ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚ አቢይ አህመድ ከታምራት ላይኔ (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር)

ታምራት ላይኔ (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር)

ታምራት ላይኔ (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር)

ኢትዮጵያን የመምራት ሃላፊነት እጅዎ ላይ በወደቀበት በእዚህ ታሪካዊ ወቅት አገሪቱን የህወሃት የበላይነት ከነበረበት የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ የስርአት ለውጥ ለማሻገር ሁለት የተሻሉ አማራጮች ከፊትዎ ተደቅነው ነበር።

አንደኛው አማራጭ በኢህአዴግ በውስጡ የተገኘውን የስልጣን ሽግሽግ በመጠቀምና ግንባሩን ራሱን መሳሪያ በማድረግ፣ በተነጻጻሪ ሰላማዊ ሊሆን በሚችል ሁኔታ፣ ደረጃ በደረጃ በሚካሄዱ ለውጦች አማካይነት ሽግግሩን ማጠናቀቅ ነው። ይህ አማራጭ የሚፈልጋቸው ቅድመ~ሁኔታዎች ግን ነበሩ፤ እነሱም እርስዎ ራስዎን የሽግግር ወቅት ጠ/ሚ ብቻ አድርገው ማየት፤ ስላም፣ ጸጥታ፣ ህግና ስርአት ማስከበር እንዲሁም ተጠያቂዎችን ለፍትህ ማቅረብ፤ ድርጅቶች ወደ አገር የሚገቡበት ለህዝብ ግልጽ የሆነ የሰላማዊ መንገድ መፎካከሪያ መስፈርቶችን በማውጣት ሁሉም ሀይሎች የሚሳተፉበት የዳያሎግ መድረኮች ተዘጋጅተው ሁሉም ጥያቄዎች (ህገ~መንግስቱና የፌዴራል መዋቅሩን ጨምሮ) ያለገደብ ለድርጅቶችም ለህዝቡም ለውይይት፣ ለክርክርና ለድርድር እንዲቀርቡ ማድረግ፤ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፤ ለነዚህ ቅድመ~ሁኔታዎች የሚያመቹ ህጋዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ፤ እስከዚያው ድረስ መንግስታዊ መዋቅሩ ሳይቀያየር በነበረበት ቆይቶ ወደ ነጻና ተአማኒ ምርጫ መሄድ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ የራስዎን ፓርቲ (ኢህአዴግም ሆነ ሌላ) ለምርጫ ማዘጋጀት መብትዎ ይሆናል። ሁለተኛው አማራጭ ስልጣን እንደያዙ ወዲያውኑ ሁሉንም ሀይሎች ኢህአዴግንም ጨምሮ የሚያሳትፍ የሽግግር  ወይም የባለአደራ (ወይም ሌላ ተመሳሳይ ስም ሊሰጠው የሚችል) አስተዳደር በማቋቋም ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ~ሁኔታዎች ባሟላ ሂደት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚያስኬደውን ጉዞ መያያዝ ነበር።

እርስዎ ሁለቱንም አማራጮች ወደ ጎን አድርገው የራስዎን ሌላ መንገድ ተከተሉ። ወይ ኢህአዴግን በአንድነት ጠብቀው የሚያሻግር ድርጅት አድርገው ሊጠቀሙበት አልቻሉም ወይም ደግሞ የሽግግር አስተዳደር አቁመው ሊያሻግሩ አልቻሉም። የመረጡት መንገድ ራስዎን ብቸኛ አሻጋሪ አድርገው ማስቀመጥ ሆነ። “አሻግራችኋለሁ” የሚለውን ቃል ኪዳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢገቡም በተግባርዎ ሊመሰክሩም ሆነ ሊያስመሰክሩ ግን ከቶ አልቻሉም። እንዲያውም የስልጣን እርካብዎን ተወጣጥተው መንበርዎ ላይ በተቀመጡ ጊዜ ባሰሙት አስገራሚ ኢትዮጵያዊ ንግግርዎ የተነሳ አግኝተውት የነበረውን በኢትዮጵያ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቀውን ድጋፍ ቢያገኙም አመት ባልሞላ ጊዜ ድጋፍዎ ሁሉ እየበነነ፣ እነሆ ዛሬ የኖቤል ሽልማትዎ እንኳ ሊያክመው ባልቻለበት ደረጃ ተከስክሶ ይገኛል። ይህ የሆነው ህዝቡ በእርስዎ ላይ የተለየ ግላዊ ጥላቻ ስላለው ሳይሆን በእርስዎ በራስዎ ተግባር የተነሳ፣ ከአሸብራቂ ንግግሮችዎ በስተቀር ፍሬውን ያልቀመሰበት ብቻ ሳይሆን ከቀድሞው ይበልጥ መራራ ፍሬ እየመገቡትና እያስመገቡት በመሆንዎ ነው። ህዝቡማ እየፈጸሙ ያሉትን ጥፋትና ስህተት ብቻ ሳይሆን ሊፈጽሙት እየተገባዎ ያልፈጸሙትን ሃላፊነትዎንም ጭምር እየታገሰ፣ እድል እንስጣቸው እያለ ከልክ ያለፈ ትእግስቱን ቸረዎታል፤ አንዳንዴ ሌሎች አላሰራ ብለዋቸው እንጂ እሳቸውማ አላማቸው ቅዱስ ነው እያለዎ፣ ሌላ ጊዜ በኦሮሞ ጽንፈኞች ተጠልፈው ነው እያለዎ፣ የሰበብ ዝርዝር እየደረደረልዎ ትእግስቱን ሰጠዎት።

