የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ዋና ዋና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ድሎች እና አስደናቂ መሪሆዎች (ብርሃነመስቀል አበበ)

በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት(#TeamLemma) ወደ ስልጣን በመጣ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን ከመበታተን እና ከመተላለቅ አድኖ የዴሞክራሲ ሃዲድ ላይ ተስፋ ሰንቀን እንድንጓዝ በማድረጋቸው ከስድስት ወራት በፊት የነበርንበትን የሚያስታውስ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለዘለዓለም የሚዘክራቸው እና ታሪክ የማይረሳቸው መሪዎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እንደ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የሚቆጠሩ ክስተቶች ናቸው።

ከዚህ በአገር ውስጥ ከተገኘው ድል የማይተናነሰው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ድሎች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው በጠቅላይ ሚንስትሩ አመራር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረገድ የተገኙት ድሎች በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ቀደምት ስፍራ ልይዙ የሚችሉ ትላልቅ ድሎች መኖራቸው ነው።

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረገድ የተጎናፀፋቸውን ድሎች እና የመሪሆ ለውጦችን በሚገባ ለመገንዘብ በእርሳቸው የሚመራው መንግስት ስልጣን ከመያዙ በፊት አገሪቷ የነበረችበትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሪሆዎች እና አደጋዎችን ዞር ብሎ መመልከት ለንፅፅር ይረዳል።

በጠቅላይ ሚንስትር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግስት ስልጣን ከመያዙ በፊት፣

1ኛ፣ ህወሃት ሲመራበት ከነበረው የአገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሲ የተነሳ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍርካ እና አጎራባች አገሮች ዛሬ ነገ ተበትናና ፈርሳ ለአጎራባች አገሮች እና ለአለም አቀፍ መህበረሰብ የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖላቲካና የማህበራዊ አደጋ(crisis) የምትፈጥ የስጋት ምንጭ እና ጠብ አጫሪ አገር ነበረች።

2 ኛ፣ ከጎረቤት አገር ሳንወጣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረውን ውጥረት ብንመለከት ኢትዮጵያ እስከ 150 ሺህ ወታደር በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ በተጠንቀቅ አሰማርታ በወር እስከ 20 ሚልዮን ብር ለወታደር ስንቅና ትጥቅ የምትገፈግፍ አገር ነበረች፣ (ይህ ገንዘብ ስንት ት/ቤት እና ጤና ጣቢያ እንደሚያሰራ ለህሊና ፍርድ መተው ነው።)

3 ኛ) ኢትዮጵያ በአፍርካ ቀንድ በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን እንድሁም በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ላሉት ግጭቶች እንደ ገለልተኛ የማትታይ አበጣባጭ እና ከብጥብጥ ለማትረፍ የምትሰራ አገር ነበረች፣

4ኛ፣ በአለም ዙሪያ ሁሉም የሰለጠኑ አገሮች መንግስታት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች እና ቡድኖች የሚያወግዟት የእስራት፣ የግድያ፣ የስደት እና የዘረፈ አገር ብቻ ሳትሆን የአሜርካ መንግስት እና የአውሮፖ ህብረት አገሮች መዕቀብ ሊጥሉባት ደፋ ቀና የሚሉባት የአለም ህዝብ ማፈሪያ አገር ነበረች።

5 ኛ፣ በኢኮኖሚው ረገድ ዓለም አቀፍ እንቨስተሮች እና የንግድ ተቋማት የሚሸሻት፣ እና እንኳን ለብዝነስ ተመራጭ መሆን ቀርቶ እንደ አገር መቀጠሏን የሚጠራጠሯት አገር ነበረች።

6ኛ፣ በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በየቀኑ የሚያወግዟት እና ያሉባቸው አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያሏቸውን ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንድያቋርጡ ግፊት የሚያደርጉበት እና ይህን ለመቋቋም ኢትዮጵያ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለውጭ lobbists የምታወጣ አገር ነበረች።

7 ኛ፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች ነፃ አውጭ ግንባሮች አቋቁመው እና በተለያዩ አገሮች መሽገው እንደ ቅርጫ ልከፋፈሏት የሚያሴሩበት አገር ነበረች።

በዚህ መልኩ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ከህወሃት የተረከባት ኢትዮጵያ የአንድ ወር የውጭ ንግድ እንኳን የምታካሄድበት የውጭ ሚንዛሪ ያልነበራት አገር ነበረች።

