የአርመን ቤተ ክርስቲያን ተምሳሌታዊ የፍትሕ ትግልና የኢትዮጵያ (ኪዳኔ ዓለማየሁ)

ኪዳኔ ዓለማየሁ

የአርመን ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ እርምጃ፤

በኒው ዮርክ ታይምስ (New York Times) እ.አ.አ. ግንቦት 19 ቀን 2015 በተዘገበው ዜና ቱርኮች ከ100 ዓመታት በፊት ስለ ዘረፉባት ንብረት የአርመን ቤተ ክርስቲያን በቱርክ መንግሥት ላይ በሐገሩ ውስጥ ክስ አቅርባለች። የቤተ ክርስቲያኗ መሪ፤ ቀዳማዊ አቡነ አረም (Aram I) በሰጡት ቃለ መጠይቅ መሠረት በደቡብ ቱርክ በአዳና (Adana) አውራጃ የሚገኘው በ1293 የተቋቋመው የአርመን ክርስቲያኖች ማእከል የነበረው ቤተ ክርስቲያንና ገዳም በቱርኮች ነጠቃ ተይዞ ስለሚገኝ በቱርክ ሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ክሱ ቀርቧል። ያ የአርመኖች ቤተ ክርስቲያን ማእከል በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ በኦቶማን ቱርኮች ከተመዘበሩት ብዙ ንብረቶች አንደኛው እንደ ነበር ገልጸዋል። የተረፉት አርመኖች እ.አ.አ. በ 1930 የቤተ ክርስቲያናቸውን ቤተ ክሕነት ማእከል አንተሊያስ (Antelias) ወደምትባል የሌባኖን ከተማ አዛውረው እንደ ነበር ተገልጿል።

በኒው ዮርክ ታይምስ* እንደ ተገለጸው የ68 ዓመት እድሜው አቡነ አረም በቱርክ መንግሥት ላይ የተወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ከ30 የሕግ ሊቆች ጋር በመመካከር መሆኑን አረጋግጠዋል። በተጨማሪም የአርመን ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ያተኮረችው ቱርኮች በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ቢሆንም ባሁኑ ጊዜ ለአርመኖች ስለሚያስፈልገው ካሣ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ለዚህም ሒደት የመጀመሪያው የንብረት ካሣ ጥያቄ ከላይ በተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያን ንብረት ላይ ሲሆን ለወደፊቱ በሌሎች በቱርኮች በወደሙና በተዘረፉ ቤተ ክርስቲያኖች እንዲሁም የግል ቤቶችና ንብረቶች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልጸዋል።

*”Aram I…..said he had decided to proceed with a lawsuit after having consulted with 30 legal experts, including some from Turkey. While the church’s efforts to achieve an international acknowledgment of the genocide were important, “after 100 years, I thought it was high time that we put the emphasis on reparation,” he said.

ቱርኮች አርመኖች ላይ ስለ ፈጸሙት ወንጀልና ስለ ፍትሕ ትግሉ ውጤት፤

በአርመኖች መግለጫዎች በይፋ በታተተው መሠረት እ.አ.አ. በ1915 የኦቶማን ቱርኮች በአርመኖች ላይ በፈጸሙት የጦር ወንጀል 1.5 ሚሊዮን አርመኖች ተጨፍጭፈዋል፤ እጅግ ብዙ አርመኖችም ለስደት ተዳርገዋል። ከአርመኖቹ ስደተኞች ውስጥ 40 ቤተሰቦች በኢትዮጵያ ተስተናግደው እንደ ነበር የታወቀ ነው። ምንም እንኳ የቱርክ መንግሥት የወንጀል አኃዙን የተጋነነ ነው ቢልም ቱርኮች በአርመኖች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ መሆኑን የአውሮፓ ምክር ቤትና የቫቲካኑ ቀዳማዊ ፖፕ ፍራንሲስ እውቅና ሰጥተውላቸው የአርመኖችን የ100 ዓመት የፍትሕ ትግል ፍሬያማ አድርገውላቸዋል።

