እንደገና እንጋባ (ዳንዔል ክብረት)

ዳንዔል ክብረት
ምን ብዬ ጠርቼሽ ልቀጥል
daniel-kibret-300x207
ዳንዔል ክብረት
ለካስ እስካሁን የተዋደዱና የተጣሉ ሰዎች የሚጠራሩበት የቅጽል ስም እንጂ የተለያዩ፣ ግን ያልተጣሉ ሰዎች የሚጠራሩበት የቅጽል ስም የለንም፡፡ መቼም አንዳንዱን ነገር የምንረዳው ሲገጥመን ብቻ ነው፡፡ በኑሯችን ውስጥ የሚጎድሉ፣ ነገር ግን ልብ የማንላቸው ጥቃቅን ነገሮች ብቅ የሚሉት ታላላቅ ነገሮችን አጥተን ቦታው ክፍት መሆኑን ስናረጋግጥ ብቻ ነው፡፡ ‹ውዴ› ብዬ እንዳልጠራሽ ተለያይተናል፤ ‹አንቺ ምናምን› ብዬ እንዳልጠራሽ ደግሞ እኔና አንቺ ተለያይተናል እንጂ ልቤና ልብሽ መለያየቱን እንጃ፡፡ ብቻ ለማንኛውም ዝም ብዬ ሐሳቤን ልቀጥል፡፡

ሰሞኑን ካንቺ ለመጨረሻ ጊዜ ተለያይቼ ከሌላ ሰው ጋር ስለ መኖር ሳስብ ነበር፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ አስቤያቸው የማላውቅ ሐሳቦች ወደ ልቡናዬ እየመጡ ይሞግቱኝ ጀምረዋል፡፡ አንዱ ሞጋች እንዲህ አለኝ፡፡ ወደህ፣ ፈቅደህ፣ አፍቅረህ ካገባሃት፣ አብረሃትም ለዚህን ያህል ዓመት ከኖርካት፣ ከምታውቅህና ከምታውቃት፣ ካነበበችህና ካነበብካት ሴት ጋር አብረህ ለመኖር ካልቻልክ ከሌላዋ ጋር አብረህ ለመኖርህ ምን ዋስትና አለህ? ይህችንምኮ ያገባሃት አንተው ነህ፤ እንደ ጥንቱ ወላጆችህ አጭተውልህ ቢሆን ኖሮ በእነርሱ ታመካኝ ነበር፤ ያመጣሃትም የተጣላሃትም አንተው ነህ፤ ለእኔ የተሻልሽው አንቺ ነሽ ብለህ፤ ዐውቄሻለሁ፤ ተስማምተሽኛል ብለህ ያገባሃት አንተው ነህ፤ ያስገደደህ አካል አልነበረም፤ እንዲህ ብለህ ካገባሃት ሴት ጋር መኖር ለምን አቃተህ? እንዲህ ብለህ ካገባሃት ሴት ጋር መኖር ያቃተህ ሰው ከሌላዋ ጋር ለመኖርህ ምን ዋስትና አለህ? 

 

አሁን ልፍታት፣ ልለያት ከምትላት ሴት ጋር ስትገናኝ የምታወራውን ነው ከሌላዋ ሴትም ጋር የምታወራው፤ አሁን ልለያት የምትላትን ወድጃታለሁ እንደምትለው ነው ሌላዋንም ወደድኩ የምትለው፤ አሁን ለመለየት አፋፍ ላይ የደረስካትን ሴት ባየህበት ዓይን ነው ሌላዋንም የምታየው፤ ከዚህችኛዋ ይልቅ ከዚያችኛዋ ጋር እንደሚሳካልህ በምን ዐወቅክ? ይለኛል ሞጋቹ፡፡ እዚህ ጨው ጎድሎ እንደሁ እዚያ ሽንኩርት ይጎድላል፣ እዚህ በርበሬው አርሮ እንደሆነ እዚያ ዘይቱ ይንጨረጨራል፣ እዚህ ወጡ ቀጥኖ እንደሆን እዚያ እንጀራው ይቆመጥጣል፣ እዚህ አልጋው አልመች ብሎ እንደሆነ እዚያ ወንበሩ ይቆረቁራል፣ እዚህ አንሶላው ቢቀዘቅዝ እዚያ ፍራሹ ይጎረብጣል፤ ሁሉም ጋ ጎደሎ አለ፡፡ ሽሽትህ አንዱን ጎደሎ በሌላ ጎደሎ ለመተካት ነው ወይ? ከነብር ሸሽተህ ከአንበሳ ለመጠለል ነው ወይ? ከዝናብ ሸሽተህ እሳት ለመግባት ነው ወይ? ከጉድጓድ አመለጥኩ ብለህ አዘቅት ለመውደቅ ነው ወይ? ይለኛል ሞጋቹ፡፡ ያቺንስ በምን አረጋገጥካት? ልክ እንደዚህቺኛዋ ከውጭ አይደለም ወይ ያወቅካት? ስትገባ ምን እንደሚያጋጥምህ ማን ነው ያረጋገጠልህ? ብሎ ይሞግተኛል፡፡ 