ሌላው ሳይጠቀስ የማይተለፈው እውነታ ደግሞ የቲም ለማ አባል ከሆነው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየው እና ጥቂት ከህወሃት ዘመን ምንጠራ የተረፉ ፕሮፌሽናል ዲፕሎማቶች በስተቀር የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ከህወሃት የተረከበው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የበሰበሰ እና በካድሬዎች እና በችሎታ ማነስ ወይም በሌብነት ምክንያት በየኤምባሲው በግዞት በተላኩ የለውጡ ተቃዋሚ አምባሳደሮች የተሞላ መሆኑ በራሱ ለኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትልቅ አደጋ ነበር።

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ዋና ዋና የውጭ ግንኙነት ድሎች የተጎናፀፈው እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ከህወሃት መንግስት የወረሳቸውን ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች በማለፍ እና በማሸነፍ መሆኑ የመንግስታቸውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ድሎች ታሪካዊ ያደርጋቸዋል።

በዚህ መሰረት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ዋና ድሎችን እና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሪሆዎችን እና ፅንሰ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል።

1ኛ፣ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ ትልቁ እና የመጀመሪያው የውጭ ፖሊሲ ድል ኢትዮጵያዊያን ቶኮር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሪህ ተከትለው በመላው አለም የተበተኑትን ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ግንባር ቀደም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ምሰሶ ማድረጋቸው ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ወደ ስልጣን እስኪ መጡ ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለስረዓቶቹ ፍጆታ የሚውሉ ድጋፎችን ለማግኘት ሲባል ፈረንጆችን በመለማመጥ እና በመለመን ላይ ያቶኮረ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ይህን ፈረንጆች ቶኮር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአናቱ ደፍተው እና ገልብጠው የኢትዮጵያዊያንን የዜግነት ክብር የሚያስመልስ እና ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመከተል በጎረቤት አገሮች በእስር ሲሰቃዩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን አስፈትተው ወደ አገራቸው በመመለስ( በራሳቸው አውሮፕላን ሳይቀር) ፣ በምዕራቡ አለም ተሰዶ ለዘለዓለሙ የኢትዮጵያ መንግስት ጥለኛ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ከአገራቸው ጋር በማስታረቅ ወደ አገራቸው መመለሰ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያን የሲኦል ደጅ የነበሩትን የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ለኢትዮጵያዊያን በመክፈት( ከላይ የጠቀስኳቸው የህወሃት ምልምሎች እያሉና እያዩ) አገር እና ህዝብን፣ መንግስት እና ዜጋን አስታርቀዋል። ደምረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ይህ ያደረጉት ለመንበረ ስልጣናቸው እና ለግል ክብራቸው እንዲሁም ለህይወታቸው ሳይሳሱ ለኢትዮጵያዊያን ክብር ቅድሚያ በመስጠት ነው።

ለምሳሌ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የጎበኙት ስልጣን በያዙ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ሲሆን እንደ አዲስ መሪ የአሜርካን መንግስትን ኦፊሴላዊ የጉብኝት ግብዣ ሳይጠብቁ ነው። ዜጎቼን ለማየት የአሜርካን መንግስት ግብዣ አልጠብቅም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለክብራቸው ቁብ ሳይሰጡ በአሜርካን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር ጎብኝተው ዜጎቻቸውን አኩርተው መመለሳቸው በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎሳን ጀለስ እና በሚንያፖሊስ ያየነው ህዝባዊ ትዕይንት ታሪካዊ ምስክር ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩ በአውሮፖ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በመጎብኘት በፍራንክ ፈርት ያደረጉት ጉብኝት ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ግንባር ቀደም ምሰሶ አድርገው የሚመለከቱ መሆኑን ያመለክታል።

በተጨማሪም ራሱን የቻለ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ስር እንዲቋቋም ማድረጋቸው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ከኢትዮጵያ የክልል መንግስታት እኩል አድርገው እንድያዩና እንደ 10ኛ ክልል እንደሚቆጥሩት ያመለክታል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ የውጭ ፖሊሲ የኢትዮጵያዊያንን የዜግነት ክብር ከማስጠበቅ እና ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ከማድረግ አልፎ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ፖላቲካ እና መህበራዊ ኑሮ በቀጥታ እንዲሳተፉ ያደርጋል።

