ኢትዮጵያ ዉስጥ አብላጫ (majority) ብሔረሰብ አለ ወይ?

ዛርጉላ ገረሴ

በየድህረ ገጾች ላይ በየጊዜዉ የሚወጡ አንዳንድ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የኦሮሞ ብሔረሰብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ሲነጻጸር አብላጫዉ ብሔረሰብ (51%) እንደሆነ ተደርጎ ነዉ። ይህንንም ጽሁፍ የሚጽፉት ከኦሮሞ ብሔረሰብ የመጡ ብሔረሰበኞች ወንድሞቻችንና እህቶቻናችን ናቸዉ። ይህም አመለካከት በኦሮሞ ፖለቲከኞች የተጀመረና በቅጡ ሳይጤን ላይ ላዩን እተንጓለለ ለብዙ አመታት የተናፈሰ በመሆኑ አዲስ መጤ የሆኑ ኦሮሞ ፖለቲከኞችም እንደ እዉነኛና ተጨባጭ ነገር አድርገዉ በመዉሰድ እያናፈሱት ያሉ ለመሆናቸዉ በየጊዜዉ ከሚወጡት ስነ ጽሁፎች ለመረዳት ይቻላል። ይህንንም ስህተት ወደ ዉይይት ለማምጣት የሚጥሩትን ግለሰቦች ማብጠልጠል እንደ ልማድ ሆኖ መታየቱ እንዲሁ በየጊዜዉ ከሚወቱት ስነ ጽሁፎች ወይም ዩቲዩቦች መገንዘብ ይቻላል። እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ግንዛቤ አሳሳች ወደ ሆነ ጎዳና የሚያመራና በኢትዮጵያዉያን መካከል አለመግባባትን ከሚፈጥሩ ሁኔታዎች አንዱ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት ነዉ ይህንን መጣጥፍ ለዉይይት ለማቅረብ የፈለግሁት።

አብላጫ (majority) የሚለዉ ቃል የሚያመለክተዉ ከመቶ እጅ ሀምሳ አንዱን እጅ (51%) እንጂ ሌላ አይደለም። ከዚህም መርሀዊ አግባብነት በመነሳት የኦሮሞን ህዝብ ቁጥር ስንመለከት ልናተኩርና እንደ አማራጭ መረጃ አድርገን ልንወስድ የሚገባን በኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረጉትን የህዝብ ቆጠራዎች ነዉ እንጂ ምንም ቆጠራ ሳያካሂዱ በይመስለኛል ዝም ብለዉ አብላጫዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ኦሮሞ ነዉ እያሉ የሚያካሂዱትን አመለካከት አይደለም ። በአጼ ሀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት እ. አ. አ. በ1972 የተደረገ የህዝብ ቆጠራ እንዲሁም በደርግና በወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመነ መንግስታት የተደረጉት የህዝብ ቆጠራዎች እንከን ቢኖራቸዉም እንዳቸዉም የኦሮሞን ህዝብ ቁጥር በአብላጫነት የፈረጀ የለም። እነዚህም ቆጠራዎች የተካሄዱት በዉጭ አገር መንግስታት አለም አቀፍ እርዳታ ነዉ። ሆኖም ከኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ከአስራ ዘጠኝ መቶ ሰባዎቹ ጀምሮ የምሰማዉ የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር አርባ በመቶ (40%) እንደሆነና በተለይም ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ አብላጫ (majority) እንደሆነ ነዉ። አርባ ፐርሰንት ደግሞ አብላጫ (majority) አይደለም። እ. አ. አ. በ2007 ዓ. ም. በወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመነ መንግስት የተካሄደዉ የህዝብ ቆጠራ የሚያመለክተዉ ኦሮሞ 34.69%፣ አማራ 26.89%፣ ትግራይ 6.7%፣ ሶማሊያ 6.20% እንደሆነ ነዉ።