በአንድ በኩል ስለ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት ዘወትር እየተናገሩ በሌላ በኩል በተለይ የኦሮሞ ብሄረተኛ ቡድኖችና የትህነግ ቡድን እንዲሁም ሌሎች እኩያን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ የጣሉ እርምጃዎችን ሲወስዱ፣ የእነ ጃዋር አይነት ዲያቢሎሳዊ ሀይሎች ከሁለት አመት በፊት በለንደን ያወጁትን የብተና አዋጅ በኢንትራሃምዌ ፋና እየተመሩ አገሪቱን ለመበታተን ተግባራዊ ሲያደርጉ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ፣ እያወቁ እንዳላወቁ ሲሆኑ የሚሰብኩትን የኢትዮጵያዊነት ስብከት ሲኖሩበት አልታዩምና ህዝቡ እምነት ቢያጣብዎት ፍርዱ ነው። ራስዎ የሚመሩት ድርጅት ኦዴፓ መሪዎችን ጨምሮ አገሪቱን አደጋ ላይ የጣሉ ብሄረተኞች እንዳሻቸው ሲሆኑ በህዝብ ገንዘብ አሉ በሚባሉት ሆቴሎች እየተምነሸነሹ፣ በመንግስት ወታደሮች ሲያስጠብቋቸው ህዝቡ ሲያይ እኚህ ሰው እውነት ለኢትዮጵያ የቆሙ ናቸው ወይስ ከትግራይ ልሂቃን የበላይነት ወደ ኦሮሞ ልሂቃን የበላይነት፣ ለሌላ ተረኝነት የተነሱ መሪ ናቸው ብሎ ቢጠረጥር ፍርዱ ነው።

አዲስ አበባ ላይ “ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን” ብለው ሲያውጁ፣ አማራ ክልል ላይ ወታደራዊ ልብስ ያስለበሰዎትን ቀልጣፋ እርምጃ ሲወስዱ፣ ያለ ማስረጃ ማሰር አብቅቷል ባሉ ማግስት ወጣቶች ሲታፈሱ፣ ያለመረጃ መታሰራቸውን ታስረው የተፈቱ ሲመሰክሩ፣ ስለ ሶሻል ሚዲያ አገር አፍራሽነት በይፋ ሲወቅሱ፣ የተቃወሙዎትን የዳያስፖራ ሰዎች “እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” ብለው ለፈጣሪ ቅጣት አሳልፈው ሲሰጡ … ወዘተ. በሌላ በኩል ግን አገር ለማፍረስ የሚደክሙትን፣ በአንድ የሶሽል ሚዲያ መልእክት ዜጎች እንዲሞቱ ምክንያት የሆነን ወንጀለኛ ግለሰብና ቡድኑን፣ አንዳሻቸው

ህዝቡ ላይ ሲፈነጩ የሚውሉትን ስርአተ አልበኞች እየተመለከቱ ምንም እንዳልሆነ ዝምታን ሲመርጡ፣ ከወንጀለኛ ጋር ድርድር ውስጥ ሲገቡ ህዝቡ ቢታዘብ ለምን ብሎ ቢጠይቅና ፊቱን ቢያዞርብዎት አሁንም ፍርዱ ነው።

