“ማኅበራዊ ሚዲያ ሊያጠፋን ነው” ኃይሌ ገ/ሥላሤ (ነፃነት ዘለቀ)

ነፃነት ዘለቀ (netsanetz28@gmail.com)

“ማኅበራዊ ሚዲያ ሊያጠፋን ነው”  “ጌጤ ያለችው በውስጧ የምታስበውን ነው። እንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ስትሄድ የምትናገረው በወስጥህ ያለውን በመድገም ነው”

“አጋንንት የለም፣ የት ነው ያለው? ጥንቆላ፣ መተት የለም፡፡ ስፖርት ላይ የለም ውሸት ነው፣ ወሬ የወለደው ነው”

“ለገንዘብ፣ለፕሮፓጋንዳ፣ የራስን ተፈላጊነት ለማጉላት… ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው ስራ የፈጣሪ ስራ አይደለም። ይኼ የፈጣሪ ስራ ሳይሆን የአጋንንት ስራ ነው”

ከፍ ሲል የተቀመጡት ንግግሮች ኃይሌ ገ/ሥላሤ እንደተናገራቸው ተገልፆ በካሣሁን ይልማ መጣጥፍ ውስጥ አሁን ዘሃበሻን ሳነብ ያገኘኋቸው ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ ጊዜያት በጻፍኳቸው መጣጥፎች በእግረ መንገድ ያነሳሁት ቢሆንም በዚህ ዙሪያ አሁን እኔም አንዳች ነገር ማለት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ማኅበረሰባችንን እግር ከወርች ካሰሩ ባህላዊ የባዕድ አምልኮ ልክፍቶች አንዱ ይሄው የጥንቆላና የመተት ጉዳይ ነውና፡፡ የካሣሁንን መጣጥፍ ለማንበብ ከፈለጉ – http://www.zehabesha.com/amharic/archives/91337

ዓለማችን በጥንቆላና በመተት የተሞላች ናት፡፡ በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ገዢ – አገላለጹን ትንሽ ረቀቅ አድርጌ ዘመናዊነትን ላላብሰውና – Negative Energy ነው፡፡ ይህ አፍራሽ ወይም አሉታዊ ኃይል ከPositive Energy በተቃርኖ የቆመና ኃያላን ሀገራትንና ምርጥ የዓለም ዜጎችን (በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በቁንጅናና በውበትና በሥልጣን የታወቁትን) በመጠቀም ተፅዕኖውን በመላው Universe በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ብዙ ሰዎች ይህን መሰል ነገር ማመን ይቅርና መስማትም አይፈልጉም፡፡ ይህ ክፉ ኃይል ከሚያስከትለው ጉዳት ግን አያመልጡም፡፡ ለምሣሌ አሁን የምናየውን የዓለምን ሸፋፋና ወልጋዳ ቅርጽ ያስገኘው ይህ መጥፎ ኃይል እንጂ ፈጣሪ አይደለም፡፡ የSatainism እምነት አውሮፓንና አሜሪካንን እያጥለቀለቀና አብያተ ክርስቲያንን ወደ ሙዚየምነት፣ ካህትና ጳጳሣትን ወደ ዘማዊነትና አለሌነት፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ወደ ኢ-አማኒነትና ወደሶዶማዊነት እየለወጠ ባለበት በዚህ የርኩሳን መናፍስት የበላይነት ዘመን ድግምትና ጥንቆላን አላምንም ማለት በርግጥም በድግምትና በትብታብ ከመያዝ የሚተናነስ አይደለም- ሩቅ ሳንሄድ ሕወሓት እንኳን በአቅሟ ይህን ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ እንደበግ የምትነዳው የጥልቁ ገዢ ከሆነው ፀላዔ-ሠናያት ጋር የሚሻረኩት ጌቶቿ ከሚሰጧት ምክርና አጠቃላይ ድጋፍ በተጓዳኝ ከሱዳን፣ ከህንድና ከምዕራብ አፍሪካ በምታስመጣው አጋንንታዊ “ባርኮት”ም ጭምር እንደሆነ ብዙዎች ይገምታሉ፡፡ እንጂ የነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ማይማን ወሮበሎች ኃይልና ጉልበት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አጠቃላይ ኃይልና ጉልበት በልጦ አይደለም፡፡ ዘመኑ ለመተትና ለደንቃራ እጅጉን የተመቻቸ ነው፡፡

