴት እንደሚገባቸው አላውቅም፡፡እናቶች የእነሱን ስራ የሆነውን ሰላም እየሰሩ እንደሆነ፤ይልቅስ ትግራይ በጠላት እንደተከበበች ነበር የነገራቸው፡፡ያው ሌላውን አስተምሩ ነው፡፡የሰላም ድርጅት ከሆነ ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ ከአራት ኪሎ ያባረረው ? መባረሩንም ይክዳል ህወሃት ነውና! ህወሃት አገር ያተራመሰ እንጂ ሰላም ሲያውጅ የኖረ አልነበረም፡፡ይህንን እናቶችም ያውቃሉ፡፡አሁን ፖለቲካ ቡና ማጣጫ ነው፡፡ለማ እንዴት ባለ ትሁትነት እንደተቀበላቸውም አይቻለሁ፡፡ከህዝብ ጋር ነዋ የኖረው፡፡ደደቢት አላደገም፡፡ህወሃት ህዝብ ጠላን ማለት ሳይሆን ማለት ያለበት ለምን ህዝብ ጠላን ቢል መልሱን ያገኘዋል፡ቀላል እኮ ነው፡፡ሽባ ያደረገውን መቁጠር ነው፤ያኮላሸውን ማሰብ ነው፤አጥቶት አይደለም፤ያው ሸፍጥና ክህደቱ ነው፡፡ይሄ ደግሞ ማነስ ነው!!! እንኳን ድርጅት ግለሰብ እንኳን ሃላነት ይወስደል፡፡አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ብዙ ሰው የሚያውቃቸው ናቸው ለቃለ መጠይቅ እንግዳ ሆነው ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያሳድጉ ተጠይቀው መምህር ናቸውና በምሳሌ ያስረዱት ነገር እስከ አሁን ትዝ ይለኛል፡፡”ህጻናት ልጆቻቸው ብርጭቆ ከጠረጰዛ ላይ ጥለው ይሰብሩና እማየ እማየ ብርጭቆው ተሰበረ ይላሉ፡፡እኔም ጠርቼ ብርጭቆውን ሰበርሁት በል! ብርጭቆው ራሱን አልሰበረም ብየ ሃላፊነት መውሰድ ከአሁኑኑ እንዲለማመዱ ነው ያደረግሁት፡፡በህይወት ውስጥ ሃላፊነት መውሰድ ትልቅ ነገር ነው” ያሉት ትዝ ይለኛል፡፡ ህወሃት ግን ደጋግሜ እንዳልሁት ጅግና እያለ ሲፎክር ከርሞ ፈተናው ሲመጣ ሮጠው እናታቸው ቀሚስ ውስጥ ነው የተደበቁት!

2ኛ፡ ይህ ደግሞ ገዱና ደብሬ በሃይማኖት ተቋማትና አገር ሽማግሌወች ድካም በጋራ የሰላም መልክት ባስተላለፋት ጉዳይ የገዱን ገራገር ንግግርና የደብሬን ዳግም ካድሬነት ወይም ኮሚኒስትነት ያየሁበት ነው፡፡ይሄ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌወች ስብሰባ ነው፡፡ደብሬ ያለው-የሃይማኖት አባቶችን የሚያከብረው ህዝብ ስለሚወክሉ፤ተከታይ ስላላቸው፤ህዝብ ደግሞ ዋናው ወሳኙ እንደሆነ ነው የተናገረው፡፡ተመልከቱ እንግዲህ የህወሃትን ሸፍጥ…ከድሮ ጀምረው የህዝብ ልጅ፤የህዝብ ድርጅት፤የህዝብ ወገንተኝነት፤ህዝባዊ ሰራዊት….ወዘተ….ይላሉ፡፡ዕውነቱን ግን የኖርነው ነው፡፡ጥቂት አምባገነኖች 27 ዓመት ዕኛንም አገራችንንም ተጫውተውብናል፡፡ህዝብ መርጦ አያውቅም ግን መርጠሃል ይሉታል፡፡ህዝብ ሰብዓዊና ህጋዊ መብት አልነበረውም፡፡እውነትም፤ህግም እነሱ ነበሩ፡፡ግን የሚሉትን በእነዚህ አባቶች ፊት ሰማን፡፡እንኳን አባቶች እኔ እንኳን ምንም ተከታይ የለለኝ በሰውነቴ ክብር ይገባኛል፡፡በዚህ ቅር የሚለው ድርጅት አለ ማለት ነው፡፡ደብሬ አባቶችን ለማመስገን የህዝብ ልጅ መሆናቸውን አመንክዮ ፍለጋ የግድ ደደቡት መውረድ ነበረበት፡፡በዕውነት ይህ ህዝብ እያሉ በህዝብ የሚቀልዱትን መቼ ነው የምናስቆማቸው? ዋና ሚዲያውም ያው ዳር ዳር እያለ ነው፡፡እናም ያለንበት ሁኔታ እየታወቀ ድንበር ችግር የለውም ይላል፤አንድ ክንድ ተገዶ ካልሆነ ይሰጥ ይመስል! እኛ ጥያቄ የለንም ይላል ደብሬ፤፤ገዱ ሃቀኛው አማራ በዕርግጥ ጥያቄ አለው ይላል፤ጸቡን ግን አንፈልግም አለ፡፡ስለ አማራ ህዝብ ከገዱ በላይ ደብሬ ተናገረ፡፡ሱዳን ይሻለናል የሚለውን አልሰማሁም፡፡ግን የቅማንትን ኮሚቴ አስታጥቆ እያስገደለ ነው ስለ አማራ ህዝብ የማዘናጊያ ንግግር የደረደረው፡፡ድሮም ፊት ለፊት ከገደሉን በቅጥረኞች ያስገደሉን ይበልጣል፡፡

እናም ሳጠቃልል የህወሃትን ነገር ፈጣሪ ይመርምረው፤እኛ ግን እውነትን ይዘን እንታገል፡፡ገዱ ጀግናና ሃቀኛ ነው፡፡ለእነዚህ ሰወች የሚሆን ሰብዕና ግን የለውም፡፡ስለሆነም የሚያሰማማን ጥያቄአችን መመለሱ ነው፡፡አባቶችም ይህንን ሊያውቁልን ይገባል፡፡ለደብሬ የወሰን  ጉዳይ ቀላል የሚሆነው ካሜራ ፊት ነው፡፡ይህንን አሳምረን እናውቃለን፡፡ አብረን አረጀን እኮ ህወሃት….የአማራ ወዳጅ ……

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.