ተገንዝበውትም ይሁን በውል ሳይገነዘቡት አገሪቱ ያለችበት አደጋ ከዚህ ቀደም ገብታበት የማታውቀው አይነት ነው። የአደጋው ትእይንተ~መቅድም እነሆ በአሰቃቂና በአሳፋሪ ሁኔታ ዜጎች በሜንጫ እየተጨፈጨፉ በመታየት ላይ ይገኛል። አሻጋሪ መሆንዎት ይቅርና ህዝቡንና አገርን መጠበቅ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ መሪ ሆነዋል። ህዝብንና አገርን የመጠበቅ መንግስታዊ ሃላፊነት ቢኖርዎትም፣ እንዲሁም ደግሞ ይህን ህላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ራስዎ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑበት መከላከያ ሰራዊት፤ በቀጥታ ለእርስዎ ተጠያቂ የሆነ የደህንነት ተቋም፤ አገር የማፍረሱ ፕሮጀክት ተካፋይ የሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያሉበት እርስዎ የሚመሩት የኦዴፓና የካቢኔት ተቋሞች ይዘው በሚገኙበት ስልጣንዎ ህዝብንና አገርን ሊታደጉ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ግልጽ ሆኗል። የሰሞኑ የጃዋር ቡድን ዲያቢሎሳዊ ተልእኮና እርስዎን ጨምሮ ከኦዴፓ፣ ከመከላከያና ከፖሊስ ባለስልጣናት የወሰዳችሁት አቋም፣ ከሞስኮ ከተመለሱ በኋላ ከቤተመንግስት አስከ ሃረርና አምቦ ያደረጉዋቸው ውይይቶች የነገሩ ሁሉ መደምደሚያ ሆኗል። እርስዎና ቡድንዎ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከኢትዮጵያ ይልቅ አገር አፍራሽ የኦሮሞ ብሄረተኞችን፣ የዲያቢሎስ መልእክተኛውን ጃዋርንና መሰል ቡድኑን፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ኤምፓየር ህልም እንጂ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ህልመኛ አለመሆንዎ ለደጋፊዎችዎም ሳይቀር፣ ከርስዎ የሚያገኙት ፍርፋሪ የሚያሳሳቸው ካልሆኑ በስተቀር፣ ግልጽ ሆኗል።

በነገራችን ላይ ምናልባት የሚደነግጡ ከሆነ የሚያስደነግጥዎትን ጉዳይ ላንሳልዎ። እርስዎና ቡድንዎ እናምነዋለን፣ እንከተለዋለን የምትሉትን እግዚአብሄርን~ኢየሱስ ክርስቶስን በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ ክዳችሁታል። እሬቻ የተባለውን የቃልቻ፣ የአቴቴና የዊች~ክራፍት መንፈስ፣ የወንዝና የቄጤማ አምላክ የፍቅርና የአንድነት ባህል ብሎ የዳቦ ስም ሰጥቶ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝብ እንዲሰግድለት ባወጀው ጉባኤ ግምባር ቀደም ተካፋይ ሆናችኋል፤ በፊርማችሁ አጽድቃችኋል፤ በፊታውራሪዎችዎ አማካይነት የእግዚአብሄር አምላክነት ተክዶ የእሬቻ አምላክ እንዲወደስ፣ ምልአተ~ህዝቡ በጭፈራ እንዲያመልከው አስደርገዋል። ህዝብ ያሻውን የማምለክ መብት ቢኖረውና ቢያደርግ ከእግዚአብሄር ጋር እንዲፋረድ ይተዋል። እርስዎን ግን አመልከዋለሁ የሚሉት ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንም በላይ ተጠያቂ እንደሚያደርግዎት ልብ ብለዋል? ወይስ እሬቻን የተክለሰውነትዎ መገንቢያ የስልጣንዎ መለኪያ ማድረግ ከኢየሱስ በልጦብዎት ህሊናዎን ሸፈነብዎት!! ለእሬቻ አምላክ ሰግደዋልና። የእግዚአብሄርን ክብር በእሬቻ ለውጠዋልና። የእርሱን አምላክነት ክደው የእሬቻን ጣኦት አምልከው አስመልከዋልና። እግዚአብሄር በክብሩ እንደማይደራደር ጠፋዎትን? እርስዎም በሚያውቁት የእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ካሉት ክጉዳዩ ጋር ከተያያዙት አንዱን ብቻ ባስታውስዎት፦