ይህ አፍራሽ ኃይል በተለይ ወጣቱን ክፍል በዳንኪራ፣ በዐመፀኛ የድብድብና ወሲባዊ ፊልሞች ፍቅር በማስገዛት፣ በፀረ አምላካዊ ፍናፍንት ተግባራት በማጥመድና ባህልንና ነባር እምነትን በማስተው የራሱ የነፍስ ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች ያደርጋል፡፡ እነዚህን ቃላት ወይም ሐረጋት ጉግል በማድረግ ተጨማሪ ግንዛቤ ማግኘት እንደሚቻል ልጠቁምና ወደተነሳሁበት ላምራ፡፡ (Luciferianism Satanism, Illuminati, The New World Order, Knights Templar, Skull and Bone, satanic symbols, Church of Satan, Anton Szandor LaVey, Secret Societies and their Influence in the 20th Century,….)

ኃይሌ ገ/ሥላሤ ምን አለ? በጠንቋይ አላምንም አለ ልበል? አይልም አይባልም፡፡ ካለ ግን ከመሣቄ በፊት ጥርሴን በደምብ ወደምነቀስበት ቦታ ሄጄ መነቀስ ሊኖርብኝ ነው፡፡ እንዲያውም በቅርብ የማውቀው መሠረት የሚባል ምድረ አትሌትና ነጋዴ እንዲሁም አርቲስትና ሙዚቀኛ የሚርመሰመስበት ደብተራ ስላለ ወደርሱ ሄጄ ጥሩ ጥርስ ነቃሽ እንዲጠቁመኝ አደርጋለሁ፡፡ ኃይሌና መሠረት ደግሞ ጓደኛሞች መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ እናም ኃይሌ ጥንቆላና መተት እንደማይሠሩ ከመሰከረ ሩጫ ማቆሙንና ጫማውን መስቀሉን እርግጠኛ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ዓለም እንዲህ ናት – የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ዜጎች በበዙበት ምድር ላይ የማንሰማው ታሪክ የለም፡፡

ብዙ ሰዎች ለችግራቸው መፍትሔ የሚያመጡ እየመሰላቸው የማያደርጉት ነገር የማይዱበትም ሥፍራ የለም፡፡ አዲስ ጠበል ፈለቀ ከተባለ መተራመስ ነው፤ አዲስ ጠንቋይ መጣ ከተባለ መተረማመስ ነው፤ መጣፍ ገላጭ ደብተራ እዚህ ቦታ መጣ ከተባለ መርመስመስ ነው፤ የቡና ሥኒ ዝቃጭ አተላ ተርጓሚ፣ የጅ መዳፍና የከብት ሞራ አንባቢ፣ ቅጠል በጣሽ፣ ሥራ-ሥር ማሽ፣ ኮከብና ክፍል ቆጣሪ፣ ዐውደ ነገሥት ገላጭ …  እዚህ ቦታ አለ ከተባለ ቦታው ላይ ጠጠር ቢጣል ማረፊያ እስኪታጣ በሰው ይጨናነቃል፡፡ በመሪር አገዛዝ፣ በማይምነትና በላሸቀ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖር ዜጋ ለዚህ ዓይነቱ አስነዋሪ ተግባር ተጋላጭ መሆኑን በተግባር እያየን ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከዚህ ሁሉ ባለጉዳይ አብዛኛው ሰውን ለመጉዳት ወይም በሚጠላው ላይ ለማስተብተብ እንጂ ራሱ እንዲያልፍለት ደጅ የሚጠናው ጥቂት መሆኑ ነው፡፡ የኛ ማኅበረሰብ እንግዲህ እንዲህ ነው – ዱሮም አሁንም፡፡ ከዚህ ልማዳዊ ድርጊት ነፃ የሆነ ሰው ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ የሉም ማለት እንዳልሆነ ግን መረዳት ይገባል፡፡ በነገሩ ባለማመን፣ በእግዚአብሔር ብቻ በመመካት፣ የትኛው ጠንቋይ ወይ ደብተራ በየት ቦታ እንደሚገኝ መረጃ በማጣት፣ ለመሄድ ገንዘብ ባለማግኘትና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተነሣ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ወደነዚህ ሥፍራዎች ላይሄዱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ በጠበሎች ፈዋሽነት አምናለሁ፡፡ እምነት ካለህ የቤትህም ውኃ በጸሎት ኃይል ጠበል ሆኖ ይፈውስሃል፡፡ በአንዳንድ ቦታ እንደሚሰማው ያለ የሁለት ጌቶች ባሪያ የሆነ አጭበርባሪና ሌባ አጥማቂ ተብዬ ሳያስፈልግህ በእምነትህ ብቻ ትድናለህ፡፡ ድኅነትን የሚሻ የኀሊናና የመንፈስ ስብራት ወይም የአእምሮና  የአካል ጉዳት ካለብህ አሁኑኑ ሞክረውና ውጤቱን ታየዋለህ፡፡

