አገሬ ላይ ሆኜ አገሬ ናፈቀኝ::” – ደምለው አልማው

እማየው እምሰማው ሁሉ እያሳቀቀኝ:

…..ያለው አዝማሪ ይሁን ገጣሚ ባለቅኔ ባላውቀውም ወይም ባላስታውሰውም እንደመጣልኝ ስለተጠቀምኩበት አንባቢዎች ሆይ ይቅርታ እላለሁ::

ከእራሴ ከግሌ እይታና እሳቤ ስነሳ  በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለው ጦርነት  አላባራ እያለ ይልቁንም እያየለ ሲሄድ  አስተዋልኩ መሰለኝ::  መሰለኝ ስል ግርግር ውስጥ መሀል ቆሜ   ተወናበድኩ ልበል?  ወይስ  ከግርግሩ የተነሳ ግራ ገባኝ ልበል?

በመንግስቱ ኃይለማርያም ሥርዓተ መንግስት ውስጥ ተቀርጾ ለአንደኛና ለመለሰተኛ ሁለተኛ ደረጃ  ላሉ ተማሪዎች የሕብረተ-ሰብእ እና የታሪክ ትምህርት ማስተማሪያ መጽሐፍ ላይ ታትሞ የተማርኩት ትምህርት እንደልክፍት እስከ ዛሬ ድረስ አልለቅህ ብሎኝ አብሮኝ እየኖረ ነው:: እየኖረ ስል ሠላም ሰጥቶኝ አይምሰላችሁ:: ሠላሜን እየነሳኝ እንጂ:: የኔ ዘመን ሰዎች ይህንኑ ሳይጋሩኝ እንዳልቀሩ መገመት እችላለሁ:: የጅባትና ሜጫ አውራጃ ተወላጅ  መልከ-መልካሙ መምህር ተረፈ በዳዳ እና የሰላሌ አውራጃ ተወላጅ መምህር ዐሊ ሞሐመድ  አማካይነት የተማርኩት ትምህርት:  ውስጤ ስህተት እንደነበረ ይጠረጥራል ::

የተማርኩት ትምህርት አርእስቱ የኦሮሞ ስደት ይላል:: በአማራ ቁዋንቁዋ:: በእንግሊዝ ቁዋንቁዋ ተርጉሙትና ተረዱት:: ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስበው አርእስቱ ብቻ ጦርነት ያስነሳል:: ዛሬ አሜሪካ ውስጥ እየኖርኩ አሜሪካዊያን የኢትዮጵያዊያን ስደት ብለው ቢጽፉ መቃወም አልችልም:: ቢያስተምሩኝም አልቃረንም:: ምክንያቱን መዘርዘር የአንባቢን ስሜት መቡዋጨር ስለሆነ ልለፍ::

እንዴት አንድ ባለሀገር የሆነ ሕዝብ ስደተኛ ተብሎ ይጠራል?  ወደኢትዮጵያ ተሰደደ እንበልና ከየት ነው የተሰደደው ብለን እንጠይቅ እስቲ?  የኦሮሞን ስደተኛነት ለትውልድ ለማስተማር ያሰቡ ወያም ያሤሩ ሃሳቡን የተቀበሉትና መርምረው ያጸደቁት ያሳተሙትና ያሰራጩት ቀጥለውም ለትውልድ ያደረሱት ሰዎች: የትምህርት ዝግጅት ባለሙያዎች: ባለሥልጣናት ስደቱን በሚገባ በማስረጃ አስደግፈው እና አስረግጠው በማቅረብ አላሳመኑኝም:: ብቻ በልጅነት አእምሮዬ  ላይ እንዳሻቸው ዘሩበት እንጂ:: የያኔው የትምህርት ባለሙያዎች ወይም አዋቂዎች ዛሬም በህይወት አሉ:: ስህተት ሠርተናል አላሉም:: ጥፋት አጥፍተናል:: በዚህም ትውልድ እንዲመረዝ አድርገናል::  ኢትዮጵያዊ ስሜትን ለማሳከር ብቅልና ጌሾ ጠንስሰናል:: የዛሬው ጉድ የበቀለው እኛ ውስጥ ነበረ አላሉም:: በዚያው መንገድ እንደተጉዋዙ ናቸው:: ኢትዮጵያ የምትባል አገር እስኪትጠፋ ድረስ:: ዳሩ ግን ኢትዮጵያ ሳትጠፋ እነሱ ቀድመው ያልፋሉ እንጂ የኢትዮጵያን ጥፋት አያዩአትም:: ምናልባት የኢትዮጵያን ጉዳት ለማየት ይታደሉ ይሆናል::

