ቁም ነገር መጽሄት – ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኜ እየኖርኩ ነው

tadsse
አትሌት መቶ አለቃ ታደሠ

አትሌት መቶ አለቃ ታደሠ ሰጥ አርጋቸው እድሜያቸው ገፍቷል፡፡ 78ኛ አመታቸውን ይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ የሩጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ከወርቅ እስከ ነሐስ ሜዳልያዎች አምጥተዋል፡፡ በወጣትነት ዘመናቸው ለሃገራቸው ክብርን አስገኝተዋል፡፡ ዋሚ ቢራቱ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ የትነበርክ በለጠ፣ ደምሴ ወልዴ፣ ከበደ ባልቻ፣ መገርሳ ቱሉና መሃመድ ከድርን ከመሳሰሉት ጋር ከ1960ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ በተለያዩ ርቀቶች ሲሮጡ ነበር፡፡

የመከላከያ ስፖርት ክለብ (የቀድሞው መቻል) አትሌት የነበሩት መቶ አለቃ ታደሰ ሰጥ አርጋቸው በጉብዝና ወራታቸው ላባቸውን ጠብ አድርገው የሃገራቸውን ባንዲራ በአለም ፊት ከፍ ቢያደርጉም አሁን በስተርጅና ጊዜያቸው፣ ጉልበታቸው ሲደክም ዞር ብሎ እንኳ የሚያያቸው ሰው አጥተዋል፡፡ የ500 ብር ጡረተኛው መቶ አለቃ ታደሠ 550 ብር ከሚከፍሉባት፣ ለማድቤት እንኳ በማትመጥን ጠባብ ቤት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ልጆቻቸውን ማሳደግ የሚችሉበት አቅም ስለሌላቸው ሁለቱን በየዘመድ አዝማዱ በትነዋቸዋል፡፡

አሁን ያላቸው ሃብት በየሃገራቱ ተወዳድረው የሰበሰቧቸው ሜዳሊያዎች ብቻ ናቸው፡፡ በስፖርት የጠበቁት ተክለ ሰውነታቸው በኑሮ ሸክም ምክንያት መጉበጥ ጀምሯል፡፡ ‹‹ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኜ እየኖርኩ ነው›› ይላሉ፡፡ ቃለ ምልልሱን ሳደርግላቸው በየመሃሉ እምባና ሳግ እየተናነቃቸው ሃሳባቸውን በአግባቡ መቋጨት እንኳን ይቸገሩ ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- በውጭ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጡት መቼ ነበር?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- መጀመሪያ የተሳተፍኩት 53 የአፍሪካ ሀገራትን ወክዬ በሜክሲኮ በተደረገው ውድድር ነበር፡፡ ከ20 ቀን በላይ የፈጀና እንደኦሎምፒክ ያለ ውድድር ነው፡፡ አፍሪካ ራሱን ችሎ፣ አውሮፓ ራሱን ችሎ፣ ሌላውም አህጉር ራሱን ችሎ ነበር የሚሳተፈው፡፡ በዚያ ውድድር በማራቶን አንደኛ ሆኜ ነው ያሸነፍኩት፡፡ የመጨረሻውን 21 ኪሎ ሜትር ብቻዬን ከሞተር ጋር ነበር የሮጥኩት፡፡
ቁም ነገር፡- በምን ያህል ሰአት ነበር ውድድሩን የጨረሱት ሰዓቱን ያስታውሱታል?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- ሁለት ሰዓት ከአስራ አምስት ደቂቃ ከ25 ሰከንድ ነበር የፈጀብኝ፡፡
ቁም ነገር፡- በመቼ አመተ ምህረት ነው?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- በ1966 አካባቢ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- በኦሎምፒክ ውድድርስ ተሳትፈው ያውቃሉ?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- ለኦሎምፒክ ውድድር ሰአት ያሟላሁት በ1976 በፈረንጆቹ ለተደረገው የሞንትሪያል ኦሎምፒክ ነበር፡፡ እዚህ መጽሔት ላይ እንደምታየው (በሞንትሪያል ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችንና ልዑካን ቡድኑን ዝርዝርና ፎቶ የያዘውን መጽሔት እያሳዩኝ) ወደ ካናዳ ሞንትሪያል ሄደን ነበር፡፡ ለ15 ቀናት ያህልም ቆይተናል፡፡