እግዚአብሄር አምላክህ እኔ ነኝ፤ ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ለራስህ ጣኦትን አታብጅ፤ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤” (ዘጸአት 20፡2~5) ይላል።

እንግዲህ ይህን በተመለከተ የቀረዎት ስራ እንባዎን እያነቡ ወደ እግዚአብሄር በንስሃ መውደቅ ነው፤ እርሱ ይቅር ባይ አምላክ ነውና ይቅር ይልዎታል።

እርካብዎን ተውጣጥተው መንበርዎን በያዙ ማግስት ካንድ የሬድዮ ጣብያ ጋር ባደረግሁት ቃለመጠይቅ በእርስዎ መሪነት ከፍተኛ ተስፋ ማሳደሬን በበርካታ ምክንያቶች ገልጬ ነገር ግን አንድ ዋነኛ ፈተና እንደሚጠብቅዎት አስምሬ ነበር፤ እሱም በኦሮሞ ብሄረተኝነትና በኢትዮጵያዊ አገራዊነት መካከል ቆመው የሚፈተኑበት ፈተና ነበር። ስልጣን በያዙ ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጀምሮ፣ ብዙዎች አንዴ መልአክ አንዴ ሙሴ እያሉ በጠሩዎት ጊዜ፣ ለውጥ የተባለው ነገር ሂደቱ እንደተደናቀፈ፣ ከበአለ~ሲመትዎ ንግግር ጀምሮ ተስፋ የተጣለበት የኢትዮጵያዊነት ትርክት ጨለማ ውስጥ እንደገባ፣ እርስዎም ተስፋ እንዳደረግሁብዎት እንዳልሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማገኛቸው ሰዎች ሃሳቤን በእርግጠኝነት ግን በሃዘን መንፈስ ገልጬላቸው እንደነበር የሚያውቁት ሰዎች ያስታውሳሉ። በየጊዜውም በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበው አደጋ ምን እንደሆነ ምንም ብዥታ አልነበረኝም፤ አሁንም ምን ጊዜም ኢትዮጵያን በሚመለከት እምነቴ በእግዚአብሄር ላይ ብቻ ቢሆንም አገራችን ያገኘችውን እድል እንደገና እያጣች ከእስከዛሬው በባሰ ችግር ውስጥ እየገባች በመሆንዋ ግን ያሳዝነኛል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፈተናዎን መውደቅዎ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ያዩት እውነታ ሆኗል። ሆኖም ግን በፈተና የወደቀ እንደወደቀ እንደማይቀር ከሌላ ሳይሆን እኔ ራሴ ከፈተና ወድቄ ያልቀረሁበት፣ እንዲያውም በበለጠ ትምህርት የተነሳሁበት ምስክርነት ስላለኝ ወድቀው ይቀራሉ ብዬ ለመበየን የምዳዳበት የሞራል እሴት የለኝም። እንዲያውም ከእኔ ወድቆ~መነሳት እድል ይልቅ እጅጉን የሚበልጥ ምቹ ሁኔታ አለልዎትና ይበርቱ፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ የወንድምነቴን ምክር ልምከርዎት፦

1) ከሁሉም በፊት የሚያስፈልግዎት ጉዳይ ፈረንጆቹ Shift of Mind ወይም ከግሪኩ በተወረሰው ቃል Metanoia የሚባለው ታላቁ መጽሀፍ ደግሞ “የአእምሮ መታደስ” የሚለው ነው። የራስዎን ተክለ~ሰውነትና ተክለ~ስልጣን ከሚያስቡበት እይታ (Mind Set) ወጥተው የራሴ ጉዳይ የፈለገው ሊሆን ይችላል፣ ለህዝቡና ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን ላድርግ ወደሚለው እይታ ራስዎን ያሽጋግሩ። ይህን ማድረግ 180 ዲግሪ መዞርን ስለሚያስከትል ደፋር ውሳኔ ይጠይቃል፤ ግን ፈቃደኝነት ካለዎት ይቻላል።

