ወደድንም ጠላንም ከፖለቲካው ዉጭ ልንሆን አንችልም #ግርማ_ካሳ

“ፖለቲከኛ” አይደለሁም። በሞያዬ ኢንጂነር/ፊዚሲስት ነኝ። ግን አንድ ነገር እረዳለሁ። ፖለቲከኞች ባንሆንም ፖለቲካው በአዎንታዊ ሆነ በአሉታዊ መልኩ ይነካናል። ፖለቲካው ከተበላሸ አገር ትጠፋለች። ሊቢያ፣ ሲሪያ፣ ሶማሊያ፣ የመን ዉስጥ እያየን ያለነው እልቂት የፖለቲካው ብልሹነት ውጤት ነው። በአገራችን “አማራ ናችሁ” ተብለው ወይንም የሚኖሩባት ቦታ ለልማት ይፈለጋል በሚል ምንም ከፖለቲካው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ብዙዎች ተፈናቅለዋል። በባድመ ጦርነት ከ120 ሺህ ወጣቶች የሞቱት አስመራና አዲስ አበባ በነበረው የፖለቲካ ብልሹነት ምክንያት ነው። የኑሮ ዉድነቱ፣ የብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆሉ፣ ለሁሉም ነገር ጉቦ መጠየቁ፣ ግፍ ሲሰራ አቤት የሚባልበት አካል አለመኖሩ፣ ዳኞች አመዛዝነው ፍርድ ከመስጠት ይልቅ ከሌላ አካል የተሰጣቸውን መመሪያ የሚያነቡ መሆናቸው፣ አቃቤ ሕጎች ምስክሮችን እያስጠኑ ዜጎችን በዉሸት እየከሰሱ ማሰራቸው…… ሁሉም ምንጫቸው የፖለቲካው መበላሸት ነው። ፖለቲካው ከተበላሻ ፍትህ አይኖርም። ፍትህ ከሌለ መረጋጋትና ሰላም አይኖርም። ሰላምና መረጋጋት ከሌለ እድገትና ልማት አይኖርም። ሁሉም ነገር የተያያዘ ነው።

ለዚህ ነው ፖለቲካ ሱሳችን ሆኖ ሳይሆን፣ የፖለቲካው መበላሸት የችግራችን ዋና ምንጭ በመሆኑ፣ ፖለቲካው እንዲስተካከል ለማድረግ የምንጽፈዉና የምንጦምረው።
የአገራችን ፖለቲካ በገዢው ፓርቲ ዘንድ ይሁን በተቃዋሚዎች ዘንድ የተመሰረተው ጤናማ በሆነ መሰረት ላይ አይደለም። ኢሕአዴግ ከስህተቶቹ መማር ያልቻለ፣ ግትርና ዘረኛ ፖለቲካን የሚያራምድ ነው። አገሪቷን በዘር ሽንሽኖ በሰላም ሲኖሩ በነበሩ ማህበረሰቦች ዘንድ ቁርሾና ጠብ እንዲያድግ እያደረገ ነው። ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ። በሸዋ፣ ኦሮሞ፣ አማራው፣ ጉራጌው…በሰላም ነበር የሚኖረው። ተዋልዶ፣ ተዛምዶ። አሁን ግን ሸዋ በአክራሪ ኦሮሞዎች ስር ወድቆ፣ አብዛኛው ሸዋ ኦሮሚያ የሚባል በታሪክ ያልነበረ ክልል ዉስጥ ተጠቃሎ፣ ኦሮሚያ ደግሞ የኦሮሞዎች ብቻ ነው ተብሎ፣ የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ብቻ ሆኖ፣ ሌሎች እንደ ዉጭ አገር ዜጋ እየታዩ ከፍተኛ የዘር መድሎ፣ በአገራቸው እየተፈጸመባቸው ነው። ሁሉም እኩል የሆኑበትን አሰራርና ክልል ከማስቀመጥ አንዱን የመሬት ባለቤት ሌላውን መጤ ኦድርጎ በመውሰድ አላስፈላጊና ኋላ ቀር የዘር ንትርቅ ዉስጥ እንድነገባ ተደርገናል።

በወልቃይት ጠገዴ ለዘመናት ሰዉ ትግሬ፣ አማራ ሳይባባል፣ በፍቅር፣ በሰላም ተዋልዶ ነበር የሚኖረው። እንደ ትግሬ ወይንም እንደ አማራ ሳይሆን እንደ ወልቃይቴ። ትግሪኛም ፣ አማርኛም እየተናገሩ፣ ሲያሻቸው ሽሬ፣ ሲያሻቸው ጎንደር ሄደው እየነገዱ። አሁን ግን በሕወሃት ዘመን፣ ነዋሪዉን በዘር መነጽር መመልከት ተጀመረ። ወልቃይቶች “ትግሬ ናችሁ” ሲባሉ፣ “ትግሬ አይደለንም፣ አማራ ነን” የሚል መልስ ሰጡ። የትግሬነት ማንነትን በግድ ካልተቀበላችሁ ተብለው ብዙዎች ታሰሩ፣ ተሰደዱ። ፖለቲካው አላስፈላጊ የትግሬነት ማንነትን ለመጫን በመሞከሩም የአማራ ማንነት አቀነቀነ። ነገሮች ከዘር ጋር በተገናኘ ከረሩ።እንግዲህ ይሄ ፖለቲካው ያመጣው ጣጣ ነው።