እነዚሁ  ልሂቃን ከእነሱ ሃሳብ ውጭ የሚከሰትን ነገር ለማጥራት ጎበዞች ናቸው:: አሳማኝ ማስረጃ ሲሹ ብርቱዎች ናቸው:: እውነትን ለመያዝ ነገሮችን ሲያበጥሩና ሲያነጥሩ ትጉኆች ናቸው:: በዚህ በኩል በጣም አረዐያ መሆን ይችላሉ::  ጠንካራ ጎናቸው ይኼ ነው:: ከእነሱ አእምሮ ውስጥ ለሚከሰት ክስተት ግን  ማስረጃ ለማቅረብ አይፈልጉም:: ወይም ማስረጃ ነው ብለው የሚያቀርቡት ፍሬ ቢስ እንኩዋን ቢሆን መለኮታዊነትን ያጎናጽፉትና ከመሬት አንስተው ሰማይ ውስጥ ይሸጉጡታል እንጂ ለመነጋገር ፈቃደኞች አይሆኑም::  እንዲያም የመልስ ምቱ እንደ ብራዚል ማፊያ  በሌላ አቅጣጫ  መሰንዘር ይጀምሩታል:: ያጠቁታልም::  ለጊዜውም ቢሆን በርብርብ ጸጥ ያሰኙታል:: በዚህም ማስረጃ ጠያቂውን ወንጀለኛ ሀሰተኛ ወይም ዐመጸኛ  አስብለው ያወግዙታል:: ያስወግዙታልም:: ይሄ ባህል ሆኖ ዛሬም አለ::

በዚህ በኩል ለምን እንደመጣሁ መግለጽ እፈልጋለሁ:: ታሪከኛ ስላልሆንኩ  እንደልቤ ነው የምናገረው::  አንዳንድ ጊዜ አላዋቂነት እራሱ  ነጻነት ነው መሰለኝ  አላዋቂነትህን እያስቀደምክ እንደአሰኘህ ያሻህን ለመናገር ይጠቅመሃል::  እንደዚያ ነው::

እናም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የተባሉት ምሁር ጉዳይ እያነጋገረ መጥቶአል::  እስቲ እኔ ባላዋቂነቴ ስለዚሁ ምሁር የተሰማኝን ስሜት ላስቀድም::

እኚህ ደፋር ምሁር  ስለሚሰጡት ቃለ ምልልስ:  ስለሚተርኩት ታሪክ: ስለሚጽፉት መጽሐፍ  ሁሉ እሰማለሁ:: አዳምጣለሁ:: እመለከታለሁ:: ከላይ ከላዩ የተሰማኝን ስሜት መጻፍ ፈለኩ ::ጥልቅ ጥልቁን ለጠላቂዎቹ ትቼ ማለት ነው::

ለእኔ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በበርካታ ጉዳዮች ያወዛግቡኛል:: ምሁራዊና ባህላዊ ስነ- ምግባር አጥቼባቸዋለሁ:: ለምሳሌ  እራሳቸውን ሲያደንቁ ከራስ መተማመን አልፎ ከትዝብት አረንቁዋ ሲጥላቸው አይቻለሁ:: ለማስረገጥ ያህል ቃል በቃል ባይሆንም ያሉትን ነገር ልጥቀስ::  ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንን  ድሬ ደዋ ላይ ስተዋወቃቸው ገጣሚ ፍቅሬ ቶሎሳ እባላለሁ::እኔም እንደአንተ ገጣሚ ነኝ ስላቸው ከመቀመጫቸው ተነስተው ተጨባበጥን እንዳሉት ብዙዎች እንደኔ የሰሙት ይመስለኛል:: ለእኔ ግን   አተዋወቃቸው እውነት አልመስልህ እያለኝ ነው::  ምክንያቱም  እኔ ሎሬት ጸጋዬን በመጠኑ ሳውቃችው እንኩዋን ለአንድ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪ ቀርቶ ለእኩዮቻቸውም ሆነ ለበላዮቻቸው  እንዲህ ዓይነቱን በድፍረት የተሞላ ሠላምታን ያስተናግዱታል ብዬ አላምንም::