 

ለመሆኑ ጎደሎ የሌለበት፣ ሁሉም የተሟላለት ሰው አለ ወይ? የትዳር ዓላማው መሟላት አይደለም ወይ? በሂደት እየገጠሙ፣ እየገጠሙ፣ እየገጠሙና እየተሟሉ መሄድ አይደለም ወይ? የስንዴው መዘራት፣ መብቀል፣ መታጨድ፣ መወቃት፣ መለቀም፣ መፈጨት፣ መነፋት፣ መቦካት፣ በእሳት መብሰል አይደለም ወይ ዳቦውን ዳቦ አድርጎ የሚያወጣው? ይኼ ሁሉ ሂደት ስንዴውን ከእንክርዳዱ ለመለየት፣ ፍሬውን ከገለባው ለመነጠል፣ ሽርክቱን ከላመው ለመለየት፣ የተለያየውን የስንዴ ቅንጣት አንድ ለማድረግ፣ አንድ አድርጎም ለማዋሐድ፣ አዋሕዶም ለማብሰል አይደለም ወይ ጥቅሙ? እንደ መዘራቱ ሁሉ መታጨዱ፣ እንደ መሰብሰቡ ሁሉ መወቃቱ፣ እንደ መበጠሩ ሁሉ መፈጨቱ፣ እንደ መቦካቱ ሁሉ በእሳት መጋገሩ አስፈላጊ አይደለም ወይ? ይለኛል ሞጋቹ፡፡ 

 

ትዳርስ እንዲህ አይደለም ወይ? በጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙት ክፉውም ደጉም አይደሉም ወይ ትዳርን ትዳር የሚያደርጉት?የሚያዋሕዱት? የሚያበስሉት? ገበሬው እህሉ ወድቆ እንዳይቀር እንጂ እንዳይታጨድ አይደርገውም፡፡ ጋጋሪዋም ዳቦው እንዳያር እንጂ እንዳይበስል አታደርገውም፡፡ ትዳርስ እንዲህ አይደለም ወይ? እህሉ ወድቆ ቢቀር ገበሬው፣ ዳቦውም ቢያርር ጋጋሪዋ አይደለችም ወይ ተጠያቂው? የሃይማኖት አባቶች ምን ይላሉ፡፡ አዳም ቢያጠፋም እግዜር ግን ‹ፍጠረኝ ሳይለኝ ፈጥሬው ልተወው አይገባም› ብሎ የፈጠረውን ሰው ራሱ ሊያድነው ሰው ሆነ፤ የአዳምን ቅጣት ራሱ ወሰደ፡፡ 

 

አንተስ ትዳሩ ‹መሥርተኝ› ብሎሃል? ጎጆው ቀልሰኝ ብሎሃል? ራስህ አይደለም የጀመርከው? ስለዚህ ትዳርህን የመዋጀት ግዴታ አለብህ፡፡ ችግሩን የመፍታት ግዴታ አለብህ? መሥርተኝ ሳይልህ የመሠረትከውን ትዳር፣ ውለደኝ ሳይሉህ የወለድካቸውን ልጆች ትተህ የመሄድ ሰዋዊ መብት ማን ሰጠህ? ለመሆኑ ይኼ ነጻ መውጣት ነው ወይስ ሽሽት? ችግር መፍታት ነው ወይስ ሽንፈት? እያለ ይሞግተኛል፡፡ 

 

በዚህ ጊዜ ነው አንድ ወዳጄ ‹‹ጓደኝነት በመኪና እንደመሄድ ነው፡፡ ቢደብርህ የፈለግክበት ቦታ ላይ ወርደህ በእግርህ ትሄዳለህ፡፡ አቁምልኝ ማለት ብቻ ነው፡፡ ቢበዛ ፖሊስ ይቀጣሃል፡፡ አለቀ፡፡ ትዳር ግን በአውሮፕላን እንደመሄድ ነው፡፡ ዝም ብለህ ደበረኝ፣ ሰለቸኝ፣ መረረኝ ብለህ የሆነ ቦታ ላይ መውረድ አትችልም፡፡ አውሮፕላኑ እስከሚሄድበት ቦታ ድረስ የመሄድ ግዴታ አለብህ፡፡ በመኪና ስትሄድ ዕንቅልፍህ ቢመጣ አቁመህ ወርደህ ትተኛለህ፤ በአውሮፕላን ግን እዚያው ነው የምትተኛው፡፡ በመኪና ስትሄድ ቢርብህ ወርደህ ሆቴል ገብተህ ትመገባለህ፡፡ በአውሮፕላን ስትሄድ ግን እዚያው የሚሰጥህን ነው የምትበላው፡፡ በመኪና ስትሄድ አየር መቀበል ቢያምርህ ከመኪናህ ወርደህ ወደ አንድ ነፋሻ ቦታ ትጓዛለህ፡፡ በአውሮፕላን ግን የሚሰጥህን አየር ነው የምትተነፍሰው፡፡›› ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ 