2) ወደዚህ ውሳኔ እንዲደርሱ ሊረዳዎት የሚችለውን የብዙዎቹ ችግሮችዎ ምክንያት የሆነ አንድ ህመም ስላለ ከዚያ ይፈወሱ ዘንድ እጠይቅዎታለሁ፦ እሱም ራስዎን መካድ አለመቻልዎ ነው። አሁንም በኢየሱስ ክርስቶስ ቋንቋ ብነግርዎት ይበልጥ ይገባዎት ይመስለኛል፦

“ሊከተለኝ የሚፈልግ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየእለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። ሰው አለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ጥቅሙ ምንድነው?” (ሉቃስ 9፡23~25)።

ለግል ተክለሰውነትዎና የስልጣንዎ አለም ለሚያተርፍልዎ ትርፍ ከቶ አይጨነቁ፤ በቅድሚያ ለእግዚአብሄር ቀጥሎ ደግሞ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ትክክል ለሆነው ነገር ብቻ እስቲ ለመኖር ይጀምሩ፤ እግዚአብሄር እጅዎ ላይ ያስቀመጠው የእለት~ተእለት መስቀልዎ አሁን ይኸው ብቻ ነው። ከተክለሰውነትዎና ከስልጣን አለምዎ ይልቅ ነፍስዎን ቢያተርፉ አይሻልዎትምን?

3) ከኦሮሞ ብሄረተኝነት ጥላ ይውጡና የማንም ብሄረተኛነትም ቢሆን ሳይጎትትዎት ለኢትዮጵያ አገራዊነት ብቻ ይቁሙ። ይህን ቢያደርጉ የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር እንደሚጋጩ ግልጽ ነው፤ ግን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጋጭተው የኢትዮጵያ አፍራሾችን ከሚያተርፉ ከኢትዮጵያ አፍራሾች ጋር ተጋጭተው ኢትዮጵያን ቢያተርፉ ለራስዎም ይሻልዎታል፣ ለህዝቡም የሚጠቅመው ይኸው ነው። መጀመሪያ አግኝተውት የነበረውን ድጋፍ ሊመልሱት የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ደግሞስ የዘውገኛ አጀንዳ መሳሪያ ከመሆን በልበ ሙሉነት ኢትዮጵያን ብለው የሚመጣውን ቢጋፈጡ አይሻለዎትም? አንዳንድ ምርጫዎች የሚያሳምሙ ቢሆኑም ውጤታቸው ከእውነት ጋር ስለሚያስቆም ይመረጣሉ። ለዚህ ምርጫ የሚሆን ድፍረት የሚያስፈልግዎት ጊዜ አሁን ነው። የመጽሀፍ ቅዱሷን የአስቴርን ታሪክ ያስታውሱታል? መርዶክዮስ ለአስቴር የላከላት የመጨራሻ መልእክት እኮ የሚከተለውን ነው፦

“አንቺ በንጉስ ቤት በመሆንሽ ብቻ ሌላው የአይሁድ ህዝብ ሲጠፋ አንቺ የምትተርፊ እንዳይመስልሽ፤ በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትይ፣ ለአይሁድ እርዳታና ትድግና ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ አንቺ ንግስት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?” (መጽሃፈ አስቴር 4፡13~14)።

እንደሚያውቁት አስቴር በዚህ የመርዶክዮስ ምክር ሰልፏን አስተካክላ አይሁድንም ራሷንም ከጥፋት ለማትረፍ ወሰነች፤ እግዚአብሄር ተጠቀመባት። እርስዎ ቤተመንግስት የገቡት ለዚህ ጊዜ እንዲጠቅሙ መሆኑን ማን ያውቃል? እርስዎ ከኢትዮጵያ አፍራሾች ጋር ቢተባበሩና ዝም ቢሉ እግዚአብሄር ለኢትዮጵያ እርዳታና ትድግና ሌላ ሰው ለማስነሳት እንደማይገደው ይጠራጠራሉ? በዚያን ጊዜ ግን እርስዎና ቤትዎ ከጥፋት እንደማይድኑ እርግጠኛ ነዎት? እንዲሆኑ የተፈለገብዎትን ሳይሆኑ እየቀሩ ነውና ሌላው መርዶክዮስ ሆኜልዎት እንደሆነስ ማን ያውቃል??

