የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የመጨረሻ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው

fron1659በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የምክር ቤት አባል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ፣ የመጨረሻ ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ቡድን ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ለአራተኛ ጊዜ ያቀረበው ተጨማሪ የ28 ቀናት ጥያቄ፣ ከተጠርጣሪው ጠበቃ ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

የአቶ ዮናታን ጠበቃ መርማሪ ቡድኑ ለሦስት ጊዜያት በድምሩ 84 ቀናት እንደተፈቀደለት በማስታወስ፣ በእነዚህ ጊዜያት ምርመራውን ሊያጠናቅቅ እንደሚችል በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ እንዳስፈላጊነቱ መርማሪው አራት ጊዜያት ሊጠይቅ እንደሚችል ይገልጻል እንጂ፣ ፍርድ ቤት የተጠየቀውን መፍቀድ እንዳለበት አስገዳጅ እንዳልሆነ አስረድተው ለአራተኛ ጊዜ የተጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲከበርም ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በበኩሉ ከተጠርጣሪው ቃል ተቀብሎ ያጠናቀቀ ቢሆንም፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረውና የሚይዛቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉ በማስረዳት፣ የቀረውን ምርመራ አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ የሚያስረክብበት ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመናገር ተከራክሯል፡፡

የሁለቱን ወገኖች ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የጠበቃውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የመጨረሻ ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.