ድህረ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያ፤ ከታሪክ ምን እንማራለን? – ደስታው አንዳርጌ (ዶ/ር)

የካቲት ፩ ቀን ፪ ሺ ፰

DC2ሆ ብለን ተነስተን ወያኔን እናስወግድ ይላሉ። ለውጥ መፈለግ ተፈጥሮሯዊ ነው። ወያኔን የመሰለ መሰሪና አደገኛ ቡድን ይቅርና በጎ የሚባል መንግስትም ቢሆን እድሜው ሲንዘላዘል ያንገሸግሻል። ለውጥ ግን በራሱ ግብ አይደለም። ለውጥማ ተፈጥሯዊ ነው፤ ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል። ተፈጥሮ ግን ለውጡን መልካም የማድረግ ግዴታ የለባትም። ለውጥን በሚፈለገው መንገድ መቀየስ የሰወች ድርሻ ነው። ያ ደግሞ ጥበብ፣ አርቆ አሳቢነትና ጠንካራ አደረጃጀት ይጠይቃል። ከምንም በላይ ዘላቂ አገራዊ ጥቅምን ከስልጣን ጥም ማስቀደም የግድ ይላል። ያ ካልሆነ ለውጥ የከፋ አደጋም እንደሚጋብዝ ታሪክ ቁልጭ አርጎ ያሳየናል (ከታሪክ እንማራለን ወይ ራሱን የቻለ ጥያቄ ሆኖ ማለቴ ነው)። የራሳችን ታሪክ ለጊዜው ወደኋላ እናቆየውና ለንጽጽር ያህል የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ላንሳ፤

ሀ. ከአረብ ጸደይ ምን እንማራለን?

የዛሬ አምስት አመታት ገደማ የአረብ ስፕሪንግ በቱኒዝያ፣ ግብጽና ሊብያ ድንገት ተቀጣጠለና ለውጥ ወለደ። አሁን ቱኒዝያውያን ቤን አሊን ሊናፍቁ አይችሉም። ማህበራዊ ችግሮቻቸው ባይፈቱም ቢያንስ የፖለቲካ ነጻነት አግኝተዋል። ግብጾችም ለነጻነት ነበር የታገሉት፤ ነጻነት ግን ላም አለኝ በሰማይ እንደሆነባቸው ነው። ሊቢያውያን በአንጻሩ የፖሊቲካ ነጻነት ሊያገኙ ቀርቶ በጋዳፊ ጊዜ የነበራቸው ምቾትና በሰላም ውሎ የመግባት ነጻነት አጡ። ከምንም በላይ አሁን ሊቢያ የለችም። ወደፊትም ላትመለስ ትችላለች። አገሪቱን ተቀራምተው የሚፈነጩባት ምን አይነት አውሬወች እንደሆኑ መቸም ልንረሳው አንችልም።

ቱኒዝያውያን አተረፉ፣ ግብጾች ሌላ ሙባረክ አገኙ፣ ሊቢያውያን ከሰሩ። ምን ለያያቸው? ብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለማሳያ ግን ሶስት ምክንያቶችን እንይ። በመጀመሪያ ምዕራባውያን በሶስቱም አገራት ላይ ያላቸው ፍላጎት የተለያየ ነው። ከዚህ አንጻር ለምሳሌ ግብጽ ውስጥ መረጋጋት እንጂ ዲሞክራሲ እንዲኖር አይፈለግም። አሜሪካ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለዚያች አገር ጦር ሀይል የምታፈሰው ዲሞክራሲ እንዲያብብ በማሰብ አይደለም። ግብጻውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በፈቃዳቸው በመረጡት መሪያቸው ላይ ምን እንደደረሰ አይተናል። የማይጠበቅ ግን አልነበረም (፹ በመቶው ግብጻዊ የአለም ቀንደኛ የሰላም ጸር አሜሪካ ነች ብሎ ያምናል)። ሊቢያ በበኩሏ የነዳጅ ሀብቷ መርገምት ሆነባት። በዋነኝነት ግን የሊቢያ ህዝብ ከሌሎች ሁለት አገራት በተለየ መልኩ በጎሳ የተቧደነ በመሆኑ የጋራ ራዕይ መንደፍ አልቻለም። ከመጀመሪያው እንደ ቱኒዝያውያን በሰለጠነ መንገድ መብታቸውን ከመጠየቅ ይልቅ በጎሳ ተቧድነው ጋዳፊን በየትኛውም መንገድ ጥሎ የአገሪቱን የነዳጅ ሀብት መቀራመት ላይ ያነጣጠረ ነውጥ ውስጥ ገቡ። እነዚህ ቡድኖች ለስልጣንና ሀብት መቀራመት እንጂ ለአገራቸው እንደማይገዳቸው ግልጽ የሆነው ከጅምሩ መሳሪያ አንስተው ምእራባውያን አገራቸውን በአየር እንዲደበድቡላቸው ሲማጸኑ ነበር።

የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የቱን ይመስላል?

amtseየሶስቱን አገራት ምሳሌ ያነሳሁት ወያኔ ቢወድቅ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለመገመት እንዲረዳን ነው። መነሻዬ ወያኔ የሞት አፋፍ ላይ ነው የሚል የዋህ ግምት አይደለም፤ ወያኔ በዋዛ ስልጣን ይለቃል ብለው የሚያስቡ ወያኔን አያውቁትም። ግን አንድ ቀን መውደቁ አይቀርም። ወያኔ የወደቀ ለታ ምን እንደሚፈጠር መገመት የሚችል አለ? እንደ ቱኒዝያውያን እናተርፋለን ወይንስ እንደ ሊቢያውያን (የመንንና ሶሪያንም ጨምሩ) ወደ ትርምስ እንገባለን? ኢትዮጵያ እንደ አገር ትቀጥላለች? በሌላ አነጋገር የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከሶስቱ አገራት ውስጥ ከየትኛው ጋር ይቀራረባል? ስለ ኢትዮጵያ ለሚገደው ሁሉ አስጨናቂ ጥያቄ ነው። የአገር ህልውና ጉዳይ ነውና ከስሜት ነጻ ሆኖ ማሰብ ያስፈልጋል። መለስ ኢህአዴግ ከሌለ አገሪቱ ትበታተናለች ሲል ሟርት ወይ ደግሞ የስልጣን ማራዘሚያ ማስፈራሪያ ብቻ የሚመስለው ይኖራል። ግን አይደለም። ወያኔና መሰሎቹ ባለፉት ፳፬ ዓመታት ሲዘሩት የኖሩት እኮ የአንድነትን ፍሬ አይደለም። የተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉት አብዛኞቹ በጎሳ የተቧደኑ መሆናቸን አስተውሉ (ከወያኔ የሚለዩት አቅመቢስ በመሆናቸው ብቻ ነው)። የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ ከቆዩት ቡድኖች ውስጥም ቢሆን ጠንከር ያሉትና የውጭ ድጋፍ ያላቸው ሁሉ ተገንጣዮች ናቸው።

በሩቅ ተቀምጦ ደሀ ኢትዮጵያዊያን የአጋዚ ጥይት ራት እንዲሆኑ መቀስቀስ አርበኛ አያሰኝም። እንዲያውም የለየለት ነውረኝነት ነው። ወያኔን ማውገዝ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ፤ ከወያኔ መሻል አይደለም። ወያኔን መጥላት አንድ ነገር ነው፤ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ ግን ፍጹም ሌላ ጉዳይ ነው። ከወያኔ መሻል ከወያኔ የተሻለ አማራጭ ማቅረብ ነው። ከወያኔ መሻል ከጭፍን ጥላቻ ወጥቶ ወያኔ ድንገት ቢወድቅ የኢትዮጵያ እጣ ምን ይሆናል ብሎ ማሰብ፣ መደራጀትና መስራት ነው። የወያኔን መውደቅ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ጸረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች መኖራቸውን ለአፍታም አለመዘንጋት ነው። በድፍረት እውነቱን መነጋገር፣ ሀሳብ ማመንጨት፣ መደራጀት፣ ህብረትና ከምንም በላይ ማስተዋል ይጠይቃል። ዲሞክራሲን ርሱት፤ ሲጀመር ኢዲሞክራሲያዊነት ወያኔ ያመጣው ችግር አይደለም፤ ስለዚህ ወያኔ ቢወድቅ ዴሞክራሲ ያብባል ማለት አይደለም። እንደ እውነቱ እኮ ዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ያለው የፖለቲካ ቡድን በአገራችን ኖሮ አያውቅም፤ አሁንም የለም። አንድ የፖለቲካ ቡድን ስታስቡ አንድ ሰው ብቻ ነው ትዝ የሚላችሁ። ያ ዴሞክራሲ አይደለም። በዚያ ላይ አብዛኛው በየጎሳው ተኳርፎ ነው ያለው፤ በጎሳ ተቧድኖ ስለ ዴሞክራሲ ማውራት ራስን መቃረን ነው። ወይ የሰወችን ምርጫ ታከብራለህ ያለዚያ እንደ ወያኔ ማንነት የሚለካው በቋንቋ አጋጣሚ ብቻ የሚል ተረት ተረት ስታወራ ትኖራለህ። በአንድ ጊዜ ጎሰኛም ዲሞክራትም መሆን አይቻልም። ዋናው ጉዳይ ግን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ቢያንስ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል የሚያስችላት ነው ወይ የሚለው ነው። ሌላው ሁሉ ዝርዝር ጉዳይ ነው።

ለ. ከራሳችን ታሪክ ምን ተማርን?

