“ምሩፅ ፤ያልተዘመረለት ጀግና” – የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላትና ቤተሰብ [የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ህብረት]

ዴሴምበር በካናዳዋ የንግድ መናኸሪያ ታላቋ ቶሮንቶ ከተማ የፈረንጆቹን የገና በዓልንና የአዲስ አመት ዘመን መለወጫን በድምቀት ለመቀበል ሽር ጉድ የምታበዛበት ወር ነው ። የአየሩ ቅዝቃዜ ያለንን ልብስ ሁሉ ደራርበን እንድንለብስ የሚያስገድደን ሲሆን አካባቢውን በነጭ ቡሉኰ ሸፋፍኖ ያለ ዕድሜዋ እድሜ የተጫናት አዛውንት ያስመስላታል።

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሰፊው እንደሰፈሩባት የምትታወቀው ቶሮንቶ በአበሾች የዘውትር እንቅስቃሴ ብትደምቅም አንድ በብዙውና እንደሚገባው ያልተዘመረለት የአትሌቲክስ ጀግና በሳምባ መሰንጠቅ ሕመም ምክንያት አልጋ ላይ ከዋለ ከረምረም ብሏል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ገና ከወጣትነቱ ጀምሮ እየኰተኰተ በቅርብ ክትትል ወደ አትሌቲክሱ የሩጫ ትራክ በማምጣት ያሳደገው ስመ ጥሩው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ፤ ያ አይበገሬው ኃይሉና ጉልበቱ ከድቶት በቶሮንቶ ብሪጅ ፖይትን ሆስፒታል ህክምናውን በመከታተል ላይ እንዳለ በዴሴምበር 23 ቀን 2016 በተወለደ በ72 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

ጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሞት የማይቀር ዕዳ ሆኖ በአካል ብትለየንም ለኢትዮጵያ አገርህ ያበረከትከው ጉልህ የጀግንነት አስተዋፅ ሁልጊዜም አብሮን ይኖራል።

መላው የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላትና ቤተሰብ ፣ ወዳጅ ጓደኛ በክብር እየተሰናበቱህ ለውድ ቤተሰቦችህና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ይመኛል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ህብረት

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.