የኦሮሞ ብሔረተኛ ፖለቲከኞች ግን አብላጫዉ ብሔረሰብ ኦሮሞ ስለሆነ አስተዳደሩም ሆነ ማንኛዉም የበላይነት ስልጣን ለኦሮሞ ህዝብ ይገባዋል የሚል ጭፍን አመለካከት በማንጸባረቃቸዉ ብዙ ወጣት ኦሮሞዎች በዚህ ሀሳብ ተዉጠዋል። አንዳንዶቹማ የፈለገዉ መረጃ ቢቀርብ ፍንክች እንደማይሉ ነዉ የምረዳዉ። በዚህ አመለካከት ወያኔዎች እንደሚሳለቁ አልጠራጠርም። ምናልባትም ከበስተጀርባዉ የወያኔ እጅ ይኖር ይሆን የሚል ጥርጣሬ ማሳደሩ አይቀርም። ይህ ማለት ደግሞ ሁሉም ኦሮሞ አንድ አይነት አመለካከት አለዉ ማለት አይደለም። ለኢትዮጵያ አጀንዳ የሚሟገቱና ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ መገኘት የሚታገሉ ኦሮሞዎች ትኩረታቸዉ መሰረታዊ የዲሞክራሲ ጥያቄ መፍትሄ እንደሚያስገኝ አበክረዉ እንደሚያመለክቱ በየጊዝዉ ድህረ ገጾች ላይ ከሚያወጧቸዉ መጣጥፎች የምቀስመዉ ትምህርት ነዉ።

ይህ አብላጫ (majority) የሚለዉ ቃል ትልቁ ወይም አንጋፋ ከሚለዉ ቃል ጋር በትርጉም ተምታቶ ነዉ እንዳልል የኦሮሞ ብሔረተኛ ፖለቲከኞች ይህንን አይረዱትም ወይም ዉዥንብር ዉስጥ ገብተዋል ለማለት ይቅርና ጨርሶ እንኳን የማላስበዉ ነገር ነዉ። በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ኦሮሞ ትልቅ ወይም አንጋፋ ብሔረሰብ ከመሆን በስተቀር አብላጫ (majority) ሆኖ አያዉቅም፤ አይደለምም። አብላጫ (majority) ብሄረሰብ ለመሆንም እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ነገር አይደለም። እኛ አብላጫዎቹ ነንና እኛ መግዛት አለብን፣ የእኛ ቋንቋ የአገሪቱ ኦፊሴል ቋንቋ መሆን አለበት የሚለዉ አባባል የትግል ስትራቴጂ ተደርጎ ተወስዶ ይሁን አይሁን አላዉቅም። ሆኖም ግን እንደዚህ አይነቱ ስትራቴጂ ይሰራል ተብሎ ተገምቶ ተግባራዊ ሆኖ ከሆነ ብዙ ስንክሳር እንደሚገጥመዉ ሊታሰብበት ይገባ ነበር እላለሁ። በብዙ አገሮች ዉስጥ ያሉ አብላጫ ብሄረሰቦች በአናሳ ብሄረሰቦች ይገዛሉ፤ ይስተዳደራሉና የአናሳ ብሄረሰብ ገዥዎች ስልጣንን ዝም ብለዉ በህዝብ ብልጫ ምክንያት ለአብላጫዉ ብሄረሰብ አያስረክቡም። አብላጫዉ ብሄረሰብ ገዢ በሆነበት አገር ሁሉ ዲሞክሳሪያዊ አስተዳደር አለ ማለት አይደለም። መሰረታዊ የሆኑ የዲሞክራሲ አስተዳደር መስፈርቶችን ያላሟላ አስተዳደር (አብላጫም ሆነ አናሳ ብሄረሰብ) ምን ጊዜም ቢሆን አስተዳደራዊ ፍትህ ለህዝብ አያጎናጽፍም። በታሪክ እንደታየዉ ብዙ የአስተዳደር መዛባቶች በብሄር ንቅናቄዎችና አስተዳደሮች ዉስጥ ታይተዋልና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ያልተቋቋሙ የብሄር ንቅናቄዎች ሀቀኛ አስተዳደር ለህዝብ ያጎናጽፋሉ ብሎ በጭፍን ማመን የፖለቲካ ባይተዋሪነት ይመስለኛል። ምክንያቱም በብሄረተኝነት ንቅናቄዎችና የስልጣን አስተዳደሮች ብዙ ምግባረ ብሉሽነቶች፣ የስልጣን ጥመኝነትና የሀገርን ጥቅም ለግል ጥቅም ማዋል ታይተዋልና። ከኤርትራ ነጻ መዉጣትና ከሻቢያ አምባገነንነት ትምህርት መቅሰም የማይችል ፖለቲከኛ አለ ብትሉኝ ከዚህች አለም ርቆ የሚኖር ባይተዋር ነዉ እላለሁ።

