የመቀሌው የ“ሠልፎች ሁሉ እናት” በወያኔ ሥሪት ኒኩሌር ቦምብ ተመታች! (ይነጋል በላቸው)

ትግራይ ቲቪን ጨምሮ የትግራይ መገናኛ ብዙኃን እስካሁን ድረስ በብቸኝነት ይዘው የሚኩራሩበት፣ የትግራይ ተወያይ ምሁራን የሠልፈኛውን ብዛት ከ200 ሺህ አስበልጠው የገመቱበት፣ ወያኔዎች ለጊዜውም ቢሆን የሚኮፈሱበት፣ ትግራይኦንላይንና አይጋፎረም “the mother of rallies” በሚል በከፍተኛ ኩራት የሚዘግቡት፣ በተጋሩ አክቲቪቶች ምሥክርነት መሠረት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየተቀባበሉ “24 ሰዓት የሚያራግቡት” … ያለፈው ቅዳሜ የመቀሌ ሠልፍ ትናንት ማታ ለመሥራት ከ27 ዓመታት በላይ ጊዜ በወሰደ የወያኔ ኒኩሌር ቦምብ መመታቱን ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ኪሣራ አያድርስ፡፡

ትናንት ማታ በዋልታና ፋና እንዲሁም በአማራና በኢቲቪ አንድ ዶኩመንተሪ ቀርቦ ነበር፡፡ በመሠረቱ እንዲህ ዓይነቱን ሰቅጣጭ ዝግጅት አለማየት ጥሩ ነበር፡፡ ግን የሀገር ነገር አያስችልምና እያዘንን፣ እያነባን፣ አንዳንዴም ዐይናችንን እየሸፈንን አየነው፡፡ ጓደኛሞች እየተደዋወልንና የስልክ መልእክት እየተለዋወጥን “እንዲህ ያለውን ዝግጅት እያየህ/ሽ ነወይ?” በሚል የሰማን ላልሰማ አዳረስን፡፡ ይህን የወያኔ ኒኩሌር ቦምብና የሕዝብ ሰቆቃ ከሞላ ጎደል አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕሕብ እንደሚመለከተው ግልጽ ነው፡፡ “ኒኩሌር ቦምብ” ለማለት የተገደድኩት ራሳቸውን በራሳቸው ለማጥፋት የሚያስችል ሁነኛ መሣሪያ ሊሆን የበቃውን ይህን ሁሉ ዘግናኝ ድርጊት ለመግለጽ ሌላ ቃል በማጣቴ ነው፡፡ የቆፈሩት ጉድጓድ እጅግ ራቀና በሚያሳዝን ሁኔታ እነሱና ደጋፊዎቻቸው ሲገቡበት ቁልጭ ብሎ ታየኝ፡፡ ትግራይ እንደሕዝብም እንደ ክ/ሀገርም ቆም ብላ ማሰብ ያለባት ጊዜ ላይ እንደደረሰች ለማስታወስ ወልይ ወይም ደብተራ መሆን አያስፈልግም፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚወራውን ሁሉ ለጊዜው እርሱት፡፡ ያ ዓይነቱ ከንቱ ስብከትና ፕሮፓጋንዳ ለሩዋንዳና ለሦርያም አልጠቀመም፡፡ እውነቱን እንጋፈጥና ከወዲሁ መፍትሔ የሚገኝ ከሆነ እንሞክር ይልቁንስ፡፡ “እንዲህ ብዬ ነበር”ም አይሠራም፡፡ አለባብሰን የምናፈው ሁሉ በኋላ እንዳይቸግረን እሰጋለሁ፡፡ መስረም አበራ የተባልሽ  መምህርትና አክቲቪት እግዜር ይስጥሽ፤ ትናንት ማታ በኢሳት ያልሽውን ሰምቻለሁ፡፡ እሷን እንስማት!