በተረፈ ወያኔን ጨምሮ እስከ አሜሪካን ቤተ መንግሥት ድረስ ጥንቆላና መተት አለ፡፡ የአፍሪካም ሆኑ የሌሎች ሀገራት መንግሥታት እንደሚያስጠነቁሉና ጠንቋዮችን እንደሚቀልቡ በስፋት ይነገርላቸዋል፡፡ የዐዋጁን በጆሮ እንዳትሉኝ እንጂ ምድረ የአዲስ አበባ ሀብታምና አትሌት ሁሉ በየጠንቋዩና በየደብተራው ቤት እንደሚያፈነድስና ለግብር ሲባል ከብዙ ብር ጀምሮ እስከሰው ዕርድ ድረስ ጭዳ እንደሚያስገባ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በእያንዳንዱ ወፍጮ ቤት፣ በእያንዳንዱ ፎቅና ፋብሪካ፣ በእያንዳንዱ ሆቴልና የንግድ ተቋም ግርጌ የተሰዋውን የከብትና የሰው ደም እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ከዚህ ሃሜት የፀዱ የሉም ማለት እንደማይቻል ግን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ ከሰይጣንና የርሱ አገልጋይ ከሆኑ የግልና የመንግሥት ተብዬው ሓወሓት ሰዎች ጋር ባልተስተካከለ የጨዋታ ሜዳ በመታገል መከራቸውን እያዩ በንጹሕ ላባቸውና ወዛቸው የሚያልፍላቸው ጥቂት ወገኖች መኖራቸው አይካድም፡፡ አብዛኛው ግን “ከእያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ አንድ ወንጀል አለ” የሚለውን የቆዬ ብሂል በሚያረጋግጥ መልኩ በብዙ ወንጀሎች የተተበተበና መጨረሻውም የማያምር የሰይጣን ሎሌ ነው፡፡ እንደክርስቲያን ልናገር ነውና ይቅርታ –  በሰይጣን ዝና ሊመጣ ይችላል፤ በሰይጣን ሀብት ሊመጣ ይችላል፤ በሰይጣን ሥልጣን ሊመጣ ይችላል፤ ተፈቅዶለታልም፡፡ አጅሬ ያከበሩትን ያከብራል፤ የወደዱትን ይወዳል፡፡ የመጨረሻውን ዕድላቸውን ግን ከእርሱው ጋር ያቆራኘዋል – ንስሃ ካልገቡና በክርስቶስ ደም ካልታጠቡ በስተቀር፡፡ ግን ግን ሰይጣን ጥሩ ድስት ይሠራል እንጂ ክዳኑን(መግላሊቱን) እንደማይሠራ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል፡፡ የዛሬ ማማር ለነገ መጥፋት ከዳረገ ደግሞ ማማር ባፍንጫ ይውጣ፡፡የምንገኝበት ዘመን እጅግ አወዛጋቢና ግራ አጋቢ ነው፡፡ የፈተናዎች አበዛዝ ደግሞ አይወራ፡፡ …

ስለዚህ እነ ኃይሌ ለማያቃቸው ይታጠኑ፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ያውቃል፡፡ ከእንትና ቤት በአሳቻ ሰዓት ስወጣ በእግረኛ ፖሊስ በመታየቴ ለአፍ ማዘጊያ  40 ብር ወተፍ አድርጌ የሄድኩት እኔ አይደለሁም – 40 ብርም ገንዘብ ሆኖ፡፡ ያን ሰው አውቀዋለሁ፡፡