የንጉሱ ዘመን አክትሞ ደርግ መጣ። ብዙ ኢትዮጵያውያን ለውጡን በደስታ እንደተቀበሉት ጥርጥር የለውም።  ለውጡ ግን ወደ ቅዠትነት ሲለወጥ ጊዜ አልፈጀም። ለምን ቢባል ንጉሱን ከስልጣን ከማውረድ ባለፈ ለውጡን በተፈለገው መንገድ ለመምራት ይህ ነው የሚባል ዝግጅትም ሆነ መግባባት አልነበረምና ነው። ግብታዊ አብዮት ነበር የሚሉ ልክ ናቸው። የመግባባት አለመኖር ሁምናን ይጋብዛልና በወቅቱ የተሻለ ጡንቻ የነበረው ደርግ ክፍተቱን ተጠቅሞ ስለጣኑን በጁ አስገባና ስጋት የመሰሉትን ሁሉ መመንጠር ጀመረ። በንጉሱ ጊዜ የነበረው የፖለቲካ አስተዋይነት በአንዴ ገደል ገባ። ምናልባትም በታሪካችን ምርጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ብዙ የአገር ባለውለታወች ያለፍርድ ታረዱ። በአገራችን ፖለቲካ ያኔ ነው የሞተው። የመጀመሪያው ኪሳራ ያ ነበር። ከዚያ ኪሳራ አሁንም አልወጣንም። አደጋው ግን ያ ብቻ አልነበረም። ደርግ አገር ለመምራት ዝግጁነት ያልነበረው ከመሆኑ በላይ የስልጣን ተቀናቃኞቹን ማጥፋት ላይ ተጠመደ። የገብያ ግርግር…እንዲሉ ሶማሊያ ባቅሟ ፈነጨችብን። የውጭ ድጋፍ ባናገኝ ኖሮ ማይጨው ሊደገም በቻለ ነበር። ቪቫ ካስትሮ!

በአጠቃላይ የ ፷፮ቱ ለውጥ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኪሳራ ነበር። ከዚያ ታሪካችን ምን ተማርን? ምንም። ደርግ የቻለውን አጥፍቶ በተራው በበለጡ በጉልበተኞች ተሸነፈ። ሌላ ለውጥ። በዚህ ጊዜ ግን ዘውዳዊው መንግስት ሲገረሰስ የነበረው አይነት ተስፋ አልነበረም። ሲጀመር ደርግን ያሸነፉት ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ሳይሆን ከኢትዮጵያ ነጻ ለመውጣት በሚል በተቧደኑ ጉዶች ናቸው። የሚገርመው ቅኝ ገዢ የሚሏትን ትልቅ አገር የመግዛት አጋጣሚ ሲያገኙ አገሪቱን ከመካፈል የተሻለ መንገድ አልታያቸውም። በስልጣን ጥም ያበደ ብዙ መንገድ አይታየውም። ደርግ አስተዋይነትን ገድሎ አውሬነትን ተከለ ብያለሁ። ያሁኖቹ ጉዶች ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ገድለው ጎሰኝነትን ተከሉ። ሁለቱም ለውጦች ይሄ ነው የሚባል የፖለቲካ ጥያቄ ያልፈቱ፤ በተቃራኒው በፊት ያልነበሩ የፖለቲካና ማህበራዊ ችግሮች የፈጠሩ ነበሩ። ለነገሩ በሀይል የመጣ ለውጥ ዴሞክራሲ ሲተክል በታሪክ ታይቶ አያውቅም። የሚቀጥለው ለውጥ ሌላ ተጨማሪ ችግር እንደማያመጣ ርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ ዙሪያችሁን ተመልከቱ። አሁን ፷፮ ወይም ፹፫ ዓ.ም አይደለም። በ፷፮ የውጭ ጠላት ካልሆነ በስተቀር የአገር አንድነትን በተመለከተ ያን ያህል ስጋት አልነበረም(የሰሜኑ ገና አልደረጀም)። በ፰፫ም ቢሆን ድል አድራጊወቹ ተባብረው ታላቅ አገር መግዛት ቢፈልጉ ኖሮ የአሪቱን አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ወታደራዊና የጸጥታ ሀይል ባለቤቶች ነበሩ። አሁን ግን ማን አለ? ወያኔ ድንገት ቢወድቅ ሌላው ቢቀር ለእለት ጸጥታ ለማስከበር የሚችል አለ? የኢትዮጵያ ህልውና ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚወድቅ ማሰብና ያ እንዳይሆን ከአደጋው ግዝፈት በበለጠ መዘጋጀት ያስፈልጋል። አንድ ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ ሳይሰማ ብሄር ብሄረሰብ እያለ አድጓል።