4) ይመስልዎት ይሆናል እንጂ እርስዎ በራስዎ ብቻ ሁሉን ነገር አዋቂ አይደሉም፣ ማንም ቢሆን ሁሉ~አዋቂ ከቶ ሊሆን አይቻለውም። ስለዚህ ለሌሎች ሰዎችን ምክርና ተግሳጽ ጆሮዎትን ያዘንብሉ። እርስዎን ከመጥላት ወይም ለእርስዎ ክፉ ከመመኘት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ከመሳሳት፣ ተልእኮዎ እንዲሳካ ከመመኘት የሚሰነዘርን ምክርና ተግሳጽ ከልብዎ ያድምጡት፣ ይፈልጉትም። ይህን መሳዩን ምክርና ተግሳጽ ሊለግሱዎት እየሞከሩ በጆሮ ዳባነት፣ በንቀትና በለበጣ የመለሱዋቸው በርካታ ሰዎች፣ ወዳጆችዎ የነበሩ ሳይቀር አዝነው እንደተዎት ያውቃሉ? በአካባቢዎ ሳይጠሩዋቸው አቤት ሳይልኩዋቸው ወዴት የሚሉዎትን አሸርጋጆች ብቻ ሳይሆን ካልጠቀመ አይጠቅምም የሚሉዎትን፣ ሲሳሳቱ ተሳስተዋል የሚሉዎትን ይሰብስቡ። መልካም ምክር የሚያገኙት ከእነዚህኞቹ ነውና።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ! ጸሀይቱ ከመግባቷ በፊት በነዚህ ምክሮች ረዘም ያለ የጽሞና ጊዜ ይወስዱ ዘንድ በታላቅ አክብሮትና ትህትና እለምንዎታለሁ፤ ባለቤቴና አኔ እንደወትሮው ሁሉ በእንባ ጭምር እንጸልይልዎታለን።

እግዚአብሄር እርስዎንና ቤተሰብዎን ይባርክ!

ጥቅምት 2012 አ.ም. አዲስ አበባ

7 COMMENTS

  1. Comment: Really God bless you. This is I think the last word God has told through you before His crucially envitable intervention to save His blessed country and show His faithfullness to His word.

