ትግራይ የምንሰማው ምስክርነት-አንድምታ (ግርማ በቀለ)

አሰዬው፣ እልል..ል..ል// ህወኃት ከ25 ዓመታት በኋላ የገባውን ቃል በ‹‹ፍትሃዊ ዕርዳታ›› ተፈጻሚ አደረገው፡፡

875tesfayeበዛሬ ምሽት ኢቲቪ ዜና ላይ በትግራ በድርቅ ለተጎዱ ወረዳ ነዋሪዎች የዕርዳታ እህል መከፋፈሉን ብቻ ሳይሆን ክፍፍሉ ያለአድልኦና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መሆኑ ተመሰከረለት፡፡ እንደተባለውና እንደተመሰከረለት ከሆነ እሰዬው ወገኖቻችን በተገባላችሁ በቀን ሶስት ጊዜ የመመገብ የተስፋ ቃል መሰረት ከ25 ዓመታት በኋላ እንኳን ‹በፍትሃዊ ዕርዳታ› ከረሃብ ተረፋችሁ እንላለን፡፡ ‹‹… ከሆነ … ›ን ምን አመጣው ካላችሁኝ እኔም ….‹ ..ለሌሎች ድርጅቶች ተብሎ አይከለከልምን…›› ምን አመጣው እላለሁ፡፡ ከዜናው የምስክርነት ገለጻዎች ይህን ጥያቄ እንዳነሳ ያስገደዱኝን ልጥቀስ፡፡

1ኛ/ አንድ ተረጅ ነስተው ‹‹ …. ዕርዳታው ያለአድልዎ ኅብረተሰቡ በወከላችው …. የ1 ለ5 አደራጆች…. መከፋፈሉን ›› ሌላውም አስከትለው ‹‹ ይህ ለሁላች የመጣ ስለሆነ …ለሌሎች ድርጅቶች አባላት ተብሎ አልተከለከለም…›› በማለት ያለአድልዎ ስለመከፋፈሉ መስክረዋል፡፡
2ኛ/ የአገርአቀፍ ፓርቲዎች ምክር ቤት አባላት /ካየኋቸው– አቶ አየለ ጫሚሶ፣ አቶ ግዑሽ፣ አቶ መሳፍንት ፣ አቶ ትግስቱ አወሉ፣…./ በተገኙበት ባደረጉት የምስክርነት የመስክ ጉብኝት ‹‹ የዕርዳታ ክፍፍሉ ‹ፍትሃዊ› ፣ መጠኑም ዓለምአቀፍ ስታንዳርድ የጠበቀ መሆኑን፣ እንዲሁም በድርቁ ምክንያት ‹‹አንድም ሰው እንዳልተሰደደ ›› ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡

ከነዚህ የምስክርነት ገለጻዎች የተገነዘብኩት/የታዘብኩት ፡–
1ኛ/ አስቀድሞ ነገር ለተራበ ወገን በሚከፋፈል ዕርዳታ ያለአድልኦ የሚለው ለምን ያስፈልጋል፣ በተራበ ወገን መካከል ‹የነፍስ አድን› ተግባር እንጂ እራሱ ገዢው ፓርቲ የፖለቲካና ደህንነት አደረጃጀት ያለውን ‹ አንድ ለ አምስት/ 1 ለ5/› ምን አገባው? ደግሞስ ማን ለዚህ አደረጃጀት የህዝብ ውክልና ሰጠው ?
2ኛ/ ቀድሞ ነገር ‹ረሃብ › ፓርቲ አለው እንዴ…? እናስ ‹‹ … ለሌሎች ድርጅቶች አባላት ..›› ማለት ምንድንነው ? ይህ ከዓመታት በፊት በደቡብ ክልል እርዳታ እህል በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ተከለከሉትን፣ አሁን በዚሁ የክፉ ቀን/ረሃብ ጊዜ ከትግራይ የ‹ዐረና› አባላት ላይ የደረሰውን ከእርዳታ ማግለል አያስታውስም ? ስንት ጊዜ ይዋሹናል አያስብልም?
3ኛ/ በድርቁ ‹‹አንድም ሰው አልተሰደደም.. ማለት ከትግራይ ውቺ በአዲስ አበባ መንገድ ላይ ያሉትን ከተሞች አልፈው አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ልጆች አስከትለው ሲለምኑ የምናያቸው የትግራይ እናቶችና አባቶች ለቱሪዝም መጥተው የሆቴሎች አድራሻ ጠፍቶባቸው የሚንከራተቱ ናቸው ማለት ነው ? ከሆነስ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎችን ለምን አላሳያቸውም ?

እንዲያው በተራበ ወገን ላይ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ አይቶ ማለፍ አላስችል ብለኝ፣ ምነው የትግራይ ህዝብ በዚህ የዕርዳታ ክፍፍል ላይ ከህወኃት ጋር ችግር ውስጥ ገብቷል እንዴ የሚለውን ቢያስጠረጥረኝ እንጂ ‹ የነዋሪዎችም › ሆነ ‹ የፓርቲ የምክር ቤት አባላት › ምስክርነት ህዝቡ ከደረሰበትና ከሚያየው የበለጠ ሚዛን እንደማይደፋ ፣ በ‹ዐረና› ፓርቲ አባልነታቸው የተገደሉ፣ የታሰሩ. የተሰደዱና ለስቃይና እንግልት የተዳረጉትን በሥም፣ በአድራሻና በተፈጸመባቸው ህገወጥ ድርጊት ለይቶ ‹‹ዐረና›› በየጊዜው ያቀረበውን ሪፖርት ሳላነብ፣ በአጠቃላይም ከረሃቡና የዕርዳታ ክፍፍል ጋር በተያያዘ እስከዛሬ የተባለውንና ‹የብርቱካን እናት ›› ላይ የተፈጸመውን በመዘንጋት አይደለም፡፡

በወገን ስቃይ ከሚነዛ ነጭ ፕሮፖጋንዳ የጸዳ ለአገራችንና ህዝባችን የሚበጀውን ያሰማን፣ በቸር ያገናኘን፡፡

ሰኔ 15/08. UNITE.

Loading...