በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ቀውስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ 11 አለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክርቤትን ጠየቁ

ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በቀጣዩ ሳምንት በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ቀውስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አለም አቀፍ ተቋማት ጠየቁ።
በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰሩ 11 ድርጅቶች የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ በጋራ ያቀረቡትን ጥያቄ ከምክር ቤቱ እንዲያስገቡ ሂውማን ራይትስ ዎች አስታውቋል።
ፍሪደም ሃውስ፣ ኢንተርናሽናል ሰርቪስ ፎር ሂውማን ራይትስ፣ ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ፣ ወርልድ ኦርጋናይዜሽን አጌይንስት ቶርቸር፣ እንዲሁም ኢንተርናሽናል ፊዴሬሽን ፎር ሂውማን ራይትስ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምክር ቤት ጥያቄያቸውን ካቀረቡ ተቋማት መካክል ዋነኞቹ መሆናቸው ተመልክቷል።
እነዚሁ ድርጅቶች ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ጥያቄ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሆኖ የሚገኘው የሽብርተኛ ወንጀል እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚመለከተው አዋጅ ለሰብዓዊ መብት መከበር ማነቆ ሆኖ መቀጠሉን በደብዳቤያቸው አብራርተዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ ያወሱት አለም አቀፍ ድርጅቶች እነዚሁ ጉዳዮች በልዩ ጉባዔው ተነስተው ውይይት እንዲካሄድበት ጠይቀዋል።
በተለይ ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃም በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት የተባበሩት መንግስታት ግፊቱን እንዲቀጥል 11ዱ ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በኦሮሚያ ክልል ተፈጽሟል ያለውን ግድያና እስራት ለመመርመር ጥያቄን ቢያቀርብም መንግስት ጥያቄውን ሳይቀበል መቅረቱ ይታወሳል። በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበሩ የምክር ቤቱ ሃላፊዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል በመጓዝ ቅኝትን ለማድረግ ለመንግስት ጥያቄን ቢያቀርቡም ፈቃድ ተከልክለዋል። ይኸው አለም አቀፍ አካል የኢትዮጵያ መንግስት ዳግም ለቀረበው የምርመራ ጥያቄ እስካሁን ድረስ ምላሽ እንዳልሰጠው ሲገልፅ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አካሄጀዋለሁ ባለው ምርመራ ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 669 ሰዎች መገደላቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናት ጥናቱ ከተጀመረበት ከሃምሌ ወር በፊት ከ100 በላይ ሰዎች ሞተው እንደነበር ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ አማራና የደቡብ ክልሎች በአጠቃላይ 745 ሰዎች ሞተዋል ቢልም አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገልጻሉ።
ቅሬታቸውን እያቀረቡ ያሉት እነዚሁ ድርጅቶች ግድያውና እስራቱ በገለልተኛ ቡድን ማጣራት እንዲካሄድበት እየጠየቁ ይገኛል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.