የኦሮሞ ብሔረሰብ ታላቁና አንጋፋዉ ብሔረሰብ እንጂ አብላጫዉ ብሔረሰብ አይደለም። ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ታሪከ ዉስጥ ታላቅ ስፍራና አኩሪ ታሪክ አላቸዉ። ኦሮሞዎች የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በደማቸዉና በአጥንታቸዉ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረዉ ገንብተዋል። የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያላካተተ የብሄረሰብ ጥያቄ ዘላቂ ፍትህ ያመጣል ብሎ ማሰብ ላሞች ካልዋሉበት ቦታ ኩበት መልቀም እንደሚሆን ይመስለኛል። የአፍሪካ አገሮችን ከቅኝ ገዢዎች አዉታር ለማስለቀቅ የተደረጉትን ብሄራዊ ትግሎች ማጤኑ ምናልባት ብዙ ሃሳብ ሊሰጠን ይችላል። አገር ወዳድ የአፍሪካ መሪዎች ጸረ-ቅኝ አገዛዝ የብሄር ንቅናቄን ከለላ በማድረግ ትግል አካሂደዉ ነጻ ከወጡ በሗላ በብዙ ምግባረ ብሉሹነት ተዘፍቀዉ ለስልጣን ያበቃቸዉን ህዝብ መልሰዉ አሰቃይተዋል፤ አዋርደዋል። አብዛኛዎቹም እድሜ ልክ በስልጣን ላይ ቆይተዋል። እናም አብላጫ ነን ማለቱ ብቻ ከፍትህ አንጻር ሲታይ የትም አያደርስም። “አለባብሰዉ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” አይነት የፖለቲካ ትርኢቶች በተለይም በአፍሪካ አህጉር በብዛት ታይተዋልና። የዲሞክራሲንና የግልሰብ ነጻነትን መሰረት ያላደረገ ትግል ሁል ጊዜ ለሰፊዉ ህዝብ ዘለቄታዊ የሆነ ፍትህና ርትእን ያመጣል ብሎ ማሰክ የዋህነት ይመስለኛል።

በኢትዮጵያ አንድ ዜጋ አንድ ድምጽ ብቻ ኖሮት የፓርላሜንታሪ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ቢሰፍን እንኳ ኦሮሞዎች ሁል ጊዜ በፓርላማ ዉስጥ አናሳዎች ሆነዉ ሊቀሩ እንደሚችሉ መገንዘብ አለባቸዉ። ይህም የሚሆነዉ አማራዉ የኢትዮጵያን አጀንዳ ለማራመድ ከሌሎች አናሳ ብሔረሰቦች ጋራ የጋራ ግንባር ፈጥሮ አብላጫዉን የፓርላማ መቀመጫዎች ከያዘ ኦሮሞዎች ሁል ጊዜ አናሳ ድምጽ እንዲኖራቸዉ ማድረግ የሚቻል መሆኑን እንደሚረዱት አልጠራጠርም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሊከሰት አይችልም ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም ማለትም የኦሮሞ ፖለቲከኞች የብሔረሰብ ፖለቲካቸዉን ሙጥኝ ብለዉ ካራመዱት። የኢትዮጵያን አጀንዳ የሚያራምድ ፖለቲከኛ ግለሰብ ወይም ብሔረሰብ ብቻ ነዉ የሌሎች ብሔረሰቦችን ወይም ግለሰቦችን እገዛ ማግኝት የሚችለዉ እንጂ ለራሱ ብቻ የሚያስብ ብሔረሰብ ወይም ግለሰብ አይደለም። ፓለቲካም ቢሆን ያልዘሩት አይበቅልም እንደሚሉት አይነት ነገር ነዉ። የፖለቲካ አጋርነት በኢትዮጵያ አጀንዳ ዙሪያ የሚገነባ እንጂ በተናጠል ለሚደረግ ትግል አጋርነት ከተፍ አይልም። የአደባባይ እዉነታም ይመስለኛል።

