የአሜሪካ ፍ/ቤት የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ አሜሪካዊ ዜጋ ላይ ፈጽሞታል የተባለው የኢንተርኔት የስለላ ወንጀል ድርጊት በይግባኝ እንዲታይ የቀረበን ጥያቄ ማድመጥ ጀመረ

ኢሳት (ጥር 26 ፥ 2009)

በአሜሪካ አገር በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሚገኝ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ አሜሪካዊ ዜጋ ላይ ፈጽሞታል የተባለን የኢንተርኔት የስለላ ወንጀል ድርጊት በይግባኝ እንዲታይ የቀረበን ጥያቄ ማድመጥ ጀመረ።

የስለላ ድርጊቱ የተፈጸመባቸውን አሜሪካዊ ሾልኮ የሚገኘው የኤለክትሮኒክስ ፍሮንቲየር ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም ሃሙስ መደመጥ የጀመረው የክስ ሂደት ከአንድ እስከ ስድስት ወራቶች ሊወስድ እንደሚችል አስታውቋል።

ሁለት ታዋቂ የህግ አካላትን ይዞ ኪዳኔ በሚል መጠሪያ የቀረቡ ከሳሽን የወከለው ድርጅቱ በደምበኛው ላይ የተፈጸመው ድርጊት ከተጠያቂነት የማያስመልጥ ለመሆኑ በህግ ባለሙያዎች ዘንድ ለይግባኝ ፍርድ ቤቱ ማብራሪያ መቅረብ ይገልጻል።

በፋውንዴሽኑ የህግ ባለሙያ (Staff Attorney) የሆኑት ናት ካርዶዞ የኢትዮጵያ መንግስት ፈጽሞታል የተባለው ድርጊት ከሳሽ በአካል ካሉበት ሃገር ውጭ የተቃጣ በመሆኑ ተጠያቂ አያደርገንም የሚል ክርክር ማቅረባቸውን ለኢሳት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትን የወከሉ ጠበቆች ማንኛውም የውጭ መንግስት ከሌላ ሃገር ሆኖ በአሜሪካ የአካል ጉዳትን ያላስከተለ ህገወጥ ድርጊት ቢፈጸም በህግ ተጠያቂ እንደማይሆን ለፍርድ ቤቱ መከራከሪያ አስደምጠዋል።

ይሁንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከሳሽ ወክለው የቀረቡት የህግ ባለሙያው ሪጃርድ ማርቲኔዝ መንግስት በአካል የላከው ሰው ባይኖርም ወንጀሉን ለመፈጸም የረቀቁ የኢተርኔት ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙንና መከራከሪያ ነጥቡ ከህግ አኳያ ምክንያታዊ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

የአቶ ኪዳኔ ጠበቃ አክለውም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በጥቅምት ወር 1976 አም በአሜሪካው ፕሬዚደንት ጄኔራል ፎርድ የጸደቀ ህገ በውጭ ሃገር መንግስታት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ለህግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካ ዜጋው ላይ ከፈጸመው የኢንተርኔት የስለላ ድርጊት በተጨማሪ መቀመጫቸውን በውጭ ያደረጉ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ኢላማ እንደነበሩ ሲቲዝን ላብ የተሰኘ የካናንዳ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያፋ ማድረጉ ይታወሳል።

መንግስት ለስለላ ድርጊቱ የሚጠቅመውን አገልግሎት ለማግኘት መቀመጫውን በጣሊያን ካደረገ የሃኪንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት አድርጎ እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በተከታታይ ዘገባ ማቅረቡ አይዘነጋም።

የመረጃው ይፋ መደረግን ተከትሎ የጣሊያኑ ኩባንያ አገልግሎቱን ለኢትዮጵያ መንግስት ሲያቀርብ እንደነበር በወቅቱ አረጋግጧል። መንግስት ለኩባኒያው የፈጸመው የአንድ ሚሊዮን ዶላር ደረሰኝም ለህዝብ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ባልደርቦቹ የኮምፒውተር ጠለፋ ሰለባ መሆናቸው ይታወሳል።

በአሜሪካ ዜጋው ክሱ በይግባኝ እንዲታይ የቀረበው የመከራከሪያ ሂደት ውሳኔን ለማግኘት ከአንድ እስከ ስድስት ወር ሊወስድ እንደሚችል ታውቋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.