  2. የተከበሩ ታምራት ላይኔ ጥሩ ብለዋል።ጥሩ ሄደው ሲያበቁ ነገሩን መልሰው አበላሹት።አስቴርና አይሁድ ጋር ሲደርሱ ነገሩን አምታቱት።የአለምና የኢትዮጵያ አንዱና ቀዳሚው የችግር መንስኤ ክርስቶስን የሰቀሉት የአይሁዶች ሴራ ነው።የተቀረው አለም በተለይም ምእራቡ አለም የአደባባይ ሚስጥር አድርጎ የነቃበትን ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ እነሱን እንደ ቅዱስ በመቁጠር ጭራሽ በረቀቀ መንገድ መከላከልና መሸፋፈን ነው የተያዘው።የክርስትና መስራች የሆነው እራሱ እየሱስ ክርስቶስ በ1ኛ ዮሀንስ 8:44 ማቴዎስ 23:15 ማቴዎስ 23:35 በግልፅ ያወገዛቸውን እኛ የክርስቶስ ተከታይ ነን የምንል ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ የነሱ ጠበቃ ለምን እንደሆንን አልገባኝም። በዮሀንስ ራእይ 2:9 3:9 በራእይ 17 እስከ 18 ያለው ሲነበብ አሁን በግሎባላይዜሽን ሽፋን በአለምና በኢትዮጵያ የተዘረጋው ስርአት ምን እንደሆነ የሚጠቁም ግልፅ ማስረጃ ነው።
    በመላው አለም በኢትዮጵያም ጭምር ክርስትናው እራሱ በአይሁዶች ሴራ ውስጡን ተቦርቡሮ ምስጥ የበላው እንጨት እየሆነ አይደለሞይ?በኮሙኒዝም በአብዮት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በግሎባላይዜሽን ሽፋን ከደርግ ጀምሮ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀስ በቀስ የተዘረጋው ስርአት የአይሁዶቹ መሆኑን ስንቶቻችን ገብቶናል?በአገሪቱ የተፈጠረው ስር የሰደደ የሞራል ዝቅጠት ነውረኝነት ሙስና ጭካኔ ስደት መፈናቀል ፀረ-ኢትዮጵያዊነት መንስኤው ይሄው የአይሁዶቹ ፀረ- ክርስቶስ መንፈስ ያመጣው ነው።
    አለም አቀፍ ክስተት ስለሆነ ሁኔታውን መቆጣጠር እና ማስቆም ይቻላል ወይንስ አይቻልም የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ እውነታውን መረዳት እና ማመን ግን ጠቃሚ ነው።ዘሃበሻ አይለጥፈውም እንጂ የአይሁዶቹን ፀረ -ክርስቶስ ፀረ-ክርስትና ፀረ-ክርስቲያን ሴራ የሚገልጡ ብዙ የውጪ ሃገራት ፅሁፎችን እና ድህረገፆችን መጥቀስ ይቻላል። ለጊዜው
    “Solving The Mystery Of Babylon The Great” By Edward Hendrie ” እና ሌሎችንም ድንቅ ነገሮች ከሚከተለው ድህረ ገፅ ላይ ፈልጎ መመልከት ይቻላል።
    antichristconspiracy
    mysterybabylonthegreat
    ኢትዮጵያ ያለችበት ፈታኝ ቀውጢ ሁኔታ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች እንዲዳሰሱ ግድ ይላል።አንድ ነገር ልጨምር።ክርስቶስን የሰቀሉት አይሁዶች አንድ የሚያምኑበት ነገር አለ።ይሄውም የእኛ መሲህ ከወደቀበት ጥልቁ አለም ተነስቶ እንዲገለጥና ወደቀድሞ ክብሩ እንዲመለስ ሁለት አማራጮች አሉ ብለው ያምናሉ።የመጀመሪያው አለም ሙሉ በሙሉ የተቀደሰ ፃድቅና ሰላም መሆን አለበት። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ አለም ሙሉ በሙሉ የረከሰ እርኩስ እና ቀውጢ መሆን አለበት። የመጀመሪያው አስቸጋሪ ነው ብለው ስለሚያምኑ ሁለተኛውን አማራጭ ነው እየተከተሉ ያሉት።በሁለተኛው አማራጭ የሚገለጠው ደግሞ የጥፋት ልጅ እርኩሰት የሆነው ፀረ-ክርስቶስ አሳሂ መሲሁ እንደሆነ ግልፅ ነው።የኢትዮጵያና የአለም ሁኔታ እንደዚህ ባለ ደረጃ ወደ ቀውስ እና እርኩሰት እየተገፋ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።ኢትዮጵያ የፀረ ክርስቶስ የአይሁዶች መዳፍ ውስጥ ወድቃለች።በተለያየ ሽፋን የተዘረጋው ስርአትም የነሱ ስርአት ነው።የነሱ ስርአት አገልጋይ የሆኑ ጥቂቶች ተጠቃሚ የሆኑበት እርዳታና ብድሩ የጎረፈውም በዚህ ምክንያት ነው።

  3. Dear Mr. Tamrat,

    Thanks for the wonderful advice which is both honest and timely. Hope the PM reads it.

    PM Abiy should wake up and act swiftly. I think God will judge him based on what his intentions are and what he would do to save Ethiopia and its people.

    May God save Ethiopia!

  4. Tamirat Layne comments on Oromo Irreecha saying it is not biblical. On this basis he advises the current PM of Ethiopia as if he denied the God he claims to praise. Tamirat quotes Exodus 20:2-5. But why Tamirat forgot his ancestral witchcraft in Ethiopian Orthodox where they carry acacia box on their head and take it to river to worship it?

    Why Tamirat vows on PM Abiy where he seems very partial for he never talk about oppressed nations at the hand of his Solomonic dynasty lines.

  5. አንተን ብሎ ምክር ሰጪ!!? በ1992 አ ም የናዚዎችን አይነት ኦሮሞን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ‘The Final Solution’ የተባለ የፕላን ሰነድ ያዘጋጀህ አይደለህም?? የአንተ አይነቶቹ የኑርንበርግ አይነት ችሎት ፊት መቅረብ ሲገባ ደግ እንደሠራ ሰው ዞረህ መካሪ መሆን ትፈልጋለህ??!! ባንተ ከተደገሰልን የዕልቂት ጽዋ የተረፍን ስላለን አንገትህን ብቅ ብቅ ማድረጉን ብታቆየው ይሻልሃል!