ለምሳሌ ከዚህ በኃላ በአግባቡ ከተሰራበት ኢትዮጵያዊያን ከውጭ የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ አሁን ካለው ወደ 4 ቢልዮን ገደማ ወደ 10 ቢልዮን ዶላር ከፍ ልል ይችላል። ይህ ኢትዮጵያ አሁን ከሁሉም አገሮች እና ድርጅቶች በእርዳታ እና በብድር ከምታገኘው ድምር የውጭ ምንዛሪ ይበልጣል። በተመሳሳይ ሁኔታ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጡ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በየአመቱ ወደ ኢትዮጵያ እንድመጡ በማድረግ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሰክተር እንዲያድግ ያደርጋል።የፖሊሲ ለውጡ የተለያየ ሙያ ያላቸው በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በሙያቸው አገራቸውን ተመልሰው እንዲያገለግሉ በር ከመክፈት አልፎ የውጭ ንግድ እና ፎሬን ዳሬክት ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ እንድያድግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

እነዚህና ሌሎች የተለያዩ ብሄራዊ ጥቅሞች ሲጤኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ ገበየሁ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቅድሚያ መስጠታቸው ታሪካዊና ብዙ ልነገርለት የሚገባ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ ነው።

2ኛ፣ ሁለተኛው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋነኛው ድል እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የነበረውን የምዕራብ እና ምስራቁ አለም ተኮር ፖሊሲ ትተው ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት የሚሰጥ ፖሊሲ መከተላቸው ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ስልጣን በያዙ በጥቂት ቀናት ውስጥ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ማለትም በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በዮጋንዳ፣ በሶማሊያ፣ በግብፅ፣ በሰውድ አረቢያ፣በአረብ ኤሜሬት እና ኋላም ታሪካዊውን የኤርትራ ጉብኝት ማድረጋቸው እንደዚህ አይነት ጉብኝቶችን በጎረቤት አገሮች ለማድረግ ጠቅላይ ሚንስትር አብይን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ የሚያደርጋቸው ብቻ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ መሪ መሆናቸውን ያመለክታል።

በዚህም ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ቅድሚያ በሰጠ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ወደ መቶ ሺህ ህዝብ ያለቀበት እና በቢልዮኖች የሚቆጠር የህዝብ ሃብት የወደመበትን ጠላትነት አጥፍተው በሁለቱ አገሮች መካከል ወዳጅነት እና መልካም ጉርብትናን መልሰዋል። በኤርትራና በጂቡቲ መካከል እርቅ ፈጥረዋል። በኤርትራ፣ በጅቡቲ እና በሶማሊያ መካከልም ሰላም አውርደዋል። በደቡብ ሱዳን ደም መፈሰስ አቁመዋል። በአረቦች እና በኢትዮጵያ መካከል ለዘመናት የነበረውን ጥርጣሬ አክስመዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ከሱዳን እስከ ታንዛንያ፣ ከጅቡቲ እስከ ዩጋንዳ ፣ ከሶማሊያ እስከ ሩዋንዳ የሚኖረው እና ለግብፅ፣ ለኑቢያ፣ ለአክሲም፣ ለላሊበላ፣ ለገዳ ስረዓት እና ለሌሎች መሰል ስልጣኔዎች መሠረት የሆነው እና በቋንቋ እና በባህል የተሳሰረው የሰሜን ምስራቅ አፍርካ ህዝቦችን ኢትዮጵያን መዕከል አድርጎ የኢኮኖሚና የፖላቲካ ትስስር ፈጥሮ የአፍርካ የኢኮኖሚ እንብርት እንዲሆኑ ለማድረግ ያቀረቡት ራዕይ የዚሁ ጎረቤት አገሮችን መዕከል ያደረገው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው አካል ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም በአፍርካ መምሪያ ስር የነበረው የጎረቤት አገሮች ንዑስ ክፍል ራሱን የቻለ መምሪያ ሆኖ ለጎረቤት አገሮች ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ተደርጓል።

በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የአፍርካ ቀንድን ምስቅልሉ ከወጣ የጦርነት ቀጠና ወደ ሰላማዊ ቀጠና በማሸጋገራቸው ብቻ ሳይሆን በህወሃት አስተዳደር ለአጎራባች አገሮች ስጋት የነበረችውን ኢትዮጵያ የአከባቢው አገሮች እንቆቅልሽ ፈቺ በማድረጋቸው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አፍርካዊ መሪ ባይሆኑ(ለዚያውም የደሃዋ ኢትዮጵያ) በአለም አቀፍ ደረጃ ለዘለኣለም የሚወደሱ እና የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። አሁንም ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።