አሁን ምን ቀረ? ምንም፡፡ ሕወሓት ለዝግጅቱ ብዙ የደከመበት ሰልፍ አፈር በላ፡፡ በሰልፉ ዕለት በየሆቴሉና በየመዝናኛው እየዞሩ ከሆቴሎቹ የዘወትር የዕለት ገቢ ዕጥፍ በመክፈል ሕዝብ በነፃ እንዲስተናገድና ጠላቶቹን በጭርሆታት(በመፈክሮች) አፈር-ድሜ እንዲያስግጥ ለማድረግ ያፈሰሱት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የሀገራችን ገንዘብ አንድም ትርፍ ሳያስገኝ ውኃ በላው፡፡ ሠልፉ ያስገኘላቸው የተወሰነ ሥነ ልቦናዊ መኮፈስ የአንድ ሣምንት ዕድ እንኳ አግኝቶ ዳዴ ሳይል በአጭር ተቀጨ፤ የበረዶ ውኃ ፈሰሰበት፡፡ ወያኔ ላለፉት በተለይ 27 እና ባጠቃላይ ደግሞ 44 ዓመታት ሲደክምበት የነበረው ኒኩሌር ቦምብ ስኬታማ ሆኖለት ይሄውና ለተፃራሪዎቹ አሳልፎ በመስጠት ራሱ ላይ እንዲፈነዳ አደረገ ፡፡ ከዚህ በኋላ ወያኔ ሊያንሠራራ በሚችልበት አቋም ላይ አይደለም የሚገኘው፡፡ ቀባሪ ካልጠፋ በስተቀር ሞቷል፡፡

በዶ/ር ዐቢይ አገላለጽ ብልሁና አስተዋይ ሲሳይ አጌና በቅርቡ በኢሳት የዕለታዊ ዝግጅት ላይ ሲናገር እንደሰማሁት ወያኔ ከቶውንም ቢሆን ከአሁን በኋላ ወደ አራት ኪሎ ሊመጣ አይችልም፡፡ የሚመጣ ከሆነ ግን እንደሲሳይ እኔም እላለሁ ሁላችንም ብንሞት ይሻለናል፡፡ ሞት ርስት ነው፡፡ እየተሰቃዩ ከመኖር ሞት ይሻላል፡፡

ወያኔ ሊነግሥና እንደቀደመው ጊዜ ጥሬ ብስናቱን ሊለቅብን የሚችለው መቶ ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያልቅ ብቻ ነው፡፡ ያ ደግሞ በዜሮና በዜሮ መካከል ያለ ዜሮ መቶኛ ዕድል ነው፡፡

በትናንትናው ዶኩመንተሪ ያየናቸው ግፉኣን ወገኖች አባይን በጭልፋ ዓይነት ናቸው፡፡ በየቤቱ ቁስሉንና ጠባሳውን ደብቆ የሚኖረው የወያኔ የስቃይ ሰለባ የትዬለሌ ነው፡፡ እነዚህ ጭራቆች ያላደረጉን ነገር የለም፡፡ ልንረዳው የሚገባው ዐቢይ ነገር ግን በነዚህና በሌሎቹም ላይ የወረደው ስቃይ በነሱ ብቻ የወረደ ሳይሆን በኛም ጭምር እንደወረደ በመቁጠር ቁስላቸው እንዲጠዘጥዝን እኛን በነሱ ቦታ ተክተን ማየት አለብን፡፡ በዚያ ላይ እነዚህ ወገኖቻችን በወያኔ ያጡትን ነገር ሁሉ ዕጥፍ ድርብ አድርገን መመለስ ይኖርብናል፡፡ ሕይወታቸውንንና የጎደለ አካላቸውን መመለስ ባንችል የተቀሙትን ሀብት ንብረታቸውንና ገንዘባቸውን፣ መሬታቸውንና ክብራቸውን፣ ሥራቸውንና ደሞዛቸውን በአግባቡ መመለስ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝብና መንግሥት ነገ ዛሬ ሳይሉ ወደ ተግባር መግባት አለባቸው፡፡ እንዲህ ሲሆን ነው ለሀገርና ለሕዝብ መታገል ዋጋ ኖሮት “ለካንስ ሕዝብና መንግሥት የዜጎችን ለፋትና ድካም ያውቃሉ!” ሊባልና ትግል ከንቱ እንዳልሆነ ዜጎች መረዳት የሚችሉት፡፡ የነሱን መስዋዕትነት ዋጋ ላለማሳጣትም ከአሁን በኋላ በወያኔዎች ፈለግ መጓዝን ዕርም ማለት ይኖርብናል፡፡ በዜግነት እንጂ በብሔርና በጎሣ የምንከፋፈል ከሆነ በዜጎቻችን ደምና አጥንት እንደመቀለድ ነው፡፡ በዚህ ጠማማ መንገድ ተጉዞ ያለፈለትና የበለፀገ ሀገር ደግሞ የለም፡፡