ሎሬት ጸጋዬን እና በዚያን ጊዜ ተማሪ ፍቅሬ ቶሎሳን  በአንድ ሆቴል በረንዳ ላ ይ የተደረገው ትውውቅ  ወይም ቃል ለቃል ንግግር  ማንንም አያሳምንም:: እኔ በምናቤ ሳየው የሚታሰብ አይደለም:: ሎሬት ጸጋዬን የሚያውቅ ሰው  መናገር ይችላል::  ነፍሳቸውን ይማረልኝና ሐይማኖት ዓለሙ ዱኪ እና አርቲስት አበበ ባልቻ  ጋሼ ጸጋዬ ፊት ቆመው ሠላምታ ሲለዋወጡ ያየሁት ግብረ- ገብ እና የዚያኔ የተማሪ ፍቅሬ  ቶሎሳ  ሠላምታ መለዋወጥ አልገናኝ ብሎኛል :: እንዲያውም  ያሳቅቀኛል:: እንግዲህ  ፕሮፌሰር ፍቅሬ ከሁሎቹም ከአገራችን ታላላቅ ሰዎች ጋራ ሲገናኙ  አደረኩት የሚላቸው ንግግሮች ሁሉ ያልተጻፈ  ጥንታዊ ባህላችንን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን የሚዳፈርም ጭምር ነው:: ታላላቆቹን: መምህራኖቹን የማክበር ባህል አላየሁበትም::   ቀደምቶቹን እያጨማደደና እያኮማተረ ከጠራ ስለሚጽፈው ታሪክ  ለማመን  ያስቸግራል::  ፕሮፈሰር ፍቅሬ ስለራሳቸውና ስለሥራዎቻቸው  ሲገልጹ ኢትዮጵያ የምትባል አገር  የታሪክ :የሥነ ጽሁፍ  እና የስነ ጥበብ  ብቸኛ  ምሁር አድርጎ በመቅረጽ ነው:: እሳቸው ያዩትን ማንም እንዳላየ: እሳቸው ያገኙትን ማንም እንዳላገኘ: እሳቸው የደረሱበትን ማንም እንዳልደረሰበት አስመስሎ ራስን ማቅረብ የጤና አይደለም::  ፕሮፌሰር ፍቅሬ  ራሳቸውን ሲያደንቁ ልክና መጠን የላቸውም:: ልክና መጠን የሌለው ደግሞ ርካሽ መሆኑ የታወቀ ነው:: ይህንን ስብእናቸውን ቢያርሙ በጣም ደስ ይለኛል::

ሰሞኑን መወያያ ስለሆነው መጽሀፋቸውን አስመልክቶ በየሚዲያው የሚሰማው ነገር  ሁለት ገጽታ አለው ብዬ አስባለሁ:: አንደኛው  ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከደረሰበት የዘረኝነት አደጋ ራሱን ለመከላከል እና አገሩንም ለመታደግ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊ የደምና የዘር ትስስር  መኖሩን አስረግጦ መጻፍ  በጎ ሃሳቡ ተቀባይነት አለው::  ሃሳቡ እንደሃሳብ ምርጥ ነው::  ውሳኔም አስገራሚ ነው:: ድፈረቱም ይደነቃል:: በዚህ መልኩ የሚያየው ሕዝብ ፕሮፌሰር ፍቅሬን  ማድነቅ ተገቢ ነው:: ሁለተኛው ገጽታ የመጽሀፉን ፍሬ ታሪክ ለማየት መጽሀፉን  መመርመር የሚሹ ኃይሎች ነው::  እነዚህ ደግሞ ወቅታዊነትን መሠረት አድርገው  አይነሱም::  የሚፈልጉት ማስረጃን ነው::  እንደ የታሪክ ምሁርነት አንድ ታሪክ ሲጻፍ ሕግጋቶች ይኖሩታልና ሕግጋቶቹን: ደንቦቹን ነው እየጠየቁ ያሉት::  ምርቱና ገለባው ተበጥሮ ሳይለይ ከጎተራ የሚገባ ጥሬ ምርት  እንዳይኖር ሲሉ ይመስለኛል::

ነገር ግን  አስቀድሜ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ትላንት የኢትዮጵያን ሕዝብ መጣተኛ አድርገው ሲያቀርቡ  ማስረጃ አልነበራቸውም:: ማሳመኛ አላቀረቡም::  ዛሬ ለፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሀፍ ያቀረቡት ማጣሪያ ለራሳቸው ታሪከ መጽሀፍ አላቀረቡም::  አደገኛ ነገር እነሱ ጋራ አለ:: ሁልጊዜ የራሳቸውን ታሪክ ደህንነት ለመጠበቅ ዘብ ሲቆሙ እንጂ የታሪካቸው እውነት ዘብ እንደማያስፈልግ  የተረዱት አይመስለኝም:: ለምሳሌ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌን ጽሁፎች ማንበብና በጥሞና መመርመር ያስፈልጋል:: እኔ በግሌ እኚህ ምሁር ላይ  የዕውቀት ሳይሆን የቅንነት ችግር እንደ ደዌ ተጠናውቶአቸው እንዳለ እጠረጥራለሁ::

ሳስበው እኚህ ምሁር  በታሪክ አጋጣሚ  ማስረጃ ጠያቂ  ትውልድ ባልነበረበት ወቅት የተባለውና የተጻፈው ሁሉ ቅዱስና አዋጅ ሆኖ በሚወሰድበት ዘመን ወይም እንዲወሰድ ሁኔታዎች በሚያስገድዱበት ጊዜ ላይ እንደየጸሃፊው ፍላጎትና ዓላማ  እንዲሆን ተደርጎ የታተሙትና  ከትውልድ ወደትውልድ እንዲተላለፍ ሆነው በሥርዓት እንዲያዙ  ሲባል በየታሪክ ወመዘክራት የተደረደሩትን ከነሕጸጻቸው እንድንቀበል ተጽእኖ ለማሳደር ከማይቦዝኑ ምሁራን መካከል  አንዱ አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ::