3ኛ፣ ሶስተኛው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አፍርካ ተኮር ሆኖ ኢትዮጵያን የአፍርካ መዕከል ማድረግ ነው። ይህ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ፣ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ እና በአዲስ አበባ ከተማ ም/ ከንቲባ በአቶ ታከለ ኡማ መካከል በቅንጅት እየተሰራ ያለው ፖሊሲ አዲስ አበባን የፀናች የአፍርካ ከተማ ማድረግ ሲሆን በቅርቡ አፍሪካዊያን ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ ቪዛ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ አየር መረፉያዎች እንዲያገኙ ተወስኗል። ይህ አፍርካዊያን ኢትዮጵያ ሁለተኛ አገራቸው እንደሆነች እንዲቆጥሩ የሚያደርግ ሲሆን አዲስ አበባም በርካታ የአፍርካ ትሩስቶችን እንድታስተናግድ ያደርጋል።

ይህ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለአፍሪካ ትኩረት የሚሰጥ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አፄ ኃይለስላሴ አዲስ አበባን የአፍርካ መዲና ለማድረግ የአፍርካ አንድነት ድርጅት እና የተመድ የአፍርካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ እንዲያደርጉ ያደረጉበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀጣይ ነው። ይህ ፖሊሲ አዲስ አበባ ከኒው ዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥላ በአለም ሶስተኛ ዲፕሎማቲክ ካፒታል እንድትሆን አድርጓል።

ኢትዮጵያ የነዚህ አለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከመቶ ሃያ በላይ የውጭ ኤምባሲዎች መቀመጫ መሆኗ ለኢትዮጵያ ኩራት ብቻ ሳይሆን ብዙ ሽህ ዜጎች በነዚህ ተቋማት ሰራተኞች እንዲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሆቴሎች በኮንፍረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖላቲካዊ እና መህበራዊ ጠቀሜታ ለኢትዮጵያ አምጥቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ እና ም/ከንቲባ ታከለ በቅንጅት አዲስ አበባ የአፍርካ መዲና እና ወደ ፊትም የበርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች Host City እንድትሆን የሚከተሉት አፍርካን መዕከል ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊና ተገቢ ነው።

ከጃኖህ ዘመን ወዲህ ከተቋረጠ በኋላ በክቡር አምባሳደር አብዱልመጂድ ሁሴን(አሁን በህይወት የሉም) እና በኔው በራሴ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተመድ ጥላ ስር ወደ ላይቤርያ፣ ቡሩንዲ እና ሱዳን በመላክ እንደገና የተጀመረው እና አሁን ወደ 12 ሺህ የኢትዮጵያ ወታደሮች ያደገው በተመድ እና በአፍርካ ህብረት ጥላ ስር ኢትዮጵያ በአፍርካ የሰላም ማስከበር ስራ መሳተፏን እንድት ቀጥል ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ መወሰናቸው የዚሁ የአፍርካ ቶኮር ፖሊሲያቸው አካል ነው።

4 ኛ፣ አራተኛው የጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትኩረት ቀድሞ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው የምዕራቡ እና የምስራቁ አለም አገራት እንዲሁም የአለም አቀፍ ድርጅቶችን ይመለከታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በቻይና፣ በቅርቡ ደግሞ በፈረንሳይ እና በጀርመን ያደረጉት ጉብኝት እና ከነበር የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለይም ከአሜርካ፣ ከእንግሊዝ እና ከጣሊያን ከፍተኛ ባለስልጣናት መቀበላቸው የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ትክክለኛ መንገዱን ይዞ እየተመራ መሆኑን ያመለክታል። የተመድ ዋና ፀሃፊ ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማግኘት አዲስ አበባ ድረስ መምጣታቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በአፍርካና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ያላቸውን ተሰሚነት ያመለክታል። ይህም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ነው።

በመጨረሻም በህወሃት ዘመን ኢትዮጵያን በቶርቸር፣ በግድያ፣ በጅምላ እስራት፣ በስደት እና በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚኮንኑት የምዕራብ አገሮች፣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች እና የተለያዩ መንግስታዊ ድርጅቶች አሁን ምን እንርዳችሁ፣ ምን እናድርግላችሁ በማለት ወደ ኢትዮጵያ የሚከንፉ ሆነዋል። ይህም የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት(#TeamLemma) የአገር ውስጥ እና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውጤት ነው።

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያስመዘገባቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ድሎች እና ከአንድ እስከ አራት የተቀመጡት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ priorities እና መሪሆዎች ኢትዮጵያን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚመራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ priorities እና መሪሆዎች እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

Loading...

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.