የግፍ ቁና ሞልቶ ሲፈስ!!! – ዘሪሁን ገሠሠ

ይህ የምታነቡት እጅግ ልብ የሚነካ አሳዛኝ ታሪክ ፣ በወንድማችን መምህር ተፈሪ መኮነን ላይ በቅርቡ የተፈፀመ ግፍ እንጂ ልብ ወለድ አይደለም፡፡ ወጣት መምህር ተፈሪ መኮነን ይባላል፡፡ የአንድ ልጅ አባትና ወላጆቹን በሞት በመነጠቁ ምክንያት ታናናሽ ወንድሞቹን የማስተማርና የመንከባከብ ድርብርብ የቤተሠብ ሀላፊነትን የተሸከመ ወጣት፡፡ መምህር ተፈሪ በሠላማዊ መንገድ የሚደረገውን ትግል በመቀላቀል፣ በ2007 ሀገራዊ ምርጫ ፣ የህዝብን ብሶትና ጥያቄ አንግቦ፣ የትውልድ ቦታው የሆነችው ቆቦ ከተማን በመወከል ፣ ለሠማያዊ ፓርቲ የተወካዮች ም/ቤት እጩ ሆኖ በመቅረቡ እጅግ መራራና አሳዛኝ ወቅቶችን አሳልፏል፡፡ በአካዳሚክ ዕውቀቱ በሚያስተምራቸው ተማሪዎች የተመሠከረለት መምህሩ ተፈሪ፣ ከሚሠራበት የዳዋ ጨፋ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት የኮከብ መምህርነት ሽልማት ተችሮታል፡፡ የትምህርት ደረጃውን ለማሻሻል በወሎ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ድግሪ የመጨረሻ አመት ተማሪ እያለ የተከሰተው ሁኔታ ህይወቱን እጅግ አሳዛኝና የማይሽር ጠባሳ አስቀምጦባት ያለፈ ሆነ፡፡
.
ነሀሴ 6/2008 ዓ.ም በመላው የወሎ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ሲታፈሱ መምህሩ ተፈሪም ከትምህርት ገበታው ላይ /ወሎ ዩኒቨርስቲ/ ታፍኖ እኔን ጨምሮ 22 ሠዎች በተከሰስንበት “የሽብር” መዝገብ ተጠርጥሮ ወደደሴ ማረሚያ ቤት ተወረወረ፡፡ መምህር ተፈሪ የሚናፍቀውን የምርቃት ቀኑን ህፃን ልጁና ባለቤቱ፣ እንዲሁም ጓደኞቹ በሀገኙበት ጥቁሩን ገዋን በጨለማው ቦታ ደርቦ ፎቶግራፍ በመነሳት፣ አሳዛኝ ትዝታውን አሀዱ አለ፡፡ መስከሰም 05 / 2009 ለሁለተኛ ጊዜ 28 ቀን ቀጠሮ ሊጨመር ፍ/ቤት በቀረብንበት ዕለት ደግሞ በተፈሪ ላይ እጅግ መራራ ክስተት ተከሰተ፡፡ እንደወላጅ ተንከባክቦ ያሳደገው ታናሽ ወንድሙ በድንገተኛ በሽታ፣ አስታማሚው እስር ቤት በሚሠቃይበት ወቅት ለህልፈት በቅቶ፣ እናትም አባትም ሆኖ ያሳደገው ታላቅ ወንድሙ ተፈሪ በድኑን እንኳ ለመቅበር ሳይችል፣ የወንድሙንም ሞት ሳይረዳ ዋስትና ተነፍጎ በእስር እንዲቆይ ተደረገ፡፡
.
መምህር ተፈሪ ከተጠረጠረበት የሽብር ወንጀል በመደበኛውና በ96 በተሻሻለው የወንጀል ህግ አንቀፅ 257 /ሀ/ ክስ ተመስርቶበት፣ ከብዙ ውጣ ውረድ በኀላ 5 ወር ገደማ ታስሮ በዋስ ከእስር ተለቀቀ፡፡ መምህሩና ሰላማዊ ታጋዩ ከእስር ሲለቀቅ የገጠመው ሞቅ ያለ አቀባበል አልነበረም፡፡ የታናሽ ወንድሙን ቅስም ሰባሪ መርዶ ተረዳ፡፡ እርሙን አውጥቶ ሳይጨርስ ሌላ ተጨማሪ መርዶ ተጨመረለት፡፡ ኮከብ መምህር ብሎ ሽልማት ያዥጎደጎደለት የዳዋ ጨፋ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ፣ በተማሪዎቹ ተወዳጁን መምህር በብጣሽ ወረቀት “ለአንተ የሚሆን ቦታ የለኝም!” ሲል አሠናበተው፡፡ ታዲያ……. << የግፍ ቁና ሞልቶ ሲፈስ! >> ፣ ማለት ይህ አይደለምን ??? ተፌ ብርቱው ሠው ከጎንህ ነን ጓድ!!!


ዘሪሁን ገሠሠ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.