በአብዛኛው ተቃዋሚ ወገኖች ዘንድም ፖለቲካው የተመሰረተው በጥላቻ ነው። አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ተቃዋሚ የሆኑት ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት ብለው አይደለም። ወይም ለስልጣን አሊያም ዘረኛ ከመሆናቸው የተነሳ እንዴት “ትግሬዎች” ይገዙናል ከሚል ነው።

ለምሳሌ ግንቦት ሰባት የተባለውን ቡድን እንመልከት። ይህ ቡድን በአንድ በኩል ለፍትህና ለዲሞክራሲ የቆምኩኝ ነኝ ይላል። ለፍትህ የቆመ ሰው ወይንም ድርጅት ኢፍትሃዊነትን የሚቃወመው እየለየ አይደለም። በማንም ፣ በየትም ቦታ ይፈጸም፣ ኢፍትሃዊነትን መታገልና ማውገዝ አለበት። በአንድ በኩል ኢሕአዴግን እያወገዙ፣ በሌላ በኩል የለየለት በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ የተወገዘ፣ ለብዙ ሺህ ኤርትራዉያን ወገኖቻችን እልቂት ምክንያት የሆነ አረመኔ አገዛዝ ስር ሄዶ መለጠፍና ይሄን አገዛዝ ማመስገን ግን ግብዝነት ነው። “ወያኔን እስከጠለልን ድረስ ሰይጣን ልለምን አይሆንም፣ አብረን እንሰራለን” ነው የሚሉት የድርጅቱ አመራሮች። ደርግም እስከጣለለን ትተብ፤ኦ ወያኔ ተደግፎ እንደነበረው ማለት ነው። ይህም ግንቦት ሰባቶችና ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች ለፍትህ ቆመናል የሚሉት በፋቸው እንጂ በልባቸው እንዳልሆነ የሚያሣየው። የሚታገሉትም በአገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ሳይሆን ወያኔን ለመጣል ብቻ ነው። ጸባቸው ከኢፍትሃዊነት፣ ከግፍ ጋር ሳይሆን ከግለሰቦችና ከድርጅቶች ጋር ነው። ይህ አይነቱም በመርህ ላይ ሳይሆን በጥላቻ ላይ፣ በፍቅር ላይ ሳይሆን በንዴት ላይ፣ በእዉነት ሳይሆን በዉሸትና በማጭበርበር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የተበላሸ ፖለቲካ ነው።

ብዙ ድርጅቶች አሉ በአንድ በኩል ሕወሃትን በዘረኝነት እየከሰሱ እነርሱም በዘር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ። እንደ ሕወሃት እነርሱም መርዛማ የዘር ፕሮፖጋንዳ የሚረጩ። ህወሃቶች “ተጋሩ፣ ተጋሩ” እንደሚሉት እነርሱም “ኦሮሞ፣ ኦሮሞ” ፣ “አማራ ፣ አማር” እያሉ መልኩን ቀየረ እንጂ፣ የሕወሃቶች ጠባብ አስተሣሰብ እየበከላቸው ነው። በዉስጣዊ አሰራራቸው ከኢሕአዴግ ባልተናነሰ እነርሱም አምባገነናዊ አስራራ ነው ያላቸው። አንዳንዶቹማ መሪዎቻቸውን ቀይረውም አያውቁም። መሪዎቻቸው፣ከአገርና ከጥቅም ይልቅ ስልጣናቸወንና የግል ጥቅማቸው የሚያስቀድሙ በመሆናቸው አብረው መስራት እንኳን የተሳናቸው ናቸው። (በተለይም በዉጭ አገር ያሉ)

ወገኖች መሰረታዊ ችግር ነው ያለብን። ዉጫዊ ሳይሆን ዉስጣዊ። እመኑኝ ትልቅ የአስተሳሰብ ተሃድሶ ካላደረግን፣ ከዘር ፖለቲካ ካልወጣን፣ ዜጎችን በዘራቸው ሳይሆን በስራቸውና በምግባራቸው ብቻ መመዘን ካልጀመርን፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሳይሆን ሁላችንም እኩል የሆንበት አሰራር ካልፈጠርን፣ ሕግ የበላይ ካልሆነ፣ የሚመሩንን በነጻነት መሾምና መሻር ካልቻልን፣ አሁን ካለንበት የበለጠ ዉድቀት ዉስጥ መውደቃችን አይቀርም። ትግሬ አማራ መባባል ካልቆመ የወልቃይት ችግር አይፈታም። አማራ፣ ኦሮሞ መባባል ካልቆመ የሸዋ/አዲስ አበባ ችግር አይፈታም። ሶምሌ ኦሮሞ መባባል ካልቆመ የሞያሌ፣ የጭናቅሰን..ችግር አይፈታም።

ከዘረኝነት ፣ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል፣ ከቁርሾ፣ ከእልህና ከኋላቀርነት ፖለቲካ ወጥተን፣ ወደ ሰለጠነ የፍቅር፣ የአንድነትና የኢትዮጳዊነት፣ የይቅር መባባልና የመቻቻል ፖለቲካ እንሽጋገር ዘንድ እግዚአብሄር ይርዳን። ልባችንን ለፍቅር፣ አይምሯችንን ለማስተዋል የተከፈተ ያድርግልን !!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.