ቁም ነገር፡- በውድድሩ ግን አልተሳተፋችሁም ነበር?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- ከተዘጋጀን በኋላ አቶ ይድነቃቸው በውድድሩ አንሳተፍም አሉን፡፡
ቁም ነገር፡- ምንድ ነበር ምክንያቱ?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- በዘረኝነት ጉዳይ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን ዘረኝነት በመቃወም ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት አንሳተፍም ብለው ውድድሩን አቋርጠው ነበር፡፡ እኛም ወደሃገራችን ተመለስን፡፡ የሚገርመው ነገር ለሞንትሪያል ኦሎምፒክ ሲባል ለአንድ አመት ያህል ሆቴል ውስጥ ሆነን ነው ልምምድ ስንሰራ የቆየነው፡፡
ቁም ነገር፡- ሌሎች የተሳተፉባቸው ውድድሮችስ የትኞቹ ናቸው? የሚያስታውሷቸውን ይንገሩኝ?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ፖርቶሪኮ የሚባል ሃገር ሄጄ ተወዳድሬ ነበር፡፡ የቡድን ጨዋታ ነበር፡፡ 6 ሆነን ነው የተሳተፍነው፡፡ ሻምበል ምሩፅ፣ እኔ፣ መሃመድ ከድር፣ ሾላና ሌሎች ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ውድድር ነበር፡፡ ዳገትና ቁልቁለት አለው፡፡ ሻምበል ምሩፅ በውድድሩ አንደኛ ሲሆን እኔ ሁለተኛ ሆኜ ነው የጨረስኩት፡፡ የተዘጋጀውን ዋንጫ በእኛ እጅ አስገባነውና ለፌዴሬሽን አምጥተን አስረከብን፡፡ የ21 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ነበር፡፡ ጅቡቲም የግማሽ ማራቶን ሩጫ ተወዳድረን ነበር፡፡ በጫማ ቀለም እየተደበደብን ነው ውድድሩን የጨረስነው፡፡ አልጄሪያ በተደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይም ተወዳድሬ ነበር፡፡ በማራቶን ዛንዚባር ላይ ሮጠን ገብሬ ጉርሙ አንደኛ ሲሆን እኔ ሁለተኛ ሆኜ ጨርሻለሁ፡፡ አቴንስ ላይ ደግሞ ደረጀ ነጂ አንደኛ እኔ ሁለተኛ ከበደ ባልቻ (አሁን ካናዳ ነው ያለው) ደግሞ ሶስተኛ በመሆን አሸንፈናል፡፡ ሌሎች ብዙ ሃገራትም ሮጫለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- በማራቶን ብቻ ነበር የሚወዳደሩት?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- በማራቶን ብቻ ሳይሆን በግማሽ ማራቶንና በ12 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድርም እሳተፋለሁ፡፡ 9 ኪሎ ሜትርም እሮጥ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከነባር የማራቶን ሯጮች እኔ ብቻ ነው ያለሁት፡፡
ቁም ነገር፡- አሁንም በተለያዩ ውድድሮች ታላቁ ሩጫን ጨምሮ ይሮጣሉ… በዚህ እድሜዎም ከስፖርቱ አልራቁም ማለት ነው?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- አዎ እሮጣለሁ፤ በደንብ ነው የምሮጠው፡፡ በእኔ እድሜ ያለ ሰው ሮጦ አይቀድመኝም፡፡
