ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚመራው አገዛዝ ካድሬዎቹንና የበታች አመራር አባላቱን በዝግ ስብሰባ ጠርቶ እያወያየ መሆኑ ተደረሰበት

ተንሳኤ ራዲዮ
ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ግራ የተጋባው የህወሃት አገዛዝ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ካድሬዎቹንና የበታች አመራር አባላቱን በአዲስ አበባና በመቀሌ ሰብስቦ እያወያየ መሆኑን ለትንሳኤ ዝግጅት ክፍል ከደረሱ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሥራ አመራር ማሠልጠኛ ውስጥ ካለፈው ሰኞ ሃምሌ 10 ጀምሮ ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ የሆኑ አባላት ልዩ ውይይትና ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነ የገለጹት ምንጮች የሥልጠናውና ውይይቱ ዋና አጀንዳ በመላው አገሪቱ ውስጥ እንደ ገና እንደ አዲስ እያጠላ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በአጭሩ ለመቅጨት ምን መደረግ እንዳለበት የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃያ ሁለት  ተብሎ በተሰየመው እና ወደ ሃያት በሚወስደው መንገድ ላይ ባለው የሥራ አመራር ማሠልጠኛ ውስጥ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙ እነዚህ ሠልጣኞች በሙሉ ለህወሃት ከሌሎች ካድሬዎችና የበታች አመራሮች የተለየ ታማኝነት አላቸው ተብለው በልዩ ጥንቃቄ የተመረጡ መሆናቸው ታውቆአል። ሠልጣኞቹን ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያዎች የሚያጓጉዙ ከ 16 በላይ ዘመናዊ አውቶቡሶች ላለፉት  4 ቀናት በማሠልጠኛው ግቢ ውስጥና በራፍ ላይ ቆመው ይታያሉም ተብሎአል። በሥልጠናው ላይ እየተሳተፉ ላሉ ለነዚህ ሠልጣኞች መንግሥት የውሎ አበል ክፍያ ከመፈጸም አልፎ መኝታ በነጻ እንዲያገኙ አድርጎላቸዋል። ሆኖም በሥልጠናው ግቢ ውስጥ በሚቆዩባቸው ቀናት የሚመገቡትን ምግብ እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ እየቀረበላቸው ነው ያሉት ምንጮች እየቀረበ ያለውን ምግብ ጥራትና ዋጋ በማነጻጸር በንጉሰ ነገሥቱ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ዝርዝሩን እንደሚከተለው ገልጸዋል። የበግ ጥብስ 7  ብር፣ ሳንዲዊች 3 ብር፣ ቀይ ወጥ 4 ብር፣ የጾም በየአይነቱ 3 ብር፣ ክትፎ 9 ብር እና ዱለት 6 በር ይሸጥላቸዋል። በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው አነስተኛው የምግብ ዋጋ የበግ ጥብስ ከአንድ መቶ ብር በላይ፣ ሳንዲዊች ትንሹ ቢያንስ 25 ብር፣ ቀይ ወጥ 60 እና 70 ብር፣ በየአይነቱ የሚባለው የጾም ምግብ 70  ብር፣ ክትፎ 150 ባላነሰ ዋጋ አንደሆነ  ይታወቃል።

ይህ በዚህ እንዳለ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የካቢኔ አመራሮች በሙሉ የተሳተፉበት ግምገማ ሰሞኑን መካሄዱን ለማወቅ ተችሎአል። በግምገማው ላይ ከተነሱት ነጥቦች ውስጥ አብዛኛው የአመራር አባል አምስት ለአንድ የተባለውን  አደረጃጀት እንዲሠራ የበኩሉን ጥረት ባለማድረጉ የተነሳ በህብረተሰቡ ውስጥ ድርጅታቸው ኢህአደግ ሊኖረው የሚገባው ድጋፍ እየተመናመነ መምጣቱን የሚገልጽና ከድርጅት የሚተላለፈውን መመሪያ የማስፈጸም ፍላጎት እየጠፋ በመምጣቱ ትልቅ አደጋ እየተጋረጠ መምጣቱን የሚገልጽ ነበር ተብሎአል። አንዳንድ አባላትም ፈጽመው የሚደወልላቸውን ስልክ እንደማያነሱና ምንም አይነት አስተዋጾ ከማድረግ እየታቀቡ መምጣታቸውም ተገልጾአል። ከዚህ በተጨማሪ የካቢኔ አባላትና  በየክፍለ ከተማውና ቀበሌው ተደራጅተው የነበሩ አባላት ከህበረተሰቡ ጋር በመወገን የድርጅታቸውን ሚስጥር ለህብረተሰቡ አሳልፈው እንደሚሰጡ ተገልጾአል። በተለይም ህገ ወጥ የተባሉ ቤቶች ለማፍረስ የሚተላለፈው ውሳኔ በነዚህ የካቢኔ አባላትና የበታች አመራሮች አማካይነት አስቀድሞ ለባለጉዳዮቹ ስለሚነገር  ቤቶቹን ለማፍረስ የተሰማሩ ሰዎች ምንም አይነት ጥቅም እንዳያገኙ እና የድካማቸው ዋጋ መንግሥት እንዲከፍላቸው እንዲጠይቁ በማድረግ ችግር እያስከተለ መሆኑ ተገልጾ ወቀሳ ቀርቦአል። የመኖሪያ ቤቶችን የሚያፍርሱ ሰዎች ከመንግሥት የሚከፈላቸው ደመወዝ እንደሌለና ለድካማቸው ያፈረሱትን ቤቶች ቆሮቆሮና ግድግዳ እንዲከፋፈሉ የተወሰነላቸው እንደሆነም ተገልጾአል። የአዲስ አበባ ከተማ ነጋዴዎች ሰሞኑን እያቀረቡት ያለው የግብር አቤቱታም የየክፍለ ከተማው አመራሮችና ካድሬዎች የንግዱን ማህበረሰብ የማሳመን ሥራቸውን በተገቢው መንገድ አለመወጣታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ተደርጎም ቅሬታ ቀርቦአል።