በኦሮሚያ ክልል ቁቤ (የላቲን ፊደል) መጻፊያ ፊደል እንዲሆን ወያኔዎች እንደገቡ ካደረጉት ቅድሚያ ተግባሮች አንዱ እንደሆነ ሁላችንም የምናስታዉሰዉ ነገር ነዉ። ይህም አማራዎችን ለመጉዳትና የአማራን ተጽእኖ ለማዳከም ተብሎ ወያኔዎች ከወሰዱት ቀደምት እርምጃዎች አንዱ ነዉ። ወያኔዎች አማርኛን የመንግስት ቋንቋ አድርገዉ እየሰሩ በተለይ የኦሮሞ ልጆች አማርኛ እንዳይማሩና እንደ ጠላት ቋንቋ አድርገዉ እንዲወስዱ ያላደረጉት ነገር የለም። ወያኔዎች ስልጣን ሲይዙ ትምህርት ቤት የገቡ ህጻናት ብዙዎቹ ባሁኑ ወቅት አማርኛ ስለማይናገሩ መስራት የሚችሉት በኦሮሚያ ክልል ብቻ እንዲሆን አድርጓቸዋል። የወያኔ ተለጣፊ ድርጅት የሆነዉ የኦህዴድ መሪዎች ልጆች ግን አማርኛ እንዲማሩና እዲናገሩ ተደርጎ ነዉ ያደጉት። ከብዙ አመታት በፊት የአማርኛ ቋንቋ መናገር የማይችል ለፓርላማ አባልነት ሊወዳደር አይችልም፤ ቢመረጥም እንኳ የፓርላማ አባል መሆን እንደማይችል ወያኔዎች ሲገልጹ ምንኛ የፖለቲካ ቧልት እንደሆነ የታዘብኩት ነገር ነዉ። ኦሮምኛ በህብራይስት ወይም በአረብ ወይም በስላቪክ ወይም በአርመን ፊደል ስለተጻፈ እድገት ያመጣል በግእዝ ፊደል ከሚጻፍ ይልቅ ብሎ ማሰብ ምንኛ አሳፋሪ እንደሚሆን አንባብያን እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። ፊደል ብቻዉን እድገት የሚያመጣ ነገር ቢሆን ኖሮ ይሄኔ እኛ የት በደረስን ነበር። ስንቶቹስ የአፍሪካ አገሮች በላቲን ፊደል ይጠቀማሉ? ስለተጠቀሙ ሰለጠኑ ማለት ነዉ ወይ? ግእዝ ፊደል ያሳፍራል ወይ? የራሳችን ፊደል ያለን መሆኑ አያኮራንም እንዴ? ወይስ የላቲን ፊደል ነጻ አዉጪ ፊደል ነዉና ነዉ? እናም ፊደል ወሳኝ ነበር ማለት ነዉ ወይ የኦሮሞን ቋንቋ ለማሳደግ ወይስ በአማርኛ ቋንቋና በአማራዎች ላይ የነበረዉን ጥላቻ ለማርካት የተደረገ የወያኔዎች ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ነዉ? መልሱን ለአንባቢያን እተወዋለሁ።

የኦሮሞ ህዝብ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ደካማ ጎንና በወያኔ ዘረኛና መሰሪ በሆነዉ የአስተዳደር ፖሊሲ ብዙ ጉዳት ደርሶበታል። የጎጠኝነት ፖለቲካ የኦሮሞንም ሆነ የሌላ ብሔረሰብን ህዝብ የትም አያደርስም። የኦሮሞ ብሔረተኛ ፖለቲከኞች “የኦሮሞ ህዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አብላጫዉ (majority) ብሔረሰብ ነዉ” እያሉ የተያያዙትን የትግል ስትራቴጂ እንደገና ቢያጤኑትና የኢትዮጵያን አጀንዳ ከግምት ወስደዉ የኦሮሞ ህዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አንድ ሆኖ ወያኔዎችን ማስወገድ የሚቻልበትን መንገድ ቢቀይሱ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እንደሚያቀርበዉ አልጠራጠርም። የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ አንጋፋ ወይም ትልቁ ብሄረሰብ ከመሆን በስተቀር አብላጫ (majority) ብሄረሰብ ሆኖ እስከ ዛሬ ድረስ አያዉቅም። ይህንንም እዉነታ የሚገነዘቡና የኢትዮጵያን አጀንዳ የሚያራምዱ ብዙ ኦሮሞዎች እንዳሉ አሳምሬ አዉቃለሁ። የአብላጫ (majority) ፖለቲካ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ብሄረሰቦች ባሉባቸዉ አገሮች ሁሉ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታያሉ። ሆኖም ግን የፖለቲካ መፍትሄ እንኳ አስገኝተዉ አያዉቁም። ወያኔዎች ባዘጋጁት የፖለቲካ ቲያትር መጨናበሱ የወያኔዎችን እድሜ ከማራዘም በስተቀር ምንም ፋይዳአያስገኝም። “ድር ቢያብር አንበሳን ያስር” የሚለዉ ተረት ትምህርት ሊሰጠን ይገባልና ቢታሰብበት ደግሞ የሁላችንንም ትግል ፍሬ ሊያስገኝ ይችላል። ይህም የትግል ስትራቴጂ ስኬታማ እንዲሆን ያለኝን ምኞት ስገልጽ ከእኔ የሚጠበቀዉን ሁሉ ያለ አንዳች ማመንታት ማድረግ እንዳለብኝ በመረዳት ነዉ። አንድነት ሀይል ነዉ!!!

ዛርጉላ ገረሴ

zargulagerese@yahoo.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.