ከወያኔ ጋር የሚደረገውን ትልቁን ጦርነት ራሱ ወያኔ እያከናወነልን ነው – በወገኖቻችን ስቃይ ማላገጥ ይሆንብኛል እንጂ በዚህ ሥራው ወያኔ ሊመሰገን ይገባው ነበር፡፡ እንደዚህ ያሉ ዝግጅቶች በስፋት መቀጠል አለባቸው፡፡ የተደበቁ ጉዶች ይውጡና ዓለም ይወቀው፡፡ አንዲትም ጥይት ሳንተኩስ ወያኔን ማንበርከክ የምንችለው በዚህ አሣፋሪ ታሪኩ ጭምር ነው፡፡ ክፉዎችን የገዛ ኃጢኣታቸው ጭምር ስለሚያሳድዳቸው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ወያኔ መቀመቅ የሚወርድበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው – ለጊዜው የሚያግደረድረው የማይናቅ የሰው ኃይልና ብዙ ገንዘብ እንዲሁም በደህናው ቀን ያሸሸው የጦር መሣሪያና ሎጂስቲክስ እንዳለው መገንዘብ አለብን፡፡ ሆኖም የመሣሪያና የወታደር ብዛት ጎዶሎ ቀንን እንደማያቃና መረዳትም ተገቢ ነው፡፡

ከአሁን በኋላ የለውጡ ኃይል የሚያደርገው ትግል ይበልጡን ከራሱ ጋርና ወያኔ ትቶብን ከሚያልፈው ዘርፈ ብዙ ችግር ጋር ነው፡፡ ይህም ትግል ቀላል አይደለም፡፡ የወያኔ ጠባሳ ከወያኔ ጋር ከሚደረገው ትግል ባልተናነሰ እልህ አስጨራሽና አድካሚ ነው፤ ተስፋ መቁረጥ ግን አይኖርብንም፡፡ የመከነ አእምሮን፣ የጠፋ መልካም ስብዕናን፣ የወደመ ኢኮኖሚን፣ የተንሰራፋ ዘረኝነትን፣ የተበረዘና የተከለሰ እንዲሁም በሰይጣን የተወረሰ ሃይማኖትን፣ አገርን እግር ከወርች ያሠረ ሙስናን፣ ሆድ አምላኪነትን፣ ኅሊናቢስነትን፣ ሀገርንና ወገንን ባወጣ መሸብቸብን የመሰለ ዕኩይ ባሕርይን፣ ጎጠኝነትን፣ ክፋትን፣ የሥልጣን ሱሰኝነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣… ማስተካለልና ሚዛናዊ ስብዕናን የተላበሰ ዜጋን ወደ ቀድሞ ቦታው መመለስ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም ከፈጣሪ ጋር ይቻላል፡፡

ከሀገሬ ጉዳይ አይበልጥም እንጂ ማስቀደም የነበረብኝ የግል ጉዳይ ነበር፡፡ ሌሊቱን በነገር ቁጭት ዕንቅልፍ የሚባል አላየሁም፡፡ በሌሊት ተነስቼ የዘወትር ጸሎቴን እንኳን ሳላደርስ ወደ ቢሮየ ገሰገስኩ፡፡ ብዙ ተጉዤ ካዛንቺስ አካባቢ ደረስኩና መንገድ ሳቋርጥ አንድ ታክሲ ሊጨፈልቀኝ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ የፍሬኑ ጩኸት አሁን ደረስ በጆሮ አለ፡፡ ፈጣሪን አመስግኑልኝ፡፡ ኢትዮጵያም ወያኔ ከደገሰላት ዕልቂት የተረፈችው ልክ እንደዚሁ ለጥቂት ነበር – ተርፋ ከሆነ፡፡ አንድ ሳይባል ሽህ ስለማይባል ስለኔ ማንሳቴን አፉ በሉኝ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.