የኮተቤ መሣለሚያው ደፍተራ አያ እንቶኔ ከቻሉ በዚህ ጸሐፊ ላይ ይድገሙና ጥበባቸውን ያሳዩ – መፈታተኔ አይደለም፡፡ ሰይጣን አይሠራም እያልኩም አይደለም፡፡ በደምብ ይሠራል፡፡ ግን አለኝታና ጋሻህ የጽርሓ አርያሙ ኅያው እግዚአብሔር ከሆነ ማንምና ምንም አይነካህም፡፡ እንጂ እነእስራኤል ዳንሳና ምድረ ፓስተር ነኝ ባይ ሁሉ አፍራሽ ዲያብሎሳዊ ኃይል በውድ ዋጋ (በነፍሱ ጭምር!) እየገዛ ምድረ አበሻን በደረቁ እየላጨ እንደሆነ አንዱ ባንዱ ላይ እየተደራረቡ ወደ አየር በሚወጡ የሳተላይት የቲቪ ቻናሎች እየተከታተልን ነው፡፡ ዘመኑ ነው ብለን ግን ብዙም አልተደናገጥንም፡፡  ኃይሌ ግን ምን አለ? እውነቱን ነው – ሰይጣን እጁ ዐመድ አፋሽ መሆኑን እርሱም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለማንኛውም ዝምታም አንዳንዴ ጥሩ ነው፤ ከወርቅም በላይ፡፡ ዶሮ አርቃ ስትቆፍር የምታወጣው ነገር አለ….

ያን በጌጤ ዋሚ ላይ የተሠራ ፊልም አይቸዋለሁ፡፡ ገርሞኛል፡፡ “እርሷ ፈቅዳ ይሆን ገመናዋ እንዲህ በአደባባይ እንደ እህል የተሰጣው?” ብዬም ራሴን ጠይቄያለሁ፡፡ መምህር ግርማ ስለሚባሉት አጥማቂም ከዱሮ ጀምሮ ብዙ እሰማለሁ፡፡ ዘመናችን የመጨረሻው ዘመን ዋዜማ እንደመሆኑ ግን ስለእርሳቸው ማንነትና የኃይል ምንጭ ምሥጢር ብዙም አልተጨነቅሁም – ፈጽሞ አልተጨነቅሁም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ መፍረድ ቀላል ነው፡፡ መፍረድ ከባድ ነው፡፡ የቀላልና ከባድ ነገሮች መወሳሰብ ደግሞ አያዎነቱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ነገሮች ሲጠጥሩብህ የዕንቆቅልሹን ፍቺ ለጊዜ መስጠት ነው፡፡ በውል በማያውቁት ጉዳይ ዘው ብሎ ገብቶ “ይህ እንዲህ ነው፤ ያ እንዲያ ነው” ከተባለ አላዋቂነትን ወይም ፍርደ ገምድልነትን ሊጠቁም ይችላልና በፍርድ ሂደት ጠንቀቅ ማለቱ አግባብ ይመስለኛል፡፡