 

እስኪ አስቢው ወላጆቻችን በዘመናት ያዳበሯቸው የትዳር ችግሮች መፍቻ መንገዶች ነበሩ፡፡ እነዚህን መንገዶች ‹ኋላ ቀር ናቸው፣ የሴቶችን መብት የሚጨቁኑ ናቸው፣ የልጆችን መብት የማያስከብሩ ናቸው፣ የወንድ የበላይነትን የሚያነግሡ ናቸው፣ ኃይልና ጉልበትን የሚቀላቅሉ ናቸው› ብለን አወገዝናቸው፡፡ ይሁን፣ አንዳንዶቹ እንደሚባለው ናቸው፡፡ ችግሩ ችግሩን ማወቃችንና ማውገዛችን አልነበረም፡፡ በሌላ፣ እኛ ዘመናዊና የተሻለ በምንለው መፍትሔ አለመተካታችን ብቻ ነው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ያለውን ዕቃ ‹ኋላ ቀር ነው› ብለን አስወጥተን ጥለን ቤቱን ወና ብናደርገው የአይጥ መጨፈሪያ ነው የሚሆነው፡፡ አንድን የኖረ መፍትሔ አስወግደን በሌላ ካልተካነውም ችግሩን ያለ መፍትሔ ነው የተውነው፡፡ አንድን ነገር ማስወገድ ማለት በተሻለ ነገር መተካት ማለት አይደለም፡፡ መተካትም እንደማስወገድ ቀላል አይደለም፡፡ ይኼው እንደምታዪው ለኢራቆች ሳዳምን ማስወገድ፣ ለሊቢያዎችም ጋዳፊን መግደል ቀላል ነበረ፡፡ የተሻለ ማምጣት ግን እንደ ማስወገዱ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ 

 

እኔና አንቺም እንዲሁ የሆንን ይመስለኛል፡፡ እኛ ከወላጆቻችን በልጠን ዘመናዊ ያደረግነው ነገር ቢኖር ፍችን ራሱን ይመስለኛል፡፡ አሁን ፍቺ ዘመናዊ ሆኗል፡፡ እጅግ በጣም ቀሏል፡፡ ዘመናዊ ትዳር፣ ዘመናዊ መፍትሔና ዘመናዊ አኗኗር ግን ገና አላመጣንም፡፡ በዚያ እኛ ባልነው የትዳር መርሕ ውስጥ ሆነው ሃምሳ ዓመት፣ ስድሳ ዓመት፣ ሰባ ዓመት የኖሩ ባለ ትዳሮች እያየን ነው፡፡ ዘመናዊ በተባለው ትዳር ውስጥ ግን ዐሥር ዓመት ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ታድያ ምኑን ዘመንነው? ምናልባት ያለፉትን ነገሮች ኋላ ቀር ናቸው እያልን ስናስወግድ አብረን ያስወገድነው ‹የትዳር ዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት› ይኖር ይሆን? 

 

ይህንን ሁሉ የምለው ነገሮችን በረጋ ኅሊና፣ በሰከነ ልቡና፣ በበሰለ አእምሮ፣ እንደገና ማየት እንችል እንደሆነ ብዬ ነው፡፡ ነገሮችን እንይና፣ እናርምና፣ እንሞረድና፣ እንደገና እንጋባ፡፡ እንዲያውም ትዳር ለመመሥረት አሁን ነው የተሻለው ጊዜ፣ የተሻለው ሁኔታ፡፡ ችግሩ በደንብ አብስሎናላ፡፡ 

 

በእውነቱ እዚህ ላይ አንድ ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ፡፡ ‹‹ባለቤቴ›› ስለሚለው ነገር እጽፋለሁ ብዬ ነበር፡፡ ለካስ እርሱ ቃል ያላወቅነው ጥልቅ ነገር አለው፡፡ ለዚህ ሲባል ብቻ አንድ የደብዳቤ ዕድል ስጭኝ፡፡ 

 

በሦስተኛው ደብዳቤዬ እነግርሻለሁ፡፡ 

 

ያንቺው (የሆንኩትም፣ የነበርኩትም፣ ምናልባትም የምሆነውም) 

 

 

Source: Danielkibret

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.