ሚድያዎች የህብረተስብ የጀርባ አጥንት ናቸው (ከጎሹ ገብሩ)

በህዝብ ላይ አፈናና ጭቆና የሚፈፅሙ የመንግስት አካላት ውይም የተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎች ከሁሉ የሚያስፈራቸው ነግር ቢኖር ነፃ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅትን ነው። ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያትም የሥልጣናቸው እድሜ ለማራዘም ሲሉ የሚቀናቀኗቸው አካሎችን በሙሉ ሰበብ አስባብ በማፈላለግ ከጨዋታው ውጭ ለማስወጣት በሚወስዱት አሰቃቂ እርምጃ ሚስጥሩ ተደብቆ እንዲቀርና ማስረጃ በማጥፋት ከተጠያቂነት ለማምለጥና ለመዳን ነው።

ኢሳት በወያኔ ፍዳውን ለሚያይ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ባለ ውለታ እንዲሁም አይንና ጀሮ ነው። በተለይ የመገናኛ ዘዴው እንደ አሁኑ ስልጣኔ ባልተራቀቀበት ዘመን አምባ ገነን መሪዎች ለስልጣናቸው አደጋ ነው የሚሉትን አካል ሁሉ አፍነው በማጥፋት የስልጣን እድሜአቸው ያለ ተቀናቃኝ ለማቆየት ሲሉ ነው። በሞያቸው በማገልገል ላይ እያሉ መንግስትን ለምን ተቻችሁ በማለት ጋዜጠኞችን  በደህንነት አካላት እየታደኑ ደበዛቸውን በማጥፋትና በቶርቸር ከሚያሰቃዩ የሦስተኛ አለም አገሮች መካከል በዋናነት ኢትዮጵያ አንዷ አገር ናት።

በእኔ የእድሜ ቀጠና ውስጥ ሦስት የመንግስት ሥርዓቶችን መታዘብ ችያለሁ። እነሱም የባላባታዊ ሥርዓት፤ወታደራዊ ፋሽስት እና የጠባብ ብሄርተኞች ፋሽስታዊ ስብስቦች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል ግን በሚዘገንንና በተራቀቀ ዘዴ የጋዜጠኞች ማህበራት በማጥፋት፤ አባሎችን በገፍ በማስር፤ በማሰቃየት፤በማሰደድና በመግደል ተወዳዳሪ ያለተገኘላት በኢትዮጵያ የአስተዳደር ታሪክ ውስጥ የትህነግ(ወያኔ)የወንበዴዎች ድርጅት በቀዳሚነት የምትጠራ ናት። ይህን ሥል  የግል ጥላቻን ለመበቀል  ሳይሆን ከኢትዮጵያውያን በስተጀርባ ዓለም ሁሉ ያወቀው እውነታ በመሆኑ ነው።

በጋዤጠኛነትና በወትድርና ሞያ የሚሰማሩ አካሎች በሙሉ የሚጠብቃቸው አደጋ ተመጣጣኝ ነው። ሁለት ተፎካካሪ ሃይሎች በሚያደርጉት  ውግያ ወቅት ከሁለት እሳት መካከል በመግባት ጦርነቱን የሚዘግበው አካል ከአደጋው ለመትረፍ ያለው እድል በጣም ጠባብ በመሆኑ የጋዜጠኝነት ሞያ አደገኛ ከሚባሉ የሥራ አይነቶች በዋናነነት የሚጠቀስ ይሆናል። ምክንያቱም ከአሁን በፊትም ሆነ አሁን ላይ እየተካሄዱ የሚገኙት ጦርነቶች የብዙ ሞያተኞች ሕይወት ሲቀጠፍ በማየቴ ነው። ጋዜጠኛ መሳርያ ካነገበው ወታደር ጋር ባልተናነሰ እኩል መስዋእትነት መክፈሉን እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።

ዛሬ ይህችን አጭር ጽሁፍ እንድጭር ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ኢሳት ከተመሰረተ ጅምሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያደረጋቸው አመርቂ ተግባሮች እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ መብቴን ተጠቅሜ የሚሰማኝን ሃሳብ ለመግለፅ እንጅ አንዱን ኮንኘ ሌላውን ለማሸማቀቅ ወይም በጭፍን ድጋፍ ለመስጠት እንዳልሆነ ቅድሚያ ግልፅ ማድረግ እፈለጋለሁ። ኢሳትን ያለ ምክንያት አልነበረም ምስጋናዬ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልኝ የፈለኩት። እንደሚታወቀው በ1968 እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ዛሬ አገራችን ለደረሰባት ውርዴትና ውድቀት ዋና ተዋናኝ የሆኑት ትግራይ በቀል የወንበዴዎች ስብስብ ቃታ ስበው የመግደል ኢላማ የተለማመዱት በወልቃይት ጠገዴ የዋህ ህዝብ ላይ መሆኑ በእርግጠኝነት መመስከር እችላለሁ። ተወልጄ ያደኩት በዚህ አካባቢ በመሆኔና ዘራፊዋ የደደቢት ሽፍታ የተከዜ ውንዝ ተሻግራ ስትመጣ በወቅቱ በአካባቢው በመኖሬ ጭካኔዋና አረመኔያዊ ተግባሮችዋ በቦታው ሁኜ ስለታዘብኩ ነው። የህዝቡን በደል ወያኔ ከደበቀችበት ጉድጓድ ቆፍሮ በማውጣት ሁሉም እንዲያውቀውና የወያኔ ገመና እንዲጋለጥ በማድረግ አብዛኛው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ከተበደለው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ጎን እንዲሰለፍ ያደረገ ትልቁ የነብስ አድን ድርጅት ቢኖር ኢሳት በመሆኑ ነው።