ሐ. ምን እናድርግ?

የፖለቲካ ለውጥ በራሱ ቁም ነገር አይደለም ብያለሁ። ጭብጡ ለውጥ መምጣቱ ሳይሆን ለውጡ የሚፈለገው አይነት መሆኑ ላይ ነው። በአገራችን እንዲመጣ የምንፈልገው ለውጥ መልካም እንዲሆን ምን ማድረግ አለብን? በመጀመሪያ ባለፉት ሁለት የመንግስት ለውጦች የደረሰውን ኪሳራ መቀልበስ ያስፈልጋል። ደርግ ካመጣው ኪሳራ እንጀምር፤ የፖለቲካ ትንሳኤ የግድ ይላል። ይኸውም፤

፩. በምንም ምክንያት ላለመገዳደል ቃልኪዳን መግባት

በመጀመሪያ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል ይኖርባታል። ቀጥለን ምን አይነት ዴሞክራሲ እንደሚያስፈልገን መነጋገር ያስፈልገናል። ይሄ ሁሉ የሚሆነው ከአውሬነት ከፍ ብለን መነጋገር ስንችል ብቻ ነው። ስለዚህ ከአሁን በኋላ በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት የሚገደል ኢትዮጵያዊ አይኖርም የሚል ቃል ኪዳን ብንገባስ? ከዚህ በኋላ ጠበንጃ የምናንሳው የውጭ ወራሪ ከመጣ ብቻ ነው ብለን ብንማማልስ? ትልቅ ታሪክ ያለን ህዝብ ሆነን የፖለቲካ ልዮነታችን በሰለጠነ አግባብ መፍታት ያለዚያም ማቻቻል አያቅተንም ብለን ከልባችን ብናምንስ? መነጋገር አያቅተንም ብለን ቆራጥ አቋም ብንወስድስ? ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ብንሆንስ? የኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ ችግር ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ የፍትህ መጓደል፣ የዲሞክራሲና ነጻነት እጦት ወዘተ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ በጦርነት ሊፈታ የሚችል አለ? የለም። በየጎሳ በመኳረፍ ሊፈታ የሚችል ችግር አለ? መልሱ አሁንም የለም ነው። ታዲያ የፖለቲካ ቡድን ነን የሚሉት ሁሉ ተበጣጥሰውና ተኳርፈው ያሉት ለማን ብለው ነው? ከስልጣን ህልምና ጥቅም ያለፈ ራዕይ ካላቸው በመነጋገርና በመተባበር ቢያሳዩንስ?