  6. ታምራት ላይኔ ወይም ጌታቸው የቀድሞው የወያኔ ቀኝ እጅ በመሆን በሃረር በኣርሲ አማርሮች ይጨፈጨፉ ዘንድ ዛሬ ድረስ የጨካኞች ኢላማ እንዲሆኑ ሽርጣም ብሎ የጨቆነህ አማራ ብሎ ክፉ ዘር የዘራ ነው:: የታምራት የቀድሞ ባልደረባ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደታምራት ሌባ አይደለሁም ብሎ በይፋ የመሰከረበት ጉድ ዛሬ የዶር አብይን ጥረት በዚህ በጥላቻ 27 አመታት መሉ የተሞላ ህዝብን በማቻቻል ያለተጨመሪ እልቂት የጥበብ የትእግስት አመራር ለመተቸት አንዳች ብቃት የለህም:: ይልቅስ አመንኩ ያልከውን ጌታን በደንብ በማወቅ ሙሉ ይፋ ይቅርታ በማድረግ እጅህንም አፍህንም በማንጻት በጸጥታ ተቀመጥ:: በአንተና በባልደረቦችህ የጥላቻ ቅስቀሳ የታረዱት ወገኖቻችንን አጽም አትርገጥ መጀምሪያ መቀሌ የመሸጉትን ካንተ ጋር ስኩዋር የበሉትን በበበቂ ማስረጃ አጋልጥ::

  7. ኣሁን ባለው የኢሃዴግ እና የመንግስት ኣወቃቀር መሰረት ዶ/ር ኣብይ እንደድሮው ኣለቃህ ኣንባ ገነን ካልሆነ በስተቀር ሀገራዊ እና ጎሳዊ ፍላጎቶችን ኣሙኣልቶ መምራት ከቶ ኣይቻለውም። The structure is inherently defective and mutually exclusive.
    one flourishes at the expense of other .
    ኣሁን ያለው ምርጫ የጀመረውን የእሁድ ፓርቲ ኣቁዋቁሞ ሀገራዊ እይታ እና መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ነው ለዚህም ጥረት ውስጥም ሆነ ውጭ ያለነው ልናበረታታው ይገባል።
    የጎጥ ኣመራር ፣ ሰላማዊን ሰው በጎሳው ብቻ በገጀራ ማረድ ፣ ጡት መቁረጥ፣ ከእምነት ቦታዎች የተጠለሉን ገብቶ መቆራረጥ፣ ሆስፒታል ያለን ህሙም ኣልጋው ላይ እንዳለ መተልተል፣ፖሊስ ጣቢያ ኣድኑኝ ብሎ የገባን በጉልበት ኣውጥቶ መጨፍጨፍ፣ ኣቡላንስን ማገት……..etc ውጤቶቹ ናቸው።የማህበራዊ ዝ ቅጠት ጫፍ !! It needs not to repair but to remake all together.
    ትውልዱን በትምህርት ኣደንቁረው፣ የኣለምን globalization /ኣብሮ የመኖርን ባህል፣ ሱልጡን ሰው መለያ ለኔ ማለቱ ሳይሆን፣ የራስን ለሰው ኣሳልፎ መስጠትን ሂደት እንዳያውቅ ኣርገው፣ - ከወገኑ እንዳይግባባ ኣማሪኛን እንዲጠላ ኣርገው የጥላቻ ኣጋሰሳቸው ያደረጉት ማንም ሳይወክላቸው የኦሮሞ ‘ወኪሎች’ ነን ባዮች ጥቂት ምሁራን ናቸው።ታሪክ ይፋረዳቸዋል።
    ይህን ሁኔታ ኣብይ ያለ ሀገራዊ ፓርቲ ሊያሻሽለው ፣ ለቀይረው ኣይቻለውም ፣ ለዚህ ነው የጎሳ ፖለቲካ ነጋዴዎች እሪታቸውን እየለቀቁ ያሉት ሰሚ ግን የላቸውም። ዋሸው እንዴ ?? ኣባጫላ ፣ በቄ ፣ ኢስቄል፣ and Co.
    የጊዜው መፈክር ፤-
    ኢትዮጵያን ያለ ; በጋራ ለሁሉ እኩል የሆነችን በነጻነት ይገንባ !!
    ኢትዮጵያን ያላለ ከኢትዮጵያ ይውጣ !!
    እንግዳ ተመቸኝ ብሎ ባለቤትን ሊያስውጣ ከቶ ኣይቻለውም !!! Call a spade a spade !!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.