በዛ ሥዓትና ወቅት እሪ የሰው ያለህ ብትል እርዳታ የማታገኝበት፤ ጉልበት ያለው መስካሪ በለለው ቦታ ላይ  እንዳሻው የሚደፈጥጥበት፤ የመሳርያ ነካሾች ዘመን ጎልቶ በገነነበት ግዜ፤ ተበዳይ አፉን ለጉሞ የሞት ፅዋ እንደ ተፍጥሯዊ ሥጦታ ሳይወድ በግድ ልጆቹ ሲገደሉ፤ሚስቱ ስትደፈር፤ያፈራው ንብረት ሲዘረፍና ከቀዬው ሲፈናቅል ማንም ያወቀና የደረሰለት አልነበረም ። ነገሩ ሁሉ ተዳፍኖ በነበረበት ወቅት በአካባቢው ተወልደን ያደግነው በስደትም ሆነ በአገር ውስጥ የምንኖር አገር ወዳዶች አቅማችን በፈቀደው ነገሩን ለሚመለከተው ያገባኛል የሚል ወገን እንዲያውቀው ለማድረግ ጥረት ብናደርግም ቅሉ በቂ ሊሆን ግን አልቻለም።

በእግዚአብሔር ሃይል ይህን በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የተፈፀመው ግፍና እረሮ እንዲያጋልጥ ኢሳት የተባለ ድርጅት ከስምንት አመት በፊት ተቋቁሞ የመጀመርያ አጀንዳው እንዴት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህብረተሰብ ከተጋረጠበት ስቃይ ማዳን እንደሚችል ጥረት ለማድረግ ቅድሚያ የተገናኘው በአካባቢው ከተወለድን የልሳነ ግፉዓን ድርጅት አባሎች ጋር ነበር። አስታውሳለሁ አቶ ሲሳይ አጌና በመጀመርያ ቀን ውይይታችን የገለፀልን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ እያለሁም የዚህ ህዝብ እረሮ በስፋት እሰማ ነበር። ሥለዚህ አብረን ጠንክረን በመስራት ይህን የታፈነው ወግናችን ሁሉም እንዲያውቅለት ቅድሚያ መስጠት ይገባናል የሚል ትልቅ ተስፋ ሰጠን።

ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓንም ወድያውኑ ይህን እድል በመጠቀም ሁለት የአካባቢው ተወላጆች በኢሳት ተሌቪዝን መስኮት በመውጣት በወገናችን የደረሰውን በደል ሁሉም እንዲያውቀ እድል አገኘን። ኢሳት ከዝያ ግዜ ጀምሮ ወያኔ በወልቃይት ሕዝብ ላይ ስትፈፅመው የቆየችውን ድብቅ ሚስጥራዊ በደል ቆፍሮ በማውጣት ዕኩይ ገመናዋን እንዲጋለጥ በማድረግ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊና የዓለም ህብረተሰብ ከተበደለው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ጎን እንዲሰለፍ ያደረገ ባለውለታችን ነው። ይህን ስላደረገ ከፍ ያለ ምስጋና ሳቀርብ ያለ ማጋነን በልበ ሙሉነት ኩራት እየተሰማኝ ነው። ሥለዚህ ኢሳትን የማይመጥን ጥላሸት የሚቀባ አካል ካለ የትላንትናን ታሪክ ሳይጠይቅ ጀግኖች በጠረጉት አውላላ ጎዳና ላይ ሆኖ አሉ ቧልታ የሚያናፍስ ሥራ ፈት ሁሉ አድማጭ አይኖረውም። ይልቁንስ በወያኔ የሚበደለውን ህዝባችሁ ለመርዳት የድርሻችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ።

ትላንት ወልቂጤና ወልቃይት ለይቶ ማወቅ የተሳናችሁ የድል አጥብያ አርበኞች ሰከን በሉ ኢሳትን አክብሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባለ ውለታ መሆኑ ባይዋጥላችሁም እውነት ትማነምናላች እንጅ አትበጠስም ነገ ሃቁን ታገኙት አላችሁ የሚል ግምት አለኝ። ሌሎችም የሚድያ ተቋማት የማይናቅ በመጠኑ መስራታችው ቢታወቅም 24 ስዓት ሙሉ በወልቃይት ጉዳይ ትህነግን(ወያኔን) በማጋለጥ ትልቅ ሥራ የሰራ ከኢሳት ጋር የሚወዳደር ማንም የለም። በተለይ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወልዳችሁ ውለታ ለዋለላችሁ አካል እርዳታውስ ይቅር እግዚአብሔር ይስጥልን ብሎ ማመስገኑ እኮ ክፍያ የለውም ። ከእንግዲህ ወድያ ኢሳት እንደሆነ በጥንካሬ እየሰፋ እንጅ እየደከመ አይሄድም። ኢሳቶች በጣም እወዳችሁ አለሁ እደጉ ተመንደጉ።

ይህች አጭር ፅሁፌ የምታንፀባርቀው የግሌን ሃሳብ እንጅ ማንንም ድርጅት ወክየ እንዳልሆንኩ እንድትገነዘቡልኝ በአክብሮት ላሳስብ እወዳለሁ። ኢሳትን በገንዘብ ማጎልበት ማለት ስንጓጓለትና ስንመኘው የነበረ ነፃ ሚድያ በአገራችን በይበልጥ እንዲስፋፋ መሰረት ጣልን ማለት ነው።

 

ነፃ ሚድያውች የህልውናችን ዋስትና ናቸው።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር።

ከጎሹ ገብሩ።

 

 

Loading...

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.