Bahrdarይሄ ማለት ወያኔ ጋርም ቢሆን አንዋጋም ማለት ነው። ኢህአዴግን የመፍትሄው አካል ማድረግ ማለት ነው። አውቃለሁ ይሄ ለብዙወች አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን የትኛውም ሀሳብ ትርጉም የሚኖረው ከእውነታ ጋር ሲታረቅ ነው። ምን አልባት እንደ ወያኔ ኢትዮጵያን የበደላት ቡድን የለም። የባህር ወደብ ከግመል ማጠጫነት ያለፈ ጥቅም የለውም እያሉ በሚገዟት አገር የቀለዱ እነሱ ብቻ ናቸው። ግን ሌላም እውነት አለ፤ ወያኔወችም ኢትዮጵውያን ናቸው። በዚያ ላይ ስልጣን ላይ ናቸው። የሞቱት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ለስልጣን ነውና ስልጣናቸውን እንደዘበት አይለቁም። ወያኔ አሁን ስጋ የያዘ አንበሳ ነው። በመጀመሪያ ብዙ ሰው ገለዋል፣ አገር ቆርሰዋል፣ ብዙ በደል ፈጽመዋል። ሲቀጥል ስልጣናቸውን ተጠቅመው ብዙ ህገወጥ ሀብት ሰብሰበዋል። ስልጣን ወይም ሞት  እንደሚሉ ማንም አያጣውም። በዚያ ላይ በጣም ጠንካራ ወታደራዊና ደህንነት መዋቅር አላቸው። የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ልምዳቸውም ጠንካራ ነው። በየጊዜው ዋሽንግተን ዲሲ የሚሰለፉ ኢትዮጵያውያን የሚያስቁኝ ለዚህ ነው፤ አሜሪካ እንደ ወያኔ የሚመቻችትና የምትተማመንበት ቡድን እንደሌለ አለማወቃቸው። እውነታው በጉልበት ወያኔን ለማቸነፍ ሽራፊ ዕደል ያለው ሀይል በሩብ ምዕተዓመት አልታየም። አሁንም የለም። ግን ነጥቡ እሱ አይደልም። ከምንም በላይ ሰላምና ብልጽግና የሚኖረው ማንም ኢትዮጵያዊ ከወደፊቷ ኢትዮጵያ እንደማይገለል ቃል ስንገባ ብቻ ነው። ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ያላካተተ ለውጥ ቢሳካ እንኳን አደጋ አለው። አላማችን አንድን የፖለቲካ ቡድን በሌላ መቀየር ሳይሆን የፖለቲካ አብዮት (ማንም ዜጋ በፖለቲካ አመለካከቱ የማይከሰስበት ምህዳር) መፍጠር ከሆነ ከወያኔወች ጋር መነጋገር ይቻላል። ጥያቄው መሆን ያለበት ወያኔወች ለድርድር ዝግጁ ናቸው ወይ የሚለው ነው። ወያኔን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው፤ የማይቻል ግን አይደለም። ይቻለል! የሚቀጥለው መንግስት ወያኔ ባለው የጸጥታና የዲፕሎማሲ ልምድ ላይ መገንባት እንጂ እንደልማዳችን ከዜሮ መጀመር የለበትም። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ህዝብ እናስብ እስቲ። በህይወቴ ብዙ አገር አይቻለው፤ ኢትዮጵያ በእውነት ውብ አገር ናት። ችግሩ እንደ ህዝብ ማሰብ አለመቻላችን ብቻ ነው።

፪. አንድነታችን ማጽናት
imagesትልቅና ለምለም አገር አለችን። ለማኝ የሆንነው፣ የአረብ ገረድና ሎሌ የሆንነው፣ ዲግሪ ይዘን የፈረንጅ መኪና ጠባቂ ይምንሆነው ተረግመን አይደለም። እንደ ህዝብ ማሰብ ባለመቻላችን እንጂ። በሌላ አነጋገር ተባብረን አገራችን እንደገና ታላቅ ከማድረግ ይልቅ ውርደትን መርጠን ነው። ያን የግድ መቀየር ይኖርብናል። መነጋገር ከቻልን እኮ ምንም አይነት መሰረታዊ ልዩነት የለንም። ኢትዮጵያውያን መልካችን ብቻ አይደለም የሚመሳሰለው፤ ችግራችን፣ ፍላጎታችን፣ እጣችን ሁሉ አንድ ነው። ከልብ መነጋገር ከቻልን ችግሮቻችን ያን ያህል ግዙፍ አይደሉም። ግን ከጠባብ ከጎሰኝነት መውጣት የግድ ይላል። ይሄ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ አይነት ቋንቋ ይናገሩ፣ ተመሳሳይ ቀሚስና ሱሪ ይልበሱ፣ ለአንድ አምላክ ይስገዱ፣ ወይ ደግሞ አንድ አይነት የፖለቲካ ዕምነት ይኑራቸው ማለት አይደለም። ልዩነት የህይወት ሀቅ ነው። በሁለት ወንድማማቾች መካከል አንድ ሺ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ከሌለ ግን ልዩነታቸው ወንድምነታቸውን አያቀጭጨውም። በአንጻሩ መከባበርና ማስተዋል የተሳነው ህዝብ አንድ አይነት ቋንቋ ስለተናገረ ወይ ደግሞ ለአንድ አምላክ ስለሰገደ ከመበታተን አይድንም። ሶማሊያን ይመለከቷል። ከመኳረፍና መገዳደል ወጥተን መነጋጋርና በጋራ መስራት ከቻልን ታላቅ ህዝብ መሆን እንችላለን። በእውነት እንችላለን!

 

ሰላም ሁኑ።