ቁም ነገር፡- የኑሮ ሁኔታዎስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- እኔ መውደቂያ የለኝ፣ መጠለያ የለኝ፣ ብዙ ችግር ላይ ነው ያለሁት፡፡ ቁሜ መሄዴን አትይ፡፡ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኜ ነው ያለሁት፡፡
ሰርቻለሁ፣ ደክሜያለሁ፣ ለኢትዮጵያ ባንዲራ በስነስርአት አገልግያለሁኝ ግን እንዳገለገልኩት አላገኘሁም፡፡ ዝም ብዬ ወድቄ ነው የቀረሁት፡፡ ምናልባት ሃገር ወዳድ ሰው አለ፣ ስፖርት አፍቃሪም አለ፤ ያለሁበትን አይተው ድጎማ ሊያደርጉልኝ፣ ሊደግፉኝ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ስንት ልጆች አሉዎት?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- አራት ልጆች ናቸው ያሉኝ፤ ሁለቱን አቅሜ ስላልቻለ ወደ ዘመድ ላኳቸው፡፡ አሁን እኔ ጋር ያሉት ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ ሁሉንም ልጆቼን አንድ ላይ አድርጌ እንዳላሳድግ ምን ላይ ይኖራሉ፤ምን ላይ ይተኛሉ፤ ምን ይበላሉ፡፡ አልቻልኩም፡፡ ብዙ ችግር ላይ ነው ያለሁት፡፡ ሌላው ይቅር የአንገት ማስገቢያ መጠለያ ካገኘሁ ልጆቼን ሰብስቤ ከጎኔ ሆነው እንዲማሩ አደርግ ነበር፡፡ ግን በየፊናው ተበትነው በቃ እኔም ከሞትኩ አንገናኛም (እያለቀሱ)
ቁም ነገር፡- በተለያዩ ውጭ ሀገራት ተዘዋውረው ሲሮጡ እዚያው ለመቅረት አስበው አያውቁም ነበር?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- ብዙ ጊዜ እዚያ እንድንቀር ይለምኑ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከሻምበል ማሞ ወልዴ ጋር ስፔን ሃገር ሄደን የመኪና ቁልፍ እንስጣችሁ… ቤት እንስጣችሁ አትሂዱ ሲሉን ነበር፡፡ታዲያ ሻምበል ማሞ ጎበዝ ነው… ቆራጥ ነው፡፡ አልፈልግም… ሃገሬን ጥዬ አልሄድም ይል ነበር፡፡ እኔም ዘወር በሉ ነው የምላቸው፡፡
የትኛውም ቦታ ስንሄድ እንድንቀር ይጠይቁናል፡፡ እዚህ ስራ እናሰጥሃለን ይላሉ፡፡ ግን ሃገሬን ጥዬ አልኖርም፡፡ የምታበላኝ የምታጠጣኝን ሃገር ጥዬ አልሄድም፣ ሞቴንም ምኔንም ሃገሬ ላይ ነው የሚሻለኝ ብየ እምቢ እያልኩ ነው እንጅ በጣም ይለምኑን ነበር፡፡ አቅም ባለን፣ ጉልበት ባለን ጊዜ ማለት ነው፡፡ ግን ያሳደገችኝን ሃገር ከድቶ መሄዱም ይከብዳል፤ ጥሩ አይደለም፤ አይቀናም፡፡
ቁም ነገር፡- በናንተ ጊዜ ሲሮጡ ከነበሩ አትሌቶች መካከል የሚያገኟቸው አሉ?
መቶ አለቃ ታደሠ፡- ብዙዎቹ አሁን በሕይወት የሉም፡፡ ጥቂት አትሌቶች ናቸው፡፡፡ አልፎ አልፎ አገኛቸዋለሁ፡፡ እና እንዲያውም አንዳንዶቹ ሲያገኙኝ ‹‹ታዴ አለህ… አልሞትክም›› ይሉኛል፡፡ እንድሞት ነው ወይ የምትፈልጉት እላቸዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር አለ የሚወስነው እሱ ነው እላቸዋለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አመሠግናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- አትሌት መቶ አለቃ ታደሰ ሰጥ አርጋቸውን መርዳት የምትፈልጉ በስልክ ቁጥር 0943108106 ልትደውሉላቸው ትችላላችሁ፡፡
ወገኖቼ ከኝህ አባት ጎን እንቁም አምላክ ብድራቱን ይከፍላችሃል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.