ላለፉት 100 ዓመታት የአርመኖች የፍትሕ ትግል በቱርኮች አማካኝነት ስለ ተፈጸመባቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፍ እውቅና ለማስገኘት ብቻ ሲሆን አሁን ደግሞ፤ በአርመን ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ የተጀመረው የካሣ ጥያቄ ጉዳይ ተጀምሯል ማለት ነው። ይህ እንቅስቃሴም በተመሳሳይ ሁኔታ በፋሺሽቶች አማካኝነት ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ለወደሙባት ለኢትዮጵያ ምሳሌነት ያለበት ሒደት ነው።

በኒውዮርክ ታይምስ በተዘገበው መሠረት የቱርኩ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እስካሁን ድረስ የሰጠው መልስ የለም። ለማንኛውም ከፍርድ ቤቱ ተገቢው ምላሽ ካልተገኘ በታዋቂው የማክጊል ዩኒቨርሲቲ (McGill University) ፕሮፌሰር (መምሕር)ና ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ የሕግ ሊቅ የሆኑት ፓያም አክሃቫን (Payam Akhavan) በአርመን ቤተ ክርስቲያን የቀረበውን ክስ የቱርኩ ፍርድ ቤት ውድቅ ካደረገው ጉዳዩን ወደ አውሮፓ ሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት

ሊያቀርበው ማቀዱን ገልጿል። በተጨማሪም ሌሎች አርመናዊ ምሑራን ለሐገራቸው ስለሚያሰፈልገው ካሣ ጠለቅ ያለ ጥናት አከናውነው ሰፊ ትንተና ያሰራጩ መሆኑን እ.አ.አ. ሚያዚያ 14 ቀን 2015 በወጣው የኒውዮርክ ታይምስ ተዘግቧል።

በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው የጦር ወንጀል የፍትሕ ትግል፤

እንደሚታወቀው፤ ፋሺሽት ኢጣልያ፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ እ.አ.አ. በ1935-41 አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ከመጨፍጨፋቸው በላይ፤ 2000 ቤተ ክርስቲያኖችን፤ 250 000 ቤቶችንና 14 ሚሊዮን እንስሳትን አውድመዋል። እንዲሁም መጠነ ሰፊ ንብረቶችን ዘርፈዋል። ከነዚሁ ውስጥ አሁንም ከ500 በላይ የሚቆጠሩ በቫቲካን ይዞታ የሚገኙ ሰነዶች አሉ። “ፀሀይ” የተሰኘች አውሮፕላንም በኢጣልያ አየር ኃይል ቤተ መዘክር ትገኛለች። ሌላም ብዙ የተዘረፈ ንብረት እንዳለ የታወቀ ነው።

ለተፈጸመባት አሰቃቂ ወንጀልና ዝርፊያ ኢትዮጵያ እስካሁን ያገኘችው ኢምንት የሆነ ቆቃ ግድብ የተሠራበት $25 ሚሊዮን እና በቅርቡ ከሮም፤ ኢጣልያ የተመለሰው የአክሱም ኃውልት ነው። ኢጣልያ ለሊቢያ $5 ቢሊዮን፤ ለዩጉዝላቪያ $125 ሚሊዮን፤ ለግሪክ ሐገር $105 ሚሊዮን እና ለሶቪየት ዩኒየን $100 ሚሊዮን ከከፈለችው ካሣ ጋር ሲወዳደር፤ በተለይ በነዚህ ሐገሮች ላይ የፈጸመችው ወንጀል ኢትዮጵያ ላይ ካከናወነችው ጋር ሲነጻጸር ለኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ ካሣ እንደሚገባት በፍትሕ ለሚያምን ሁሉ ግልጽ ነው። እጅግ ብዙ ንብረት የወደመባትና የተዘረፈባት እንዲሁም እነአቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል በተጨማሪም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከ2000 በላይ መነኮሳትና ምእመናን፤ ሌሎችም የተሰዉባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያገኘችው ካሣ የለም።

በኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው የጦር ወንጀል በመከናወን ላይ ያለው ትግል ከኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር የተሰማው አቤቱታና የዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) (www.globalallianceforethiopia.org) የተሰኘው ተቋም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመተባበር በመፈጸም ላይ ያለው እንቅስቃሴ ነው። ይህ ድርጅት እየተንቀሰቀሰባቸው ያሉት መሠረታዊ ዓላማዎችም የሚከተሉት ናቸው፤

(ሀ) የኢጣልያ መንግሥት ተገበዊን ካሣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲከፍል፤

(ለ) ከኢትዮጵያ የተዘረፉት በኢጣልያ መንግሥትና በቫቲካን ይዞታዎች የሚገኙት ንብረቶች ለኢትዮጵያ እንዲመለሱ፤

(ሐ) ቫቲካን ፋሺሽቶችን በመደገፏ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤

(መ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የፋሺሽት ጦር ወንጀል እንዲመዘግብ፤ እና (ሠ) ለፋሺሽቱ ወንጀለኛ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ በኢጣልያ፤ አፊሌ ከተማ በቅርቡ የተሠራው መታሰቢያ እንዲወገድ።

ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለማሳካት ድርጅቱ ለሚመለከታቸው ሁሉ፤ ማለትም፤ ለኢጣልያ  መንግሥት፤ ለቫቲካን፤ ለአውሮፓ አንድነት ድርጀት፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያና ለአሜሪካ መንግሥቶች በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ለዓለም ቤተ ክርስቲያኖች ምክር ቤት የአቤቱታ ደብዳቤዎች አቅርቧል።

በተጨማሪም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ግንዛቤና ድጋፍ እንዲገኝ 30 ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የኢጣልያ ፋሺሽቶች በሶስት ቀኖች ብቻ አዲስ አበባ 30 000 ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፉበትን የየካቲት 12ን

ዝክረ በዓል ምክንያት በማድረግ በጸሎት፤ በጉባኤዎች እና/ወይም በሰላማዊ ሰልፎች እንዲሳተፉ ክፍተኛ ጥረት አድርጓል። በዚህ ምክንያት ከተገኙት ተጨባጭ ውጤቶች መሀል፤ (ሀ) በቅርቡ በኢጣልያ፤ የላዚዮ አውራጃ ምክር ቤት የግራዚያኒ ኃውልት ስያሜ እንዲወገድ ያስተላለፈው ውሳኔ፤ (ለ) በኢትዮጵያ የካቶሊክ ካርዲናል ከሆኑት ከአቡነ ብርሃነየሱስ የተሰጠው ቀና መልስ፤ (ሐ)የአውሮፓ አንድነት ምክር ቤት ጉዳዩን የሚመለከተው መሆኑን በመግለጽ የሰጠው መልስ፤ እና (መ)በድርጅቱ ድረ- ገጽ (www.globalallianceforethiopia.org) ላይ የሚገኘው ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ የሚያመለክተው በ4500 ሰዎች የተፈረመው አቤቱታ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው።

እንዲሁም ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው ፍትሕ በበለጠ ጥልቀት ግንዛቤ እንዲገኝ ድርጅቱ በቅርቡ የሚከናወን አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እያዘጋጀ ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ጥረቶች የሚያበረታቱ ቢሆኑም፤ የፍትሕ ትግሉ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የታወቀ ነው። ለዚህም ተግባር የሚመለከታቸው መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶች መንፈሳዊዎቹም ጭምር፤ በዓለም ዙሪያ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የአርመን ቤተ ክርስቲያንን ምሳሌነት በመመልከት ለሐገር ክብርና ፍትሕ ጠንክረን የዘለቄታ ትግል ማከናወን ይጠበቅብናል።

ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን።

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.