በአዲስ አበባ የታክሲዎችን የስራ ማቆም አድማ ጥሪ ተከትሎ ባለስልጣኑ መመሪያውን ማራዘሙን ይፋ አደረገ

ታክሲ

(ሳተናው)  ከሶስት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ባልታወቁ ሰዎች ለታክሲ አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች የተበተነ ወረቀት ከነገ ሰኞ ማለዳ ጀምሮ በከተማይቱ የሚገኙ ታክሲዎችና ሃይገር አውቶብሶች የስራ ማቆም አድማ በመምታት አዲሱን የትራንስፖርት መመሪያ እንደሚቃወሙ አስታውቆ ነበር፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በከተማዋ በከፍተኛ ደረጃ እየተመዘገበ ይገኛል ያለውን የተሸከርካሪዎች አደጋ ለመቀነስ ያግዘኛል ያለውን የቅጣት መመሪያ በማውጣት ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ በስራ ላይ ለማዋል ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡
መመሪያው በመስኩ በተሰማሩ አሽከርካሪዎችና የተሸከርካሪዎች ባለቤቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ቅጣትን በማክበድና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላትን በማስፈራራት አደጋን መቀነስ አይቻልም የሚሉ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች የመመሪያዎቹ አላማ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ነው በማለት ነቀፌታ ይሰነዝራሉ፡፡
በታክሲና በሀይገር አውቶቢሶች ባለቤቶች ስም በሚንቀሳቀሱ ማህበረት ሳይጠራ አይቀርም የተባለለት የስራ ማቆም አድማ በአዲስ አበባ ከፍተኛ መነጋገሪያ በመሆን የሰነበተ ቢሆንም ከሰዓታት በፊት የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በአገር ውስጥ ለሚገኙ የመንግስት ሚዲያዎች በላከው መግለጫ ‹‹የታክሲ ማህበራት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መመሪያ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ጊዜ ለሶስት ወራት አራዝመናል››ብሏል፡፡
መስሪያ ቤቱ ለሶስት ወራት የሚራዘመው መመሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይትና መግባባት ከተደረሰበት በኋላ በስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ማለቱም ተሰምቷል፡፡ የስራ ማቆም አድማውን የጠሩ አካላት የመመሪያውን መራዘም እንደ አንድ ትልቅ ድል ሊቆጥሩት እንደሚችሉ የሚጠቅሱ ሰዎች መስሪያ ቤቱ መመሪያውን እስከመጨረሻው ማንሳቱን እስኪገልጽ ድረስ በአድማው ሊገፉበት ይችላሉ ይላሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.