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሊነሳ የሚችለው ማንኛውም አይነት ህዝባዊ ተቃውሞ በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነውን ሠላምና መረጋጋት  ሊያደፈርስ ከመቻል አልፎ ተቃዋሚዎች የአገዛዙን ዕድሜ በማሳጠር ወደ ሥልጣን የሚመጡበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ስለምችል እና ይህ ደግሞ ከማንም በላይ እስከ ዛሬ ከመንግሥት ጎን ቆመው በየክፍለ ከተማው እያገለገሉ ያሉ የካቢኔ አባላትና ካድሬዎችን በዋንኛው ሊጎዳ  እንደሚችሉ አውቀው ከመንግሥታቸው ጎን በመቆም ይህንን አደጋ የመቀልበስ ሃላፊነት እንዳላቸው ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸዋል ተብሎአል።

በሌላ ዜና ባለፈው ጊዜ ባህር ዳር ከተማ ተካሂዶ ያለውጤት የተጠናቀቀው  የአማራና የትግራይ ሽማግሌዎች ስብሰባ በድጋሚ መቀሌ ከተማ ላይ መካሄድ ላይ እንደሆነ በአገዛዙ ሥር የሚገኙ ሚዲያዎች ሳይቀር መዘግባቸው ታውቆአል። ባህር ዳር በሚገኘው ሆም ላንድ ሆቴል ውስጥ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ተደርጎ ያለውጤት የተበተነው የሁለቱ ክልሎች ሽምግልና ስብሰባ በአገዛዙ በኩል እንዳልተዘገበ ይታወቃል። የትንሳኤ ሬዲዮ በሽምግልናው ላይ የተሳተፉ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ዜናውን ለህዝብ ጆሮ ካደረሰ ከሁለት ሳምንት ቦኋላ መቄሌ ከተማ ላይ የተጀመረው ተመሳሳይ ስብሰባ ምን አይነት መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል አልታወቀም። መቀሌ ከተማ ላይ እየተደረገ ባለው የሽምግልና ስብሰባ ላይ የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና ትላልቅ ካድሬዎች እንደተገኙ ተገልጾአል።

ለረጅም አመታት ተከባብሮና ተዋዶ በሠላም ይኖር በነበረው የአማራና የትግራይ ብሄረሰብ መካከል ጥላቻንና መቃቃርን ሲዘራ የኖረው የህወሃት አገዛዝ ታሪካዊ የሆነ የጎንደር ግዛትን ወደ ትግራይ ክልል በመከለል ሁለቱን ህዝቦች ደም ለማቃባት ዛሬ ድረስ ለት ተቀን እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል። የትግራይ ዋና ከተማ በሆነችው መቀሌ አሁን የተጠራው የሽምግልና ስብሰባ ላይ የተሳተፉ የአማራ ተወላጆች በህዝባቸው ውክልና የተመረጡ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን በምን ጉዳይ ከትግራይ አቻዎቻቸው ጋር እንደሚመክሩ የአማራም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ነገር እንደሌለት ትንሳኤ ሬዲዮ አረጋግጦአል።

ህወሃት በአዲስ አበባም ሆነ በሽምግልና ስም መቀሌ ከተማ ላይ እያካሄደ ያለው ስብሰባ ዋና አላማ ሰሞኑን እንደገና የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ አማራና ሌሎች ክልሎች እንዳይዛመት ለመማጸንና ህዝብን ለማደናገር ያለመ እንደሆነ የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሁሉ ይስማሙበታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.