ኢትዮጵያ፡ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ወረርሽኝ አዲስ ስጋት ፈጥሯል – ቢቢሲ

ከአስር ዓመት በፊት የበርካታ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈው፣ ልጆችን ያለወላጅ የስቀረው እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከተለው ኤች.አይ.ቪ ኤድስ አሁንም አንደ ወረርሽኝ ተከስቶ ስጋትን ፍጥሯል።

የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በሃገር ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት 1.18 በመቶ ደርሷል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ከአንድ በመቶ በላይ ከሆነ በአንድ ሃገር ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ወረርሸን ተከስቷል ይባላል።

በ1978 ዓ.ም በሁለት ሰዎች ደም ውስጥ ብቻ ይገኝ የነበረው ቫይረስ ዛሬ ላይ ከ700ሺ በላይ ዜጎች ደም ውስጥ ይገኛል ይላል፤ ከፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የተገኝው መረጃ።

የኤች አይ.ቪ.ኤድስ ወረርሽኝ ቀንሷል የሚለው በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት፤ በሽታው በድብቅ እንዲስፋፋ አስችሎታል።

በ2009 ዓ.ም ብቻ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ27ሺ በላይ ነው፤ ይላል የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጸ/ቤት።

ከፍተኛ ተጋላጭነት

የቫይረሱ ስርጭት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፤ የስርጭት መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸው ቦታቸው፣ አዲስ በሚመሰረቱ ከተሞች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ ነው ተብሏል።

በገጠር አካባቢ የሚኖሩና በአበባ እርሻ ሥራ ላይ ተቀጥረው ከሚሰሩ ሴቶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ-ሥጋ ግኑኝነት በመፈፀማቸው ፅንስ ለማቋረጥ ተዳርገዋል፤ ይላል የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት።

ለቫይረሱ ተጋላጭነት የፆታ፣ የሥራ አይነት እና የኑሮ ደረጃ አስተዋፅኦ አንደሚያደርጉ የጽ/ቤቱ መረጃ ያሳያል።

በሴቶች ላይ የለው የኢኮኖሚ እና ህብረተሰቡ የሚያደርስባቸው ጫና ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው መረጃው ያትታል። ከዚህም በተጨማሪ ሴተኛ አዳሪዎች ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው ጨምሯል።

ጫት ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች እና ማሳጅ ቤቶች ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ ሲሉ አቶ ክፍሌ ምትኩ የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሸ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ተናግረዋል።

ሃገሪቷ በ2030 የኤች.አይ.ቪ ቫይረስን ስርጭት ለመግታት የያዘችው እቅድ በዚህ አካሄድ መሳካቱ አጠራጣሪ ሆኗል።

hiv patient taking medicineImage copyrightGETTY IMAGES

ኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ ስርጭትን መቀነስ ለምን ተሳናት?

ከጥቂት ዓመታት በፊት መንግሥት አና ምንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባከናወኗቸው ተግባራት በቫይረሱ ምክንያት ይከሰት የነበረን ሞት በ70 በመቶ መቀነስ ተችሎ ነበር።

በዚህ ስኬት ምክንያትም መንግሥትምና መንግሥታዊ የልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ህበረተሰቡ በአጠቃላይ ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ ይሰጡ የነበረው ትኩረት እንዲቀንስ ሆኗል።

አቶ ክፍሌ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስን ስርጭት ለመቀነስ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ የተመዘገበውን ስኬት ከግምት ውስጥ አስገብተው ሃገሪቷ በሽታውን በራሷ አቅም መቆጣጠር ትችላለች በማለት የደርጉ የነበረውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ አቁመዋል።

ጽ/ቤታቸውም መንግሥት በመደበው በጀት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ ተግባራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይናገራሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.