እንደአጠቃላይ ግን አንዳንድ ክርስቶሳዊ እውነቶችን መጠቆም ይቻላል፡፡ ይህን ጥቆማየን ከእገሌ ወይ ከእንትና ጋር ማያያዝ አልፈልግም፡፡ በምሽት ክበብ ልብስ ዝንጥ ብለው በየኪዮስክ መሰል የኪራይ “ቤተ ክርስቲያናቸው” ውስጥ የተጨነቁ ወገኖችን በመሰብሰብ “ሃሌ ሉያ! በቅርቡ ዱባይ እንደምትሄጅ የሱስ ነግሮኛል!” የሚሉትን እንኳን አሁን እዚህ ላይ ማስታወስ አልሻም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቱን ብቻ ላስታውስ፡፡ እናም ክርስቶስ እንደሰው በምድር ይመላለስ በነበረበት ወቅት “ጓደኞቹ”ና አብሯቸው ይውልና ያመሽ ያድርም የነበሩት ፍጹም ድሆችና አንዳች ፈውስ የሚያስፈልጋቸው ምንዱባን ነበሩ፡፡ እንዲያውም ክርስቶስ ራሱ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ህሙማን እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ይል ነበር፡፡ ስለዚህም ከሀብታሞችና ባለፀጋዎች ጋር አንድም ኅብረት አልነበረውም፡፡ በስፋት የሚነገርለት “ሀብታም መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል” የሚለው ብሂል የሚጠቁመውም የሀብታምነትን ቁልፍ ምሥጢር ስለሚያውቀውና ከዚያ ዓይነቱ መንገድም እንድርቅ ለማስተማር ፈልጎ ነው፡፡ ለተዓምራዊ የፈውስና ዲያብሎስን ከሰዎች ገስጾ የማስወጣት ተግባሩም አምስት ሣንቲም አያስከፍልም፡፡ ክርስቶስ ፀጋውን በገንዘብ አልሸጠም፡፡ በገንዘብ የሚሸጥ መለኮታዊ ፀጋ የለም፡፡ “በነፃ እንደሰጠኋችሁ በነፃ ስጡ” አለ እንጂ “በፀጋየ ገንዘብ እፈሱ፤ የማዳን ተዓምራቴን ተጠቅማችሁ በሰዎች ዘንድ ክብርንና ሞገስን ተጎናጸፉ፣ በስሜ አጋንንትን እያወስወጣችሁ ፎቅና ሊሞዝን ግዙ፣ በዓለምም ተንቀባረሩ፣ ዓለም የምታመርተውን መብልና መጠጥ – ሴትና ብልጭልጭ ነገር ሁሉ ተቆጣጠሩ…” ያለበት አንድም ትዕዛዝም ሆነ መመርያ የለም፡፡ ክርስቶስ ገንዘብ ቢያስከፍል ኖሮ ለአራት ቀናት ሞቶ የተነሣው አልዓዛር፣ ለአሠርት ዓመታት ደም ይፈሳት የነበረችዋና የጨርቁን ጠርዝ ነክታ የተፈወሰችው መበለት፣ ከሞት የተነሳችው የመቶ አለቃው ልጅ….. ስንትና ስንት ሽህና ሚሊዮን ብር ይከፍሉ ነበር? ከዚህና ከሌሎቹም አሁን ያልጠቀስኳቸው ክርስቶሳዊ አስተምህሮዎች ተነስተን የዘመናችንን “አጥማቂዎች፣ ፋዋሾችና መሲሖች”ን ስንቃኝ የትኞቹ ፈተናውን እንደሚያልፉ መገመት አይቸግረንም፡፡ ደግሞም በመጨረሻው ዘመን “የተመረጡትን” ሳይቀር የሚያስቱ ብዙ ድንቃ ድንቅ ተዓምራት በአጋንንት አማካይነት እንደሚከናወኑና ብዙዎችም እንደሚስቱ ቀድሞ ተነግሯል – አሁን በየቦታው የምናያቸውን መንገድ ጠራጊዎቹን ታናናሽ መሲሆች ተክቶ የሚመጣው ዋናው ሃሣዊ መሲሕ ሲመጣ “ከሰማይ እሳት ያዘንባል”ም እኮ ተብሏል፡፡ ጊዜዋ ስትደርስ አሁን በዓለም ከምናያቸው ተዓምራት ባለፈ ብዙ ዕፁብ ድንቅ የሚያስብሉ ትንግርቶች እናያለንና አሁን በምናያው እስከዚህም አንደነቅ፡፡ ለነገሩ ምን አገባን? እርሱ ራሱ በመንበሩ ተቀምጦ እንዲህ ሲያላግጡበት አስችሎት ዝም ያለ ጌታ እያለ የኛ መንጨርጨር ከምን የመጣ ነው? “ቅና ያለው በጎረቤት ፓስተር ይቀናል” አሉ….


13 
 እንዲህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አታላይ ሠራተኞች ናቸውና።+ 14  ይህም ምንም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣልና።+ 15  ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም። ሆኖም ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል።

ቆሮንቶስ 11፡ 13 – 15

እግዚአብሔር ሕዝባችንንና ሀገራችንን በፀጋው ይባርክ! ከሐሣይ መሢሖችም ወጥመድ ይጠብቀን! አሜን፡፡

Loading...

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.