ምክንያቱም በእሳቸው አፍላ ዘመን  ብዙ ስህተቶች ተፈጽመዋል:: ብዙ የጥፋት መሠረቶች ተጥለዋል:: ዛሬ ለደረስንበት አሳፋሪ ገጽታ መሠረቱ ጥልቅ ሆኖ እንዲሠራ የተደረገው በዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ዘመን ነበረና:: ያኔ እሳቸው ኦሮሞ መጣተኛ ነው ሲባል  ዘራፍ አላሉም:: ዛሬ እስከዕለተ ዕድሜዬ ፍጻሜ ድረስ ለኢትዮጵያ ታሪክ ተሙዋጋች እንደሆንኩ ይታወቅልኝ እንዳሉት ሁሉ ያኔ ግን የታሪክ ስህተት ሲፈጸም ድምጻቸውም ሆነ ብዕራቸው አልነበረም::  አለ ካሉ ያቅርቡና ወቀሳዬን ከይቅርታ ጋራ አነሳለሁ::

ያለአንድ ሐይማኖት: ያለአንድ ቁዋንቁዋ: ያለአንድ ባህል: ያለአንድ ባህላዊ ትውፊት  እንዳይኖር በሚደረግበት ዘመን ተወልደው አድገው ተምረው ተመራምረው  የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ዛሬም የማይደፍሩት ነገር ወይም የማይነኩት ቁስል እንዳለ  ይገባናል ::ለነገሩ ሕመሙ ያለበትን ሥፍራ ታማሚው ነው የሚያውቀው:: ልክ እሾኽ አጣሪውን እንደሚባለው ሁሉ::  ስለዚህ በኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ታሪክ ወይም የገዢዎች ታሪክ ብቻ ነው የተጻፈው:: እናም የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ምሉዕ አይደለም ለሚሉት  እንደምሁርነትዎ በቂ  መልስ ይስጡ:: ለአሸናፊዎች/ለገዢዎች ታሪክ ደህንነት ዘብ ከመቆም ይልቅ ለእውነት ዘብ መቆሙ  ያስከብራል::  ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ፈቃደኛ ከሆኑ የተሳሳተውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ በሚያርም መልኩ ይጻፉትና ይነበብ::  ሁልጊዜ ቀጥታ መልስ ከመስጠት በቁዋንቁዋ ምሁርነትዎ እየተጠቀሙ ሰዋሰውና ዐረፍተ ነገር በማጣጣል በመንቀፍ ላይ ብቻ አያተኩሩ እላለሁ::

በመጨረሻም ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ የሰነጽሁፍ ሙያቸውን አጎልብተው ገጣሚነታቸውን በዓለም ላይ አስመስክረው  የኢትዮጵያ ሎሬት  ለመባል ቢጥሩ በጣም የተሻለ አቅጣጫ እንደሆነ ልጠቁማቸው እፈልጋለሁ:: ምክንያቱም  ኢትዮጵያ ሁለት ሎሬት ብቻ ነበራት:: ሁለቱንም በሕይወት አጥተናቸዋልና:: ዶክተር ፍቅሬ በዘርፋቸው ላይ ጠንክረው ይህንን ክፍተት  ይሞላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: ድሬዳዋ ውስጥ  ገና ልጅ ተማሪ ሆነው  ሎሬት ጸጋዬ ጋራ ራሳቸውን እስተካክለው እንደጠሩት ሁሉ: ምኞታቸውን እውን አድርገው የሎሬት ጸጋዬን ማዕረግ ቢወርሱ  ግርግር ውስጥ አይገቡምና ይስሙኝ እላለሁ::

ለዶክተር ጌታቸው ኃይሌም መልእክት አለኝ::  ሁልጊዜ የማይነካ ነገር አድርገው እንደታቦት የቀረጹትን ታሪክ  ደፍረው በመፈተሽ ስህተቶችን ነቅሰው በመለየት ይህንን ትውልድ ያቃኑ ዘንድ እጠይቅዎታለሁ::  ሁልጊዜ ለኢትዮጵያ ታሪክ ህመም መፈወሻውን ከማቅረብ ይልቅ ማስታገሻው ላይ ብቻ ባያተኩሩ እላለሁ::

ዶክተር ጌታቸው:-

ደምለው አልማው እባላለሁ:: ደግሞም  ለኢትዮጵያዊነቴ  ደምለው አልማው መባል ብቻውን ኢትዮጵያዊ አያስብልም